Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘዳግም 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዐሥሩ ትእዛዞች
( ዘፀ. 20፥1-17 )

1 ሙሴም የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፥ ዛሬ የምነግራችሁን ሕግና ሥርዓት ሁሉ አድምጡ፤ በጥንቃቄም አጥንታችሁ እነዚህን ትእዛዞች ጠብቁ።

2 እግዚአብሔር አምላካችን በሲና ተራራ ላይ ቃል ኪዳን አደረገ፤

3 ቃል ኪዳን ያደረገውም ከአባቶቻችን ጋር ብቻ ሳይሆን፥ አሁን በሕይወት ካለነውም ከእኛ ሁሉ ጋር ነው።

4 እዚያም በተራራው ላይ በተቀጣጠለው እሳት ውስጥ ሆኖ ፊት ለፊት አነጋገራችሁ፤

5 እናንተ እሳቱን በመፍራት ወደ ተራራው መውጣት ስለ ፈራችሁ እኔ በዚያን ጊዜ እርሱ የሚለውን ሁሉ ልነግራችሁ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ቆምኩ፤ “እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤

6 ‘በባርነት ተገዢ ሆነህ ከኖርክበት ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤

7 “ ‘ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ።

8 “ ‘በሰማይ፥ ወይም በምድር፥ ወይም ከምድር በታች በውሃ ውስጥ ከሚገኙት ነገሮች የተቀረጹ ምስሎች ሠርተህ አታምልካቸው፤

9 እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፥ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን የሚያመልኩትን ሰዎች፥ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች፥ እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ የምበቀል ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆንኩ እነዚያን የተቀረጹ ምስሎች አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም።

10 ለሚወዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ዘለዓለማዊ ፍቅሬን አሳያቸዋለሁ።

11 “ ‘የእኔን የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ሰው እግዚአብሔር ሳይቀጣው አይቀርም።

12 “ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዝኩህ የሰንበትን ቀን ጠብቅ፤ ቀድሰውም፤

13 ሥራህን ሁሉ በስድስት ቀኖች ሠርተህ ታከናውናለህ፤

14 ሰባተኛው ቀን ግን ለእኔ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ቀን ነው፤ በዚያን ቀን ምንም ዐይነት ሥራ አትሥራ፤ አንተም ሆንክ ልጆችህ፥ አገልጋዮችህም ሆኑ እንስሶችህ በአገርህ ውስጥ የሚኖሩ መጻተኞችም ቢሆኑ ምንም ሥራ አትሥሩበት፤ አገልጋዮችህም ልክ እንደ አንተው ዕረፍት ያድርጉ።

15 በግብጽ ምድር ባሪያ የነበርክ መሆንህን አስታውስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በታላቅ ኀይልና በብርቱ ሥልጣን ከዚያ አወጣህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብር ዘንድ ያዘዘህ ስለዚህ ነው።

16 “ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ባዘዝኩህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር፤ ይህን ብታደርግ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ በምሰጥህ ምድር የረዥም ዘመን ዕድሜ ይኖርሃል።

17 “ ‘አትግደል፤

18 “ ‘አታመንዝር፤

19 “ ‘አትስረቅ፤

20 “ ‘በማንም ሰው ላይ በሐሰት አትመስክር፤

21 “ ‘የሌላውን ሰው ሚስቱን፥ ቤቱን፥ ርስቱን፥ አገልጋዮቹን፥ ከብቱን፥ አህዮቹንም ሆነ ማናቸውንም ንብረቱን ሁሉ አትመኝ።’

22 “በተሰበሰባችሁ ጊዜ እግዚአብሔር በተራራው ላይ ሆኖ ለእናንተ ለሁላችሁም የሰጣችሁ ትእዛዞች እነዚህ ናቸው፤ በእሳት፥ በደመናና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ብርቱ በሆነ ታላቅ ድምፅ በተናገረ ጊዜ የሰጣችሁ ትእዛዞች እነዚህ ብቻ ናቸው። እነርሱንም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ለእኔ ሰጠኝ።


የሕዝቡ ፍርሀት
( ዘፀ. 20፥18-21 )

23 “ተራራው በእሳት ይነድ በነበረበት ወቅት ከጨለማው ውስጥ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ የነገድ አለቆችና መሪዎች ሁሉ ወደ እኔ መጥታችሁ፥

24 እንዲህ አላችሁ፦ ‘በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር በሰማነው ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን ታላቅነቱንና ክብሩን በግልጥ አሳይቶናል፤ እግዚአብሔር ካነጋገረው በኋላ እንኳ ሰው በሕይወት መኖር እንደሚችል በዛሬው ዕለት አይተናል።

25 ነገር ግን ያ ብርቱ እሳት ያጠፋናል፤ ታዲያ ለምን መሞት እንፈልጋለን? እግዚአብሔር አምላካችን እንደገና ቢናገረን እንሞታለን።

26 ሕያው እግዚአብሔር በእሳት ውስጥ ሆኖ ከተናገረው በኋላ በሕይወት የኖረ ከሰው ዘር መካከል አንድ ሰው እንኳ ይገኛልን?

27 ስለዚህ ወደ እርሱ ቀርበህ እግዚአብሔር አምላካችን የሚለውን ሁሉ አዳምጥ፤ ተመልሰህም እርሱ ያለውን ሁሉ ንገረን፤ እኛም ሰምተን እንታዘዛለን።’

28 “እግዚአብሔርም፥ ይህን ስትሉኝ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለኝ፤ ‘እነዚህ ሰዎች ለአንተ የተናገሩትን ሁሉ ሰምቻለሁ፤ አባባላቸውም ትክክል ነው፤

29 ሁልጊዜ በዚህ ዐይነት ቢያስቡማ እንዴት መልካም ነበር! ሁልጊዜ ቢያከብሩኝና ትእዛዞቼንም ሁሉ ቢፈጽሙ ሁሉ ነገር ለእነርሱና ለዘሮቻቸው ለዘለዓለም በመልካም ሁኔታ በተከናወነላቸው ነበር።

30 አሁንም ሂድና ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ ንገራቸው።

31 አንተ ግን እዚህ እኔ አጠገብ ቁም፤ እኔም ሕግጋቴን፥ ትእዛዞቼንና ሥርዓቶቼን ሁሉ እሰጥሃለሁ፤ እኔ በምሰጣቸው ምድር እነዚህን ሕግጋቴን፥ ትእዛዞች ሥርዓቶቼን በመጠበቅ እንዲኖሩ ለሕዝቡ አስተምራቸው።’

32 “ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችሁ ያዘዛችሁን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ሁኑ፤ ከሕግጋቱም አንዱን እንኳ አትጣሱ፤

33 ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ እንዲከናወንላችሁ፥ በምትወርሱአትም ምድር ለረጅም ዘመናት እንድትኖሩ፥ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ሁሉ ፈጽሙ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos