ኤርምያስ 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምባዕድ አምልኮና እውነተኛ አምልኮ 1 የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር የሚነግራችሁን ቃል ስሙ፤ 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የአሕዛብን አካሄድ አትከተሉ፤ መቼም አሕዛብ ያልተለመደ አዲስ ነገር በሰማይ ባዩ ጊዜ በፍርሃት መንቀጥቀጥ ልማዳቸው ነው፤ እናንተ ግን በዚህ አትሸበሩ። 3 የአሕዛብ ልማዳዊ እምነት ከንቱ ነው፤ ዛፍ ከደን ይቈረጣል፤ አናጢ በመሮ ቅርጽ ያወጣለታል፤ 4 በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፤ እንዳይወድቅም በምስማር ያጠብቁታል። 5 እንደነዚህ ያሉት ምስሎች በዱባ ተክል ውስጥ ለወፍ ማስፈራሪያ እንደሚተከሉ ነገሮች ናቸው፤ መናገር አይችሉም፤ መራመድ ስለማይችሉ ሰዎች ይሸከሙአቸዋል፤ ጒዳት ማድረስም ሆነ ጥቅም ማስገኘት ስለማይችሉ፥ ፈጽሞ አትፍሩአቸው።” 6 እግዚአብሔር ሆይ! አንተን የሚመስል ማንም የለም፤ አንተ ኀያል ነህ፤ ስምህም ታላቅና አስፈሪ ነው። 7 የመንግሥታት ሁሉ ንጉሥ ስለ ሆንክ አንተን የማይፈራ ማን ነው? በአሕዛብ ጠቢባንም ሆነ በንጉሦቻቸው መካከል አንተን የሚመስል ስለሌለ ክብር ይገባሃል። 8 ሁሉም ሞኞችና አላዋቂዎች ሆነው ነው እንጂ ከእንጨት ከተሠሩ ምስሎች ከቶ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? 9 ምስሎቻቸው ከተርሴስ በመጣ ጥሬ ብርና ከኡፋዝ በተገኘ ወርቅ ተለብጠዋል፤ በብልኀተኞችም ሥራ አጊጠዋል፤ ጥበበኞች ሸማኔዎች በሠሩአቸውም የወይን ጠጅና ሐምራዊ ልብስ ተሸፍነዋል። 10 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን እውነተኛ አምላክ ነህ፤ አንተ ሕያው አምላክ፥ ዘለዓለማዊ ንጉሥ ነህ፤ አንተ በምትቈጣበት ጊዜ ዓለም ይናወጣል፤ የአሕዛብ መንግሥታትም የአንተን ቊጣ ችለው አይቆሙም። 11 “ጣዖቶች ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ መሆናቸውንና አንተ እግዚአብሔር ጣዖቶችን ሁሉ እንደምትደመስስ ንገራቸው” አልከኝ። ለእግዚአብሔር የቀረበ ምስጋና 12 እግዚአብሔር በኀይሉ ምድርን ሠራ፤ በጥበቡም ዓለምን ፈጠረ፤ በማስተዋሉም ሰማያትን ዘረጋ፤ 13 በእርሱ ትእዛዝ ከሰማይ በላይ ያሉ ውሃዎች የመናወጥ ድምፅ ያሰማሉ፤ እርሱ ደመናዎችን ከምድር ዳርቻ ያመጣል፤ በዝናብ ጊዜም መብረቅ እንዲበርቅ ያደርጋል፤ ነፋስንም ከማከማቻው ይልካል። 14 ሁሉም ሞኞችና አላዋቂዎች ሆኑ፤ የሠሩአቸው ምስሎች ሐሰተኞች ስለ ሆኑና ሕይወትም ስለሌላቸው አንጥረኛው በሠራቸው ጣዖቶች አፍሮባቸዋል። 15 እነዚህ አማልክት ዋጋ ቢሶችና የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤ እግዚአብሔር እነርሱን ለመቅጣት በሚገለጥበትም ጊዜ ይደመሰሳሉ። 16 የያዕቆብ አምላክ ግን እንደ እነርሱ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው። እስራኤልንም የራሱ ሕዝብ እንዲሆን መርጦታል፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ሊመጣ የተቃረበ ስደት 17 እናንተ በተከበበችው በኢየሩሳሌም ከተማ የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ! ከዚያ ለመውጣት ንብረታችሁን በፍጥነት ሰብስቡ! 18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚህ ጊዜ በዚህች አገር የሚኖሩትን ሰዎች አስወጣለሁ፤ እነርሱን አስጨንቄ እንዲማረኩ አደርጋለሁ።” 19 የኢየሩሳሌም ሕዝብ እየጮሁ እንዲህ ይላሉ፥ “በብርቱ ስለ ቈሰልን ወዮልን! ቊስላችንም የማይፈወስ ነው፤ እኛ ግን ይህን ሁሉ መከራ መታገሥ የምንችል መስሎን ነበር። 20 ድንኳኖቻችን ፈራረሱ፤ መወጠሪያ ገመዶችም ተቈራረጡ፤ ልጆቻችን በሙሉ ተሰደው ስለ ሄዱ፥ ድንኳኖቻችንን መልሶ የሚተክልልንና መጋረጃዎቻችንን የሚሰቅልልን አንድ እንኳ አልቀረም።” 21 እኔም እንዲህ ስል መለስኩ፥ “መሪዎቻችን ሞኞች ከመሆናቸው የተነሣ፥ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልጠየቁም፤ ውድቀት የደረሰባቸውና ሕዝባችንም ተበትኖ የቀረው ስለዚህ ነው። 22 አድምጡ አዲስ ዜና መጥቶአል! የሰሜን መንግሥት የይሁዳን ከተሞች ወደ ምድረበዳነት ለውጦ የቀበሮዎች መመሰጊያ ለማድረግ በመራወጥ ላይ ይገኛል።” 23 እግዚአብሔር ሆይ! ሰው በራሱ ሕይወት እንደማያዝበትና አካሄዱንም በራሱ ሥልጣን መቈጣጠር እንደማይችል ዐውቃለሁ። 24 እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ትክክለኛ ፈራጅ እንደ መሆንህ ገሥጸን፤ ነገር ግን ፈጽመን እንዳንጠፋ በምትቈጣበት ጊዜ አይሁን። 25 ቊጣህን አንተን በማያውቁና ስምህን በማይጠሩ ሕዝቦች ላይ አፍስሰው፤ እነርሱ ሕዝብህን ፈጅተዋል፤ ሁላችንንም ፈጽመው በመደምሰስ፥ አገራችንን አውድመዋል። |