Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 74 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ ሕዝብ ሰላም የሚቀርብ ጸሎት

1 አምላክ ሆይ! እንደዚህ ለምን ተውከን? ሕዝብህንስ የምትቈጣው ለዘለዓለም ነውን?

2 ከጥንት ጀምሮ የመረጥከውን፥ የራስህ ወገን እንዲሆን ከባርነት የዋጀኸውን ሕዝብህን አስታውስ፤ ከዚህ በፊት መኖሪያህ ያደረግኸውን የጽዮንን ተራራ አስብ።

3 በጠላቶቻችን ለዘለቄታ የፈራረሰውን ቤተ መቅደሱን ተዘዋውረህ ተመልከትልን።

4 ጠላቶችህ “ድል አደረግን” ብለው በቤተ መቅደስህ ውስጥ ይደነፋሉ፤ በዚያም የድል ምልክት የሆነውን ዐርማቸውን ተክለዋል።

5 እነርሱ እንጨቶችን በመጥረቢያ እንደሚቈርጡ የደን እንጨት ቈራጮችን ይመስላሉ።

6 የግድግዳዎችዋን ጌጣ ጌጦች በመጥረቢያና በመዶሻ ሰባበሩ።

7 መቅደስህን አፍርሰው በእሳት አቃጠሉት፤ ስምህ የሚጠራበትን ቦታ በመሬት ላይ ጥለው አረከሱት።

8 እነርሱም “ኑ በሥልጣናችን ሥር እናድርጋቸው” አሉ። በሀገሪቱ ያሉትን የተቀደሱ ቦታዎችን ሁሉ አቃጠሉ።

9 ከእንግዲህ ወዲህ ተአምራት አይኖሩም፤ ነቢያትም አይኖሩም፤ ይህ ሁኔታ እስከ መቼ እንደሚቈይ ከእኛ መካከል ማን ያውቃል?

10 አምላክ ሆይ! ጠላቶች በአንተ ላይ የሚሳለቁት እስከ መቼ ነው? ስምህንስ የሚዳፈሩት ያለማቋረጥ ነውን?

11 ለምን አትቀጣቸውም? ለምንስ ዝም ብለህ ትተዋቸዋለህ?

12 አምላክ ሆይ! ከጥንት ጀምሮ ንጉሣችን አንተ ነህ፤ በምድርም ላይ ደኅንነትን አመጣህ፤

13 በታላቁ ኀይልህ ባሕሩን ከፈልክ፤ በባሕር የሚኖሩትን የታላላቅ አውሬዎች ራስ ቀጠቀጥክ፤

14 ሌዋታን የተባለውን የባሕር ዘንዶ ራስ ቀጠቀጥህ፤ ሥጋውንም በበረሓ ለሚኖሩ ፍጥረቶች ምግብ አድርገህ ሰጠሃቸው።

15 ምንጮችና ጅረቶች እንዲፈስሱ አደረግህ፤ ታላላቅ ወንዞችን ግን አደረቅህ።

16 ቀኑንና ሌሊቱን የፈጠርክ፥ ፀሐይንና ጨረቃን በየቦታቸው ያጸናህ አንተ ነህ፤

17 አንተ ለምድር ዳርቻን ወሰንህ፤ ክረምትና በጋ እንዲፈራረቁ አደረግህ።

18 እግዚአብሔር ሆይ፥ ጠላቶችህ በአንተ ላይ እንደሚሳለቁ ተመልከት፤ እነርሱ ሞኞች ስለ ሆኑ ስምህን ይዳፈራሉ።

19 አንተን የሚያምኑትን ነፍሶች ለአራዊት አሳልፈህ አትስጥ፤ የአገልጋዮችህንም ሥቃይ ለዘለዓለም አትርሳ!

20 ከእኛ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን አስብ፤ ጨለማ በሆነው ምድር ማእዘን ሁሉ ዐመፅ አለ።

21 ጭቈና የደረሰባቸው ሰዎች ዐፍረው ወደ ኋላ እንዲመለሱ አታድርግ፤ ድኾችና ምስኪኖች ስምህን እንዲያመሰግኑ ይሁን።

22 አምላክ ሆይ! ተነሥ! ስምህን የሚዳፈሩትን ተከላከል! እነዚህ ሞኞች ቀኑን ሙሉ በአንተ ላይ እንደሚሳለቁ ተመልከት።

23 ጠላቶችህ ዘወትር የሚጮኹትን ጩኸትና የሚደነፉትን ድንፋታ አስታውስ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos