Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ኤርምያስ 50 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ ባቢሎን መያዝ የተነገረ ትንቢት

1 ስለ ባቢሎንና ስለ ሕዝብዋ እግዚአብሔር በነቢዩ በኤርምያስ አማካይነት የተናገረው ቃል ይህ ነው፦

2 “ለአሕዛብ ሁሉ በማወጅ ወሬውን ንገሩ! አርማ አንሥታችሁ ዜናውን አስታውቁ! ከቶ ምሥጢር አድርጋችሁ አታስቀሩ! እነሆ ባቢሎን ተያዘች፤ ቤል የተባለው ጣዖት እንዲያፍር ተደረገ፤ ‘ማርዱክ’ የተባለ ጣዖቷም ተሰባብሮአል፤ የባቢሎን ጣዖቶች አፍረዋል፤ አጸያፊ ምስሎችዋም ተሰባብረዋል።

3 በባቢሎን ላይ አደጋ ጥሎ ምድረ በዳ የሚያደርጋት ሕዝብ ከሰሜን በኩል ተነሥቶባታል፤ ሰውም እንስሳውም ጥሎአት ይሸሻል፤ የሚኖርባትም የለም።”


የእስራኤል መመለስ

4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዘመኑና ጊዜው ሲደርስ የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ በአንድነት ሆነው እኔን አምላካቸውን ፍለጋ እያለቀሱ ይመጣሉ፤

5 ወደ ጽዮን የሚያደርሰውን መንገድ ይጠይቃሉ፤ አቅጣጫውንም ተከትለው ይጓዛሉ፤ ከእኔም ጋር ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤ ከቶም አያፈርሱትም።

6 “ሕዝቤ እንደ ጠፉ በጎች ሆነዋል፤ ጠባቂዎቻቸውም አሳቱአቸው፤ በተራራ ላይ ባዝነው እንዲቀሩም አደረጉአቸው፤ ከተራራ ወደ ኰረብታ እንደሚባዝኑ በጎች ተንከራተቱ፤ ማደሪያቸውንም ረሱ።

7 በጎች የአውሬ ሰለባ እንደሚሆኑ እነርሱንም ያገኛቸው ሁሉ አደጋ ጣለባቸው፤ ጠላቶቻቸውም ‘እኛ እኮ ምንም አልበደልንም፤ ይህ ሁሉ ጥፋት በእነርሱ ላይ የደረሰባቸው የቀድሞ አባቶቻቸው ተስፋ አድርገውበት በኖሩት አምላክ ላይ በማመፃቸው ምክንያት ነው፤ እነርሱም እንደ አባቶቻቸው ለእርሱ ታማኞች ሆነው መኖር ይገባቸው ነበርና ነው።’

8 “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ከባቢሎን ሸሽታችሁ ውጡ! አገሪቱን ለቃችሁ ሂዱ! መንጋውን እንደሚመራ የፍየል አውራ ሁኑ!

9 እኔ ከወደ ሰሜን የተባበሩ ሕዝቦች በባቢሎን ላይ እንዲዘምቱ አነሣሣለሁ፤ በእርስዋም ላይ አደጋ ይጥሉባታል፤ ከዚያም ትያዛለች፤ የእነርሱም ቀስቶች ተወርውረው ዒላማቸውን እንደማይስቱ እንደ ሠለጠኑ ወታደሮች ቀስቶች ናቸው።

10 ባቢሎን ትመዘበራለች፤ በዝባዥዎችዋም እስከሚበቃቸው ድረስ ያገኙትን ሁሉ ይወስዳሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”


የባቢሎን አወዳደቅ

11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎን ሕዝብ ሆይ! ሕዝቤን፥ በመበዝበዛችሁ ደስታና ሐሴት በማድረግ ፈንጥዛችሁ ነበር፤ በመስክ ላይ እንደምትፈነጭ ጊደር ተቀናጥታችሁ፥ እንደ ሰንጋ ፈረሶችም አሽካክታችሁ ነበር፤

12 አሁን ግን ታላቂቱ ከተማችሁ በጣም ታፍራለች፤ እናት አገራችሁም ትዋረዳለች፤ ከመንግሥታት ሁሉ ያነሰች ትሆናለች። ውሃ የማይገኝባት ሆና ወደ ምድረ በዳነት ትለወጣለች።

13 ከቊጣዬ የተነሣ በባቢሎን መኖር የሚችል የለም፤ ፈራርሳ ትቀራለች፤ በአጠገብዋ የሚያልፍ ሁሉ ይደነቃል፤ ይደነግጣልም።

14 “እናንተ ቀስተኞች ባቢሎንን ለመውጋት ዙሪያዋን ክበቡ፤ በእኔ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት ስለ ሠራች ፍላጾቻችሁንም ሁሉ በባቢሎን ላይ ወርውሩ፤ ለፍላጾቻችሁ አትሳሱ።

15 በከተማይቱ ዙሪያ በማቅራራት ደንፉ! እነሆ ባቢሎን እጅዋን ሰጥታለች፤ ግንቦችዋ ተጥሰዋል፤ ቅጽሮችዋም ፈራርሰዋል፤ ባቢሎናውያንን እበቀላለሁ፤ እናንተም ተበቀሉአቸው፤ በሌሎች ላይ የፈጸሙትን ጭካኔ በእነርሱም ላይ ፈጽሙባቸው፤

16 ዘሪውንና መከር ሰብሳቢውን ከባቢሎን አስወግዱ፤ በዚያች አገር የሚኖር እያንዳንዱ የውጪ ዜጋ አደጋ የሚጥልባትን ሠራዊት በመፍራት ወደ ወገኑ ይመለሳል፤ ወደ አገሩም ይሸሻል።”


የእስራኤል መመለስ

17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል ሕዝብ አንበሳ እያባረረ እንደሚበትናቸው በጎች ሆነዋል፤ በመጀመሪያ አውሬ ያደነውን ሁሉ ቦጫጭቆ እንደሚበላ የአሦር ንጉሥ እነርሱን ፈጃቸው፤ ከዚያም በኋላ አንበሳ አጥንትን እንደሚቈረጣጥም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አደቀቃቸው።

18 ስለዚህ እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት እንደቀጣሁ፥ ናቡከደነፆርንና አገሩን ጭምር እቀጣለሁ።

19 የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ምድራቸው እመልሳለሁ፤ በቀርሜሎስ ተራራና በባሳን አውራጃ የሚበቅለውን ሁሉ ይመገባሉ፤ በኤፍሬምና በገለዓድ ከሚበቅለውም እህል የፈለጉትን ያኽል ይመገባሉ፤

20 በዚያን ጊዜ እኔ ከእስራኤልና ከይሁዳ መንግሥታት እንዲተርፉ ያደረግኋቸውን ሰዎች ይቅር ስለምል ኃጢአትና በደል ተፈልጎ አይገኝባቸውም።”


የእግዚአብሔር ፍርድ በባቢሎን ላይ

21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በምራታይምና በፈቆድ ሕዝብ ላይ አደጋ ጣሉ፤ ግደሉ፤ አጥፉአቸውም፤ እኔ የማዛችሁን ሁሉ አድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

22 በምድሪቱም የጦርነት ድምፅ ተሰምቶአል፤ ታላቅ ጥፋትም ደርሷል።

23 የዓለምን ሕዝብ እንደ መዶሻ ታደቅ የነበረችው ባቢሎን እርስዋ ራስዋ ደቃለች፤ በዚያች አገር ላይ የደረሰው በሕዝቦች ዘንድ ምንኛ አስደንጋጭ ነው?

24 ባቢሎን ሆይ! በራስሽ ላይ ባጠመድሽው ወጥመድ ሳታውቂው ተያዝሽበት፤ ተይዘሽ የተጋለጥሽውም እግዚአብሔርን ስለ ተዳፈርሽ ነው።

25 እግዚአብሔር የመሣሪያ ግምጃ ቤቱን ከፍቶ የቊጣ ጦር መሣሪያውን አወጣ፤ ይህንንም ያደረገው የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር በከለዳውያን ምድር የሚሠራው ሥራ ስላለው ነው።

26 ከየአቅጣጫው ዝመቱባት፤ እህልዋ የተከማቸበትን ጐተራ ሁሉ ክፈቱ፤ ምርኮውንም እንደ እህል ምርት ቈልሉት፤ ምንም ነገር ሳትተዉ አገሪቱን አጥፉ!

27 ወታደሮቻቸውን፥ ወደ ማረጃ ቦታ ወርደው እንደሚታረዱ የዕርድ ኰርማዎች ወስዳችሁ ግደሉ፤ የሚቀጡበት ጊዜ ስለ ደረሰ ለባቢሎን ሕዝብ ወዮላቸው!

28 “የባቢሎን ምርኮኞችና በባቢሎን የነበሩ ስደተኞች ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። አምላካችን እግዚአብሔር በባቢሎናውያን ላይ ስለሚበቀለው በቀል የሚናገሩትን አድምጡ።”

29 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ቀስት መደገን የሚችሉትን ቀስተኞች በባቢሎን ላይ ይዘምቱ ዘንድ ጥሩአቸው፤ ከተማይቱን ይክበቡ፤ ማንም እንዳያመልጥ ተጠባበቁ፤ የክፉ ሥራዋንም ዋጋ ክፈሉአት፤ በሌሎች ላይ የፈጸመችውንም ግፍ በእርስዋም ላይ ፈጽሙባት፤ እርስዋ በእስራኤል ቅዱስ በእኔ ላይ ተዳፍራለች፤

30 ስለዚህ ጐልማሶችዋ በከተማይቱ መንገዶች ይገደላሉ፤ ወታደሮችዋም ሁሉ በዚያው ጊዜ ይደመሰሳሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

31 “ትዕቢተኛይቱ ባቢሎን ሆይ! እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በአንቺ ላይ እነሣለሁ፤ አንቺንም የምቀጣበት ጊዜ ደርሶአል።

32 አንቺ ትዕቢተኛይቱ ተሰናክለሽ ትወድቂአለሽ፤ ደግፎ የሚያነሣሽም አይኖርም፤ ከተሞችሽን በእሳት አቃጥላለሁ፤ በዙሪያሽም ያለው ነገር ሁሉ ይደመሰሳል።”

33 የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ተጨቊነዋል፤ ማርከው የወሰዱአቸውም ሁሉ አጥብቀው ይዘዋቸዋል፤ ሊለቁአቸውም አልፈለጉም።

34 ነገር ግን ታዳጊያቸው ብርቱ ነው፤ ስሙም የሠራዊት አምላክ ነው፤ እርሱ ራሱ ይረዳቸዋል፤ ሰላምን በምድር ላይ ያወርድላቸዋል፤ በባቢሎን ሕዝብ ላይ ገና መከራን ያመጣባቸዋል።”

35 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በባቢሎን፥ በሕዝቦችዋ፥ በመሪዎችዋና በጥበበኞችዋ ላይ ሰይፍ ይመዘዝ!

36 ሟርተኞቻቸው ሞኞች ይሆኑ ዘንድ ወታደሮቻቸውም በፍርሃት ይርበደበዱ ዘንድ ሰይፍ በእነርሱ ላይ ይመዘዝ!።

37 በፈረሶቻቸው፥ በሠረገሎቻቸውና በቅጥር ወታደሮቻቸው ላይ ሰይፍ ይመዘዝ! እነርሱም እንደ ሴቶች ይሁኑ፤ በሀብታሞቹ ላይ ሰይፍ መዛችሁ ሀብታቸውን ሁሉ ዝረፉ!

38 ባቢሎን በአጸያፊና ሰውን በሚያሳብድ ጣዖት የተሞላች ስለ ሆነች ወንዞችዋ ሁሉ ይድረቁ።

39 “ስለዚህ የዱር አራዊት ከቀበሮችና ከሰጎኖች ጋር በባቢሎን ይኖራሉ፤ እንዲሁም እስከ መቼም ድረስ ከትውልድ እስከ ትውልድ የሰው መኖሪያ አትሆንም።

40 ሰዶምንና ገሞራን በአካባቢያቸው ካሉ ከተሞች ጋር በደመሰስኩ ጊዜ እንደሆነው እንዲሁም በባቢሎን ማንም እንደገና ሰፍሮ መኖር አይችልም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

41 እነሆ ሕዝብ ከሰሜን እየመጣ ነው፥ ኀያል ሕዝብና ብዙ ነገሥታት ከምድር ዳርቻ እየተንቀሳቀሱ

42 ቀስታቸውንና ሰይፋቸውን ይዘዋል፤ እነርሱ ምሕረት የሌላቸው ጨካኞች ናቸው፤ ፈረሶቻቸውን ሲጋልቡ፥ ድምፃቸው እንደሚተም ባሕር ነው፤ ባቢሎን ሆይ! እነርሱ በአንቺ ላይ አደጋ ለመጣል ለዘመቻ ተዘጋጅተው እንደሚመጡ ሰዎች ወደ አንቺ እየመጡ ነው።

43 የባቢሎን ንጉሥ ይህን ወሬ ሲሰማ እጁ ሽባ ሆኖ ተንጠልጥሎ ይቀራል፤ በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ይጨነቃል።

44 “በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ከሚገኘው ጥቅጥቅ ካለ ደን ወደ ለምለም መስክ እንደሚወጣ አንበሳ፥ እኔ እግዚአብሔር መጥቼ ባቢሎናውያን ድንገት ከከተማቸው ወጥተው እንዲባረሩ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እኔ የምመርጠውን እሾማለሁ፤ ታዲያ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ሊጠይቀኝ የሚደፍር ማነው? የሚቋቋመኝስ መሪ ማን ነው?

45 አሁን እንግዲህ እግዚአብሔር በባቢሎናውያን ላይ የመከረውን ምክርና በከለዳውያን ምድር ላይ ያቀደውን ዕቅድ ስሙ፤ ልጆቻቸው እንኳ እንደ በግ ግልገሎች ተጐትተው ይወሰዳሉ፤ በእነርሱም ምክንያት መሰማሪያቸው አስደንጋጭ ይሆናል።

46 የባቢሎን መያዝ ዜና ሲሰማ ምድር ትናወጣለች፤ ጩኸትዋም በሕዝቦች መካከል ይሰማል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos