መዝሙር 146 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለአዳኙ አምላክ የሚቀርብ ምስጋና 1 እግዚአብሔር ይመስገን! ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! 2 በሕይወቴ ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ። 3 ማዳን ስለማይችሉ በመሪዎች ወይም በማንኛውም ፍጡር አትተማመኑ። 4 እነርሱ በሚሞቱበት ጊዜ ወደ ዐፈር ይመለሳሉ፤ በዚያኑ ቀን ዕቅዳቸው ሁሉ ይጠፋል። 5 የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነለትና በአምላኩ በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረገ ሰው ደስ ይበለው፤ 6 እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ የፈጠረ ነው። እርሱ ዘወትር ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል፤ 7 ለተጨቈኑት ፍትሕን ይሰጣል፤ ለተራቡ ምግብን ይሰጣል። እስረኞችን ነጻ ያወጣል። 8 የዕውሮችን ዐይን ያበራል፤ የወደቁትን ያነሣል፤ ጻድቃንን ይወዳል። 9 እግዚአብሔር መጻተኞችን ይጠብቃል፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆች ይረዳል፤ የክፉዎችን ዕቅድ ግን ያፈርሣል። 10 እግዚአብሔር ለዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ጽዮን ሆይ አምላክሽ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይነግሣል። እግዚአብሔር ይመስገን! |