ኤርምያስ 10:10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን እውነተኛ አምላክ ነህ፤ አንተ ሕያው አምላክ፥ ዘለዓለማዊ ንጉሥ ነህ፤ አንተ በምትቈጣበት ጊዜ ዓለም ይናወጣል፤ የአሕዛብ መንግሥታትም የአንተን ቊጣ ችለው አይቆሙም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው፤ በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቁጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን መቋቋም አይችሉም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፥ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፥ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፥ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። |
አንተ ታላቅና ኀያል ነህ፤ በክብር፥ በውበትና በግርማም የተሞላህ ነህ፤ በሰማይና በምድር ያለው ነገር ሁሉ የአንተ ነው፤ አንተ ከሁሉ በላይ ከፍ ያልክና በሁሉም ላይ ሥልጣን ያለህ ንጉሥ ነህ፤
ግዛትህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። መንግሥትህም ዘለዓለማዊ ነው። እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ የታመነ ነው፤ እርሱ የሚያደርገው ሁሉ መልካም ነው።
የአሦር ንጉሥ ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባለሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢውን ይቀጣ ይሆናል፤ ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ስለሚተርፉት እባክህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።”
በእግዚአብሔር ፊት ሕዝቦች እንደ አንድ የውሃ ጠብታ ናቸው፤ በሚዛንም ላይ እንዳለ ዐቧራ ናቸው፤ ደሴቶችም በእርሱ ዘንድ እንደ ትቢያ የቀለሉ ናቸው።
ከቶ አታውቅምን? ከቶስ አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘለዓለም አምላክ ነው፤ ዓለምን ሁሉ የፈጠረ እርሱ ነው፤ እርሱ ከቶ አይደክምም ወይም አይታክትም፤ ሐሳቡን መርምሮ ሊደርስበት የሚቻለው የለም።
ከፍተኛውና ከሁሉ የላቀው፥ ለዘለዓለም የሚኖር ቅዱሱ እንዲህ ይላል፦ “እኔ በተቀደሰና በከፍተኛ ቦታ፥ እንዲሁም ልባቸው ከተሰበረና መንፈሳቸው ትሑት ከሆኑት ጋር እኖራለሁ፤ ይኸውም ትሑት መንፈሳቸውንና የተሰበረ ልባቸውን ለማደስ ነው።
የቀድሞው ችግር ስለ ተረሳና ከዐይኔ ስለ ተሰወረ በሀገሪቱ በረከትን የሚለምን በእኔ በታማኙ እግዚአብሔር ስም ይለምናል፤ በሀገሪቱም የሚምሉ በእኔ በታማኙ እግዚአብሔር ስም ይምላሉ።”
የእግዚአብሔር ሸክም ብላችሁ ከቶ አትናገሩ፤ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት ሸክም ሊሆን ይችላል? እናንተ ግን የሠራዊት ጌታ የሕያው እግዚአብሔርን ቃል ታጣምማላችሁ።
ባቢሎንን ማንም የማይኖርባት ምድረ በዳ እንድትሆን ለማድረግ እግዚአብሔር ያቀደውን የሚፈጽምበት ጊዜ ከመሆኑ የተነሣ፥ ምድር በመናወጥ ትንቀጠቀጣለች።
“እግዚአብሔር የሚያሳየው ተአምር እንዴት ታላቅ ነው! እርሱ የሚፈጽመው ድንቅ ሥራ እንዴት ብርቱ ነው! እግዚአብሔር ለዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።
ንጉሡ ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፦ “ሰባቱ ዓመቶች ካለፉ በኋላ ቀና ብዬ ወደ ሰማይ ተመለከትኩ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገንኩ፤ ለዘለዓለማዊው አምላክ ክብርና ውዳሴ አቀረብኩ፤ “ግዛቱ ዘለዓለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤
በመንግሥቴ የሚኖር ሕዝብ ሁሉ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር በዐዋጅ አዝዤአለሁ፤ “እርሱ ሕያውና ዘለዓለማዊ አምላክ ነው፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤
በልዩ ልዩ አገር የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ያገለግሉት ዘንድ ሥልጣን፥ ክብርና ንጉሥነት ተሰጠው፤ ግዛቱም የማይጠፋ ዘለዓለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።
እግዚአብሔር እንደ ነጐድጓድ ያለ ድምፁን በሠራዊቱ ላይ ያሰማል፤ ሠራዊቱ ምንኛ ብዙ ነው! ትእዛዙን የሚቀበሉ ከቊጥር በላይ ናቸው፤ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቀን ታላቅ ነው፤ በጣም አስፈሪ ስለ ሆነ በዚያ ቀን ማን ችሎ ይቆማል?
በዚያን ጊዜ ሰም በእሳት እንደሚቀልጥና፥ ውሃም ከከፍተኛ ቦታ ወደ ታች እንደሚወርድ እንዲሁም ተራራዎች ከእርሱ ሥር ይቀልጣሉ፤ ሸለቆዎችም ይከፈታሉ።
በእግዚአብሔር ፊት ተራራዎች ይንቀጠቀጣሉ፤ ኰረብቶችም ይቀልጣሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት ምድር ትናወጣለች፤ ዓለምና በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ።
በእርሱ ኀይለኛ ቊጣ ፊት መቆም የሚችል ማን ነው? ቊጣውስ እንደ እሳት በነደደ ጊዜ የሚችለው ማነው? እንደ እሳት የሚያቃጥል ቊጣው በሚወርድበት ጊዜ አለቶች ተሰነጣጥቀው ይበታተናሉ።
ተራራዎች አንተን አይተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ የዝናብም ጐርፍ ምድርን እየጠራረገ አለፈ፤ ውቅያኖስ ከፍተኛ ድምፅ አሰማ፤ ማዕበሉም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለ።
እርሱ ሲቆም ምድር ትናወጣለች፤ እርሱ ሲመለከታቸው ሕዝቦች ይንቀጠቀጣሉ፤ የጥንቱ ተራራዎች ይናዳሉ፤ ከጥንት ጀምሮ የእርሱ መረማመጃ የነበሩት ኰረብቶች ወደ ታች ይሰጥማሉ።
ነገር ግን እርሱ እንደ ብረት ማቅለጫ እሳትና እንደ ልብስ ማጠቢያ ሳሙና ስለ ሆነ በእርሱ የመምጫ ቀን ጸንቶ መቆም የሚችልና እርሱስ ሲገለጥ በፊቱ መቆም የሚችል ማነው?
ኢየሱስ ግን ዝም አለ። የካህናት አለቃውም እንደገና ኢየሱስን “በሕያው እግዚአብሔር ስም ይዤሃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ መሲሕ እንደ ሆንክ ንገረን!” አለው።
“እናንተ ሰዎች ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እንደ እናንተ ሰዎች ነን፤ እኛ እዚህ የመጣነው እናንተ ከዚህ ከከንቱ ነገር ሁሉ ርቃችሁ ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርንና በውስጣቸው የሚገኙትን ሁሉ ወደ ፈጠረው ወደ ሕያው አምላክ እንድትመለሱ መልካም ዜና ልናበሥርላችሁ ነው፤
“እርሱ ምሽጋችን ነው፤ ሥራዎቹም ፍጹሞች ናቸው፤ መንገዶቹም ሁሉ የቀኑ ናቸው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፥ እርሱም ቀጥተኛና እውነተኛ ነው።
ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ እንዴት እንደ ተቀበላችሁን ሕያውና እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖቶች ተለይታችሁ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለሳችሁ እነዚያ ሰዎች ራሳቸው ይመሰክራሉ።
የዚህ ዓለም ሀብታሞች እንዳይታበዩ ወይም ተስፋቸውን አስተማማኝ ባልሆነ ሀብት ላይ እንዳያደርጉ እዘዛቸው፤ እንዲሁም ተስፋቸው እኛን ደስ እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን እዘዛቸው።
ኢያሱም ንግግሩን በመቀጠል፦ “ሕያው እግዚአብሔር በመካከላችሁ መሆኑን የምታውቁት እናንተ ወደ ፊት እየገፋችሁ በሄዳችሁ መጠን እርሱ ከነዓናውያንን፥ ሒታውያንን፥ ሒዋውያንን፥ ፈሪዛውያንን፥ ጌርጌሳውያንን፥ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊታችሁ የሚያስወጣ በመሆኑ ነው።
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣና እውነተኛውን አምላክ እንድናውቅ አስተዋይ ልቡና እንደ ሰጠን እናውቃለን በልጁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእርሱ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ኅብረት አለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።
እግዚአብሔር ሆይ! ከኤዶም ተራራ በተነሣህ ጊዜ፥ በኤዶምም ምድር ላይ በተራመድህ ጊዜ ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ሰማያት ዝናብን አዘነቡ፤ አዎ! ውሃ ከደመናዎች ወደታች ጐረፈ።
ዳዊትም በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እስራኤልን ከዚህ አሳፋሪ ውርደት ለሚያድን ሰው ምን ይደረግለታል? ኧረ ለመሆኑ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት የሚፈታተን ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።
እኔ ያንተ አሽከር አንበሳና ድብ ገድያለሁ፤ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ስለ ተፈታተነ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል።