ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ተረፈ ባሮክ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ባሮክም ይህን ከተናገረ በኋላ ንስሩ ደብዳቤውን ይዞ በረረ፤ ወደ ባቢሎንም ሄዶ በምድረ በዳ ባለው ቦታ ከከተማ ውጭ ባለ ዛፍ ላይ ዐረፈ። 2 ኤርምያስ እስኪያልፍ ድረስ ሌሎችም ወገኖች እስኪያልፉ ድረስ በዚያው ቈየ፤ ኤርምያስም ናቡከደነፆርን ከወገኖች የሞተውን የምቀብርበት ቦታ ስጠኝ ብሎ ለምኗልና፥ እርሱም ሰጥቶታልና ሕዝቡ የሞተውን ሰው ሊቀብሩ በዚያ በኩል ዐለፉ። 3 ለሞተውም ሰው እያለቀሱ ሲሄዱ ከንስሩ ፊት ደረሱ። 4 ንስሩም በዚያ ቦታ ሆኖ በታላቅ ቃል አሰምቶ ጮኸ፤ “አምላክ የመረጠህ ኤርምያስ ሆይ፥ ለአንተ እነግርሃለሁ፤ ሄደህ ሕዝቡን ሁሉ ሰብስባቸው፤ እኔ ያመጣሁትን መልካም የምሥራች እስኪሰሙ ድረስ ወደዚህ ይምጡ” አለው። 5 ኤርምያስም ይህን ሰምቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው፤ ያንጊዜም ሕዝቡን ሁሉ ሚስቶቻቸውንም፥ ልጆቻቸውንም ሰበሰበ፤ እነርሱም ንስሩ ወዳለበት ደረሱ። 6 ንስሩም ሬሳው ወዳለበት ወርዶ ረገጠው፤ ሙቱም ተነሣ፤ ይህንም ያደረገ ስለ ተደረገላቸው ተአምራት ሕዝቡ ሁሉ ያምኑና ያደንቁ ዘንድ ነው። 7 እነርሱም፥ “ከሙሴ ጋር በምድረ በዳ ሳሉ ለአባቶቻችን የታያቸው አምላካችን እነሆ፥ ይህ ነው፤ ዛሬም በታላቅ ንስር አምሳል ለእኛ የታየን እርሱ ነው” አሉ። 8 ንስሩም ኤርምያስን እንዲህ አለው፥ “መጥተህ ይህን ደብዳቤ ከፍተህ ለሕዝቡ አንብብላቸው።” እርሱም ለሕዝቡ አነበበላቸው። 9 ሕዝቡም በሰሙ ጊዜ ሁሉም አንድ ሆነው አለቀሱ፤ በራሳቸውም ላይ አመድ ነሰነሱ፤ ኤርምያስንም፥ “ወደ ሀገራችን እንገባ ዘንድ ምን እናድርግ? ንገረን” አሉት። 10 ኤርምያስም ተነሥቶ፥ “በደብዳቤ የሰማችሁትን ሁሉ እንደዚሁ አድርጉ ወደ ሀገራችሁም ይመልሳችኋል” አላቸው። 11 ኤርምያስም ለባሮክ እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ፥ “ልጄ ወዳጄ፥ በኀጢአተኛ ንጉሥ ትእዛዝ እስክንወጣ ድረስ ይቅር ይለን ዘንድ፥ ወደ ጎዳናችንም ይመራን ዘንድ ለአምላካችን እየተገዛህ ስለ እኛ መጸለይን ቸል አትበል። 12 አንተ ግን ወደ ባቢሎን ተማርከው ከመጡ ወገኖች ጋር ልትመጣ ባልተወህ በአምላክ ፊት ባለሟልነትን አገኘህ። 13 አንድ ልጅ እንዳለው አባት፥ ልጁም ይፈረድበት ዘንድ እንደ ተሰጠ፥ የሚያረጋጉት በአባቱ ዘንድ ያሉት ሰዎችም አባቱ በኀዘን ሲጐሰቍል እንዳያዩት ፊታቸውን እንደሚሸፍኑ፥ 14 እንደዚሁ አምላክህ አንተን ይቅር አለህ፤ እኛም ወደዚህ ሀገር ከደረስን ጀምሮ እስከ ዛሬ ከኀዘን አላረፍንምና የሕዝቡን መከራ እንዳታይ ወደ ባቢሎን ትመጣ ዘንድ አልተወህም። ወደዚህ ሀገር ከመጣን ጀምሮ ለስድሳ ስድስት ዓመታት ከኀዘን አላረፍንም። 15 ወደ ንጉሡ ወደ ናቡከደነፆርም አንጋጠው እያለቀሱ “አቤቱ፥ የሶሮት አምላክ ሆይ፥ ይቅር በለን” የሚሉ ከሕዝቡ አገኘን። 16 እኒህ ያዘኑ ሰዎች ሌላውን አምላክ ሲጠሩ “ይቅር በለንም” ሲሉ ይህን ነገር በሰማሁ ጊዜ አዝኜ አለቀስሁ። 17 ዳግመኛም እኔ ሳንማረክ በኢየሩሳሌም ያደረግነውን በዓል ዐሰብሁ፤ ይህንም ዐስቤ እየተጨነቅሁና እያለቀስሁ ወደ ቤቴ እመለስ ነበር። 18 አሁንም ከፋርስ ሀገር እንዲወጡ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ፥ ከአፌ የወጣውንም ነገር ይቀበሉ ዘንድ ስለ ወገኖቻችን አቤሜሌክና አንተ ባላችሁበት ቦታ ፈጣሪያችንን ለምኑ። 19 አሁንም በኖርንበት ዘመን ሁሉ “ፈጣሪያችሁ በጽዮን ከሚመሰገንበት ምስጋና ወገን አዲስ ምስጋናን ንገሩን” ብለው ያዙን ብዬ እነግርሃለሁ። 20 እኛም፥ “በባዕድ ሀገር ሳለን እንደ ምን እንዘምርላችኋለን?” አልናቸው። 21 ኤርምያስም እንደዚሁ አድርጎ ጽፎ ደብዳቤውን በንስሩ አንገት አስሮ “በሰላም ሂድ፤ ጌታም አንተን ይጐብኝህ” አለው። 22 ንስሩም ደብዳቤውን ይዞ በርሮ ሄደ፤ ደብዳቤውንም ወደ ባሮክ አደረሰ፤ ባሮክም ደብዳቤውን ከፍቶ አነበበው፤ የሕዝቡንም ኀዘንና መከራ በሰማ ጊዜ አለቀሰ። 23 ኤርምያስ ግን ያን በለስ ተቀብሎ በሕዝቡ ዘንድ ላሉ በሽተኞች ሰጣቸው። 24 የባቢሎንንም አሕዛብ ርኵሰት እንዳይሠሩ እያስተማራቸው ተቀመጠ። 25 እግዚአብሔርም ሕዝቡን ከባቢሎን የሚያወጣባት ቀን በደረሰች ጊዜ፥ 26 ጌታ ኤርምያስን እንዲህ አለው፥ “አንተ ተነሥ፤ ወገኖችህም ይነሡ፤ ወደ ዮርዳኖስም ኑ፤ ለሕዝቡም የባቢሎንን ሕዝብ ሥራ ይተዉ ዘንድ ጌታ ይወዳል በላቸው። 27 ከእናንተ ሴቶችን ያገባ ወንድን፥ ወንዶችን ያገቡ ሴቶችንም ፈትናቸው፤ ቃልህን የሰሙ ሰዎችን ወደ ኢየሩሳሌም መልሳቸው፤ ያልሰሙህን ሰዎች ግን ወደ እርሷ ይገቡ ዘንድ አትተዋቸው።” 28 ኤርምያስም እንዲሁ ይህን ሁሉ አነበበላቸው፤ ሊፈትናቸውም ወደ ዮርዳኖስ አመጣቸው፤ ጌታም ያላቸውን ይህን ነገር ሲነግራቸው ያገቡ ሰዎች ተለያዩ፤ ሊፋቱም አልወደዱም፤ ኤርምያስንም አልሰሙትም። 29 “ሚስቶቻችንን ለዘለዓለሙ አንተውም፤ ከእኛ ጋራ ወደ ሀገራችን እንወስዳቸዋለን” ያሉ ሰዎችም ነበሩ፤ ከዮርዳኖስም ተሻግረው ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። 30 ኤርምያስና ባሮክ፥ አቤሜሌክም “ከባቢሎን ሴት ያገባ ሰው ሁሉ ወደ ሀገራችን አይገባም” ብለው ተነሡ። 31 ሚስት ያገቡ ሰዎችም ባልንጀሮቻቸውን፥ “ተነሡ፤ ወደ ባቢሎን እንመለስ” አሏቸው ወደ ባቢሎንም ተመልሰው ሄዱ። 32 የባቢሎንም ሰዎች ባዩአቸው ጊዜ ሊቀበሏቸው ወጡ፤ “እናንተ አስቀድማችሁ እኛን ጠልታችሁናልና ከእኛ ተሰውራችሁ ወጣችሁ” ብለው ወደ ባቢሎን ይገቡ ዘንድ አልተዉአቸውም። 33 “ከእኛ ተሰውራችሁ ስለ ወጣችሁ እናንተንና ሴቶች ልጆቻችሁን እንዳንቀበላችሁ በአምላካችን ስም ምለናልና ስለዚህ ነገር በደላችሁ፤ ወደ ሀገራችንም አትገቡም” አሏቸው። 34 እንደዚያም ያለውን ቃል ሰምተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በኢየሩሳሌምም አውራጃ ከተማ አቀኑ፤ ያንም ከተማ ሰማርያ አሉት። 35 ኤርምያስም “ንስሓ ግቡ፤ እነሆ፥ የጽድቅ መልአክ ይመጣል፤ ለብዙ ዘመንም ወደምትኖሩበት ቦታችሁ ይመልሳችኋል” ብሎ ወደ እነርሱ ላከ። እነርሱም ደስ ብሏቸው ስለ ሕዝቡ መሥዋዕት እየሠዉ ሰባት ቀን ተቀመጡ። 36 ይህም ከተደረገ በኋላ በዐሥረኛው ቀን ኤርምያስ ብቻውን ወጣ። 37 ኤርምያስም እንዲህ ብሎ ጸለየ፥ “ለሰው በጎ መዓዛ የምትሆን አንተ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ወደ አንተ እስክደርስ ድረስ ዕውቀትን የምትገልጥልኝ እውነተኛ ዐዋቂ አንተ ነህ። 38 ስለ ወገኖችህ ስለ እስራኤልም እለምንሃለሁ፤ ስለ ተወደደው ስለ ሱራፌል ምስጋና፥ በጎ መዓዛ ስላለው ስለ ኪሩቤልም ዕጣን እለምንሃለሁ፤ የጽድቅ ሊቀ መላእክት ሚካኤልም በእውነት አመስጋኝ ነው፤ የሚያበራልኝ፥ ጻድቃንም እስከ ገቡባቸው ድረስ የጽድቅ በሮችን የሚከፍትልኝ እርሱ ነው። 39 የሁሉ ጌታ አቤቱ፥ እለምንሃለሁ፤ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አንተ ነህ፤ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ፈጥረህ የጨረስህ፥ የተሰወረው ሁሉ፥ ሳይፈጠርም ተሰውሮ የነበረው ሁሉ በአንተ ዘንድ አለ።” 40 ይኽንም ጸለየ፤ ጸሎቱንም ከፈጸመ በኋላ ኤርምያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ቆመ፤ ባሮክና አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ኤርምያስም ነፍሱ ከሥጋው እንደ ተለየች እንደ አንድ ሰው ሆነ። 41 ያንጊዜም ባሮክና አቤሜሌክ ወድቀው በታላቅ ድምፅ ጮሁ፤ “ወዮልን! የአምላክ ካህን አባታችን ኤርምያስ ከእኛ ተለየ” አሉ። 42 ሕዝቡም እንዲህ ሰምተው ወደ እርሱ ሮጡ፤ ኤርምያስንም ወድቆ እንደ ሞተም ሆኖ አገኙትና አለቀሱ፤ ልብሶቻቸውንም ቀደዱ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ፤ መራራ ልቅሶንም አለቀሱ። 43 የሚቀብሩበትንም ካዘጋጁ በኋላ “ደኅና ነውና ነፍሱም ዳግመኛ ወደ ሥጋው ትመለሳለችና አትገንዙት” የሚል ቃል መጣ። 44 ይህንም ቃል በሰሙ ጊዜ ዳግመኛ ነፍሱ ወደ ሥጋው እስክትመለስ ድረስ እየጠበቁት ሦስት ቀን በዙሪያው ተቀመጡ እንጂ አልገነዙትም። 45 በሁሉም መካከል እንዲህ የሚል ቃል ተሰማ፤ “በአንድ ቃል አመስግኑት፤ አምላካችንን አመስግኑት፤ ሁላችሁም የአምላክን ልጅ መሢሑን አመስግኑት። 46 የዓለሙ ሁሉ ብርሃን የአምላክ ልጅ ኢየሱስም ይፈርድባችኋል። 47 የማይጠፋ ብርሃን፥ የሃይማኖትም ሕይወት ነው። 48 ከዚህ ዘመን በኋላም ወደ ምድር ለመምጣቱ ሦስት መቶ ሠላሳ ሦስት የቀን ሱባዔ ይሆናል። 49 “በገነት መካከል ያለ ያልተተከለ የሕይወት ዛፍ፥ ዛፎችን ሁሉ ፍሬ እንዲያፈሩ፥ የደረቁትም ወደ እርሱ እንዲመጡ ያደርጋቸዋል። 50 ፍሬ እንዲያፈሩ፥ እንዲለመልሙና እንዲያድጉም ያደርጋቸዋል፤ ሥሩ ምድርን እንዳልያዘ ተክል ሥራቸው እንዳይደርቅ ለሰማያዊ አምላክ ግብርን እንስጥ፤ ቀይ መልክ ያለው ቀለምም እንደ ባዘቶ ይነጣል። 51 የጣፈጠው ውኃ መራራ ይሆናል፤ መራራውም የጣፈጠ ይሆናል፤ በልጁም አንደበት ፍሬን ያፈሩ ዘንድ እግዚአብሔር በታላቅ ሐሤትና ደስታ ደሴቶችን ይመርቃቸዋል። 52 እርሱም ራሱ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፤ እኔ ሰው ሆኖ ያየሁት፥ ከአባቱም ወደዚህ ዓለም የሚላከው፥ ሰው ሆኖም ወደዚህ ዓለም የሚመጣው፥ እርሱ አብሯቸው ይታይ ዘንድ፥ ይገለጥላቸውም ዘንድ ዐሥራ ሁለት ሐዋርያትን ለእርሱ ይመርጣል፤ ወደ ደብረ ዘይትም ይሄዳል፤ የተራበችንም ነፍስ ሁሉ ያጠግባል።” 53 ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ ኤርምያስ የአምላክን ልጅ ነገር እንዲህ ተናገረ። 54 ሕዝቡም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ኤርምያስ፥ “የአምላክን ልጅ አምላክን አየሁት” ብሎ ስለ ተናገረው ስለዚህ ነገር ተቈጡ፤ እነሆም፥ “በኢሳይያስ እንዳደረግን በእርሱም እናድርግበት፤ ተነሡ” አሉ። እኩሌቶቹ፥ “በደንጊያ ወግረን እንግደለው እንጂ አይሆንም” አሉ። 55 ባሮክና አቤሜሌክም፥ “በዚች ሞት አትግደሉት” ብለው ጮሁላቸው፤ ባሮክና አቤሜሌክም ስለ ኤርምያስ አዘኑ። 56 ዳግመኛም ያያቸውን የተሰወሩ ምሥጢሮችን ይነግራቸው ዘንድ አልተዉትም፤ ኤርምያስም፥ “ያየሁትን ሁሉ እስካስተምራችሁ ድረስ እኔን መግደል አይችሉምና አታልቅሱ” አላቸው። 57 “አሁንም አንዲት ድንጋይ አምጡልኝ፤” አላቸው፥ እነርሱም አንዲት ድንጋይ አመጡለት፤ እርሱም አቆማት፤ “የዘለዓለም ብርሃን ሆይ፥ ይህቺን ድንጋይ እንደ እኔ ትሆን ዘንድ አድርግልኝ” አለ። 58 ያንጊዜም ድንጋዩ ኤርምያስን በመልክ የሚመስለው ሆነ፤ ኤርምያስንም መሰላቸውና ድንጋዩን በድንጋይ ይደበድቡ ጀመር፤ ወንጀልንም ጨረሱ። 59 ኤርምያስ ግን ያያቸውን ምሥጢሮች ሁሉ ለባሮክና ለአቤሜሌክ ነገራቸው፤ ይህንም ነግሯቸው ከጨረሰ በኋላ ምግብናውን ይፈጽም ዘንድ ወደደ፤ ሄዶም በሕዝቡ መካከል ቆመ። 60 ያንጊዜም ያ ድንጋይ፥ “እናንት ሰነፎች የእስራኤል ልጆች፥ ኤርምያስን መስያችሁ በድንጋይ ስለ ምን ትደበድቡኛላችሁ? ኤርምያስስ እነሆ በመካከላችሁ ቁሟል” ብሎ ጮኸ። 61 ኤርምያስንም ባዩት ጊዜ ብዙ ድንጋይ ይዘው ወደ እርሱ ሮጡ፤ እርሱም ምስክርነቱን ጨረሰ፤ ባሮክና አቤሜሌክም መጥተው ቀበሩት፤ ያንም ድንጋይ አምጥተው በመቃብሩ አፍ እንደ መዝጊያ አድርገው አኖሩት። 62 “የኤርምያስ ረዳቱ እነሆ፥ ይህ ድንጋይ ነው” ብለው በውስጡ ጻፉ፤ የኤርምያስም የቀረች ነገሩ እነሆ፥ በባሮክ መጽሐፍ ተጽፋለች። |