ሚልክያስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ በፊቴ መንገድን ያዘጋጅ ዘንድ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ የምትፈልጉት ጌታም በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ በእርሱ የምትደሰቱበት የቃል ኪዳን መልእክተኛም በእርግጥ ይመጣል።” 2 ነገር ግን እርሱ እንደ ብረት ማቅለጫ እሳትና እንደ ልብስ ማጠቢያ ሳሙና ስለ ሆነ በእርሱ የመምጫ ቀን ጸንቶ መቆም የሚችልና እርሱስ ሲገለጥ በፊቱ መቆም የሚችል ማነው? 3 እርሱ እንደ ብረት አቅላጭና እንደ ብር አንጥረኛ ፍርድን ለማጣራት ይቀመጣል፤ የሌዊንም ልጆች የጽድቅ መሥዋዕት ለማቅረብ እስከሚችሉ ድረስ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል። 4 የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ የሚያቀርቡት መሥዋዕት እንደ ቀድሞ ዘመንና እንዳለፉት ዓመቶች እግዚአብሔርን የሚያስደስት ይሆናል። 5 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በአስማተኞች፥ በዘማውያን፥ በሐሰት መስካሪዎች፥ የቀን ሠራተኞችን ደመወዝ አታለው በሚያስቀሩ አሠሪዎች፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፥ እናትና አባት የሌላቸው ልጆችንና ስደተኞችን በሚጨቊኑና እኔን በማይፈሩ ሰዎች ላይ ፈጣን ፍርዴን አስተላልፋለሁ። ዐሥራት የመክፈል ግዴታ 6 “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ገና ፈጽማችሁ አልጠፋችሁም። 7 ከቀድሞ አባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሕጌ ርቃችኋል፤ አልጠበቃችሁትምም። ‘ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ’፥ እናንተ ግን ‘ወደ አንተ የምንመለሰው በምን ዐይነት ነው?’ ትላላችሁ። 8 ሰው የእግዚአብሔርን ሀብት ይዘርፋልን? ሆኖም እናንተ እኔን ዘርፋችኋል፥ እናንተ ግን እንዴት ከአንተ እንዘርፋለን ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ ከእኔ የዘረፋችሁት ዐሥራትንና መባን ባለመክፈላችሁ ነው። 9 እናንተ፥ ሕዝቡም ሁሉ ከእኔ ስለምትዘርፉ የተረገማችሁ ሆናችኋል። 10 በቤተ መቅደሴ ሲሳይ ይበዛ ዘንድ ዐሥራቴን በሙሉ ወደ ጐተራ አግቡ፤ እናንተ ይህን ብታደርጉ እኔ ደግሞ የሰማይን መስኮቶች ከፍቼ መልካም የሆነውን በረከት ሁሉ አብዝቼ ባልሰጣችሁ በዚህ ልትፈትኑኝ ትችላላችሁ። 11 እህላችሁን ተባይ እንዳያጠፋው እከለክላለሁ፤ የወይናችሁ ተክል ፍሬ አልባ አይሆንም፤ 12 ከዚህ በኋላ ሕዝቦች ሁሉ እናንተን የተባረከ ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል፤” ይህን የተናገርኩ እኔ የሠራዊት አምላክ ነኝ። እግዚአብሔር ምሕረት እንደሚያደርግ የሰጠው ተስፋ 13 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በእኔ ላይ የድፍረት ቃል ትናገራላችሁ፤ እንደገና ደግሞ ‘እኛ በአንተ ላይ ምን ክፉ ነገር ተናገርን?’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ 14 እናንተ ‘እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዞቹን መጠበቅና እንደ ሐዘንተኞች በሠራዊት አምላክ ፊት መመላለስ ምን ይጠቅመናል? 15 እንደምናየው ከሆነ እነሆ፥ ክፉ አድራጊዎች ዕድለኞች ናቸው፤ በእርግጥም እነርሱ በብልጽግና ይኖራሉ፤ እግዚአብሔርን እንኳ እየተፈታተኑት ምንም ችግር አይደርስባቸውም እያላችሁ ትናገራላችሁ።’ ” 16 ከዚያ በኋላ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም በጥሞና አዳመጣቸው፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩና ስሙንም የሚያከብሩ ሰዎች ለተግባራቸው መታሰቢያ በመጽሐፍ ተጻፈ። 17 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ የእኔ ይሆናሉ፤ እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ የግሌ ይሆናሉ፤ ወላጆች ለሚያገለግሉአቸው ልጆች ምሕረት እንደሚያደርጉላቸው እኔም ለእነርሱ ምሕረት አደርግላቸዋለሁ። 18 በዚያን ጊዜ በጻድቅና በኃጢአተኛ ለእግዚአብሔር በሚታዘዝና በማይታዘዝ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት እንደገና ታያላችሁ።” |