ዮሐንስ 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሱስ ጸሎት 1 ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ እያየ እንዲህ አለ፦ “አባት ሆይ! እነሆ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ እንዲያከብርህ ልጅህን አክብረው፤ 2 የምታከብረውም ለሰጠኸው ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲሰጥ በሰዎች ሁሉ ላይ ሥልጣን ስለ ሰጠኸው ነው። 3 የዘለዓለም ሕይወትም አንተ ብቻ እውነተኛውን አምላክና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው። 4 እኔ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ። 5 አባት ሆይ! ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር አሁንም በአንተ ዘንድ አክብረኝ። 6 “ከዓለም ውስጥ መርጠህ ለሰጠኸኝ ሰዎች የአንተን ማንነት ገለጥኩላቸው፤ እነርሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተ እነርሱን ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል፤ 7 የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ እነርሱ አሁን ዐውቀዋል። 8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤ እነርሱም ተቀብለውታል፤ ከአንተ ዘንድ መጥቼ መምጣቴንም በእውነት ዐውቀዋል፤ አንተ እንደ ላክኸኝም አምነዋል። 9 “እኔ የምጸልየው ለእነርሱ ነው፤ እነዚህ የሰጠኸኝ የአንተ ስለ ሆኑ ለእነርሱ እጸልያለሁ፤ ለዓለም አልጸልይም። 10 የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው የአንተም የሆነው የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ እከብራለሁ። 11 እኔ ከእንግዲህ ወዲህ በዓለም ላይ አልኖርም፤ እነርሱ ግን በዓለም ናቸው። እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህ የሰጠኸኝ እንደእኛ አንድ እንዲሆኑ ለእኔ በሰጠኸኝ ስምህ ጠብቃቸው። ይላሉ” 12 እኔ አብሬአቸው በነበርኩ ጊዜ በሰጠኸኝ ስምህ ጠብቄአቸዋለሁ፤ እኔ ጠበቅኋቸው፤ ስለዚህ የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከዚያ ከጥፋት ልጅ በቀር ከቶ ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። 13 አሁን እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ በዓለም ላይ ሳለሁ ይህን የምናገረው ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ ፍጹም እንዲሆን ነው። 14 እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉም፤ ስለዚህ ዓለም ጠላቸው። 15 ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም ውጪ እንድትወስዳቸው አለምንም። 16 እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። 17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። 18 አንተ እኔን ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም እነርሱን ወደ ዓለም ላክኋቸው። 19 እነርሱ በእውነት ቅዱሳን እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ ቅዱስ አደርጋለሁ። 20 “በእነርሱ ቃል አማካይነት በእኔ ስለሚያምኑትም እለምናለሁ እንጂ ለእነርሱ ብቻ አለምንም። 21 እኔም የምለምነው ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም አባት ሆይ! አንተ በእኔ እንዳለህ፥ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱም በእኛ እንዲኖሩ ነው፤ አንተ እንደ ላክኸኝም ዓለም እንዲያምን ነው። 22 እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ ለእኔ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። 23 እኔ የምለምነው እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ እንደ ሆንክ እነርሱም በፍጹም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም እኔን እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድከኝ መጠን እነርሱንም እንደ ወደድካቸው ዓለም እንዲያውቅ ነው። 24 “አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እነዚህ አንተ የሰጠኸኝም እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋር እንዲኖሩ እወዳለሁ። 25 ጻድቅ አባት ሆይ! ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን ዐውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ ዐውቀዋል። 26 አንተ እኔን የወደድክበት ፍቅር በእነርሱ ላይ እንዲሆንና እኔም በእነርሱ እንድሆን እነርሱ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ ደግሞም እንዲያውቁ አደርጋቸዋለሁ።” |