መዝሙር 145 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምስጋና መዝሙር 1 አምላኬና ንጉሤ ሆይ! ታላቅነትህን ዐውጃለሁ፤ ለዘለዓለምም አመሰግንሃለሁ። 2 በየቀኑ አመሰግንሃለሁ፤ ለዘለዓለምም ስምህን አከብራለሁ። 3 እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ከፍተኛ ምስጋናም የሚገባው ነው፤ ታላቅነቱም ሰው ከሚያስተውለው በላይ ነው። 4 አንድ ትውልድ የአንተን ሥራ ለሚቀጥለው ትውልድ ያስተላልፋል፤ ድንቅ ሥራህንም ይገልጣል። 5 ሕዝቦች ስለ ክብርህና ስለ ግርማህ ታላቅነት ያወራሉ፤ እኔም ድንቅ ስለ ሆነው ሥራህ አሰላስላለሁ። 6 ሕዝቦች አስደናቂ ስለ ሆኑት ታላላቅ ሥራዎችህ ይናገራሉ፤ እኔም ታላቅነትህን ዐውጃለሁ። 7 ስለ ደግነትህ ገናናነት ይናገራሉ፤ ስለ ጽድቅህ ኀይል ከፍ ባለ ድምፅ ይዘምራሉ። 8 እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነው፤ ለቊጣ የዘገየና በዘለዓለማዊ ፍቅር የተሞላ ነው። 9 እርሱ ለሰው ሁሉ ቸር ነው፤ ለፍጡሮቹም ሁሉ ይራራል። 10 እግዚአብሔር ሆይ! ፍጡሮችህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ ሕዝቦችህም ሁሉ ያወድሱሃል። 11 ስለ ንጉሥነትህ ክብር ያወራሉ፤ ስለ ኀይልህም ይናገራሉ። 12 በዚህ ዐይነት ሰዎች ሁሉ በኀይልህ ስላደረግሃቸው ታላላቅ ሥራዎችና ስለ መንግሥትህም ታላቅ ግርማ ያውቃሉ። 13 ግዛትህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። መንግሥትህም ዘለዓለማዊ ነው። እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ የታመነ ነው፤ እርሱ የሚያደርገው ሁሉ መልካም ነው። 14 የሚንገዳገዱትን ይደግፋል፤ የወደቁትንም ያነሣቸዋል። 15 ሁሉም በተስፋ ወደ አንተ ይመለከታሉ፤ አንተም በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ። 16 እጅህን ከፍተህ የእያንዳንዱን ሕያው ፍጥረት ፍላጎት ታረካለህ። 17 እግዚአብሔር በሚያደርገው ሁሉ እውነተኛ ነው፤ በሥራውም ሁሉ ታማኝ ነው። 18 እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ ማለትም በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። 19 በአክብሮት ለሚፈሩት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ይሰጣቸዋል፤ ጩኸታቸውንም ሰምቶ ያድናቸዋል። 20 እርሱን የሚወዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ክፉዎችን ግን ይደመስሳል። 21 እኔ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ እርሱ የፈጠራቸው ሁሉ ቅዱስ ስሙን ለዘለዓለም ያወድሱ። |