Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 77 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የመጽናኛ ጸሎት

1 እርሱ ይሰማኝ ዘንድ ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤ አሁንም ድምፄን ከፍ አድርጌ እጮኻለሁ።

2 በችግር ጊዜ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ሌሊቱን ሙሉ ያለ ዕረፍት እጆቼን ዘርግቼ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ይሁን እንጂ ለመጽናናት አልቻልኩም።

3 ስለ እግዚአብሔር በማስብበት ጊዜ እተክዛለሁ፤ በጥሞና ሳሰላስል መንፈሴ ይዝላል።

4 ሌሊቱን ሙሉ አነቃኸኝ፤ ጭንቀቴም ስለ በዛ መናገር አልቻልኩም።

5 ስላለፉት ቀኖች አስባለሁ፤ ጥንት ስለ ነበሩት ዓመቶችም አስታውሳለሁ።

6 ሌሊቱን የማነጋው በጥልቅ ሐሳብ ነው፤ ሳሰላስል ሳለሁ ራሴን የምጠይቀው እንዲህ እያልኩ ነው፤

7 “እግዚአብሔር ለዘወትር ይጥለናልን? ከእንግዲህስ ወዲህ ለእኛ ቸርነት አያደርግምን?

8 እኛን ማፍቀሩንስ ፈጽሞ ትቶአልን? ቃል ኪዳኑስ ከእንግዲህ ወዲህ አይጸናምን?

9 እግዚአብሔር ምሕረት ማድረጉን ረስቶአልን? ቊጣውስ ርኅራኄውን ገታውን?”

10 ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! እኔን ያስጨነቀኝ በታላቁ ኀይልህ እኛን ከመርዳት ማቆምህ ነው።

11 እግዚአብሔር ሆይ! ያከናወንካቸውን ታላላቅ ሥራዎች አስታውሳለሁ፤ ባለፉት ዘመናት ያደረግኻቸው ተአምራት ትዝ ይሉኛል።

12 ሥራዎችህን በጥሞና አሰላስላለሁ፤ ለድርጊቶችህም ከፍ ያለ ግምት እሰጣለሁ።

13 አምላክ ሆይ፥ አንተ የምታደርገው ሁሉ ቅዱስ ነው፤ እንደ አንተ ያለ ታላቅ አምላክ ማነው?

14 ተአምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ፤ አንተ በሕዝቦች መካከል ኀይልህን አሳይተሃል።

15 በኀይልህ የያዕቆብና የዮሴፍ ዘሮች የሆኑትን ሕዝብህን ተቤዥተሃል።

16 አምላክ ሆይ! ውሃው አንተን ባየ ጊዜ ፈራ፤ ጥልቅ ባሕሮችም ተንቀጠቀጡ።

17 ደመናዎች ዝናብን አዘነቡ፤ ነጐድጓድ በሰማይ አስገመገመ፤ የመብረቅ ፍላጻዎችህም ከላይ ከሰማይ አንጸባረቁ።

18 የነጐድጓድህ ጩኸት በዐውሎ ነፋስ አስተጋባ፤ የመብረቅ ብልጭታ ዓለምን አበራ፤ ምድር ተናወጠች፥ ተንቀጠቀጠችም።

19 መንገድህ በባሕር መካከል ነበር፤ ያለፍከውም በታላላቅ ወንዞች በኩል ነበር፤ ነገር ግን የእግርህ ዱካ አልተገኘም።

20 እረኛ የበጎችን መንጋ እንደሚመራ፥ አንተም በሙሴና በአሮን አማካይነት ሕዝብህን መራህ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos