Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዳንኤል 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለዳንኤል የተገለጠለት ስለ አራቱ አራዊት ራእይና ትርጒሙ
( 7፥1—12፥13 )

1 የባቢሎን ንጉሥ ብልጣሶር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት በአልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ፤ ዳንኤል ሕልምና ራእይ አየ፤ ከዚያም በኋላ ያየውን ሕልም ጻፈ።

2 እርሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ዳንኤል ከአራቱ ማእዘን የተነሣ ነፋስ ታላቁን ባሕር ሲያናውጥ ሌሊት በራእይ አየሁ።

3 አራት የተለያዩ ታላላቅ አውሬዎች ከባሕሩ ወጡ።

4 የመጀመሪያው አውሬ አንበሳ ይመስል ነበር፤ እርሱም እንደ ንስር ያሉ ክንፎች ነበሩት፤ እኔም እየተመለከትኩት ክንፎቹ ተነቃቀሉ፤ አውሬውም ቀና ብሎ እንደ ሰው በሁለት እግሮቹ ቆመ፤ ሰብአዊ አእምሮም ተሰጠው።

5 “ሁለተኛው አውሬ በኋላ እግሮቹ ሸብረክ ብሎ እንደ ቆመ ድብ ይመስል ነበር፤ በጥርሶቹም ሦስት የጐድን አጥንት ነክሶ ይዞአል፤ ‘የፈለግኸውን ያኽል ሥጋ ብላ!’ የሚል ድምፅም ተነገረው።

6 “ይህንን በመመልከት ላይ ሳለሁ እነሆ፥ ሌላ ነብር የሚመስል አውሬ ወጣ፤ እርሱም የወፍ ክንፎች የሚመስሉ አራት ክንፎች በጀርባው ላይ ነበሩት፤ አራት ራሶችም ነበሩት፤ የገዢነት ሥልጣንም ተሰጠው።

7 “ከዚያ በኋላ አራተኛውን አውሬ አየሁ፤ እርሱም አስፈሪ፥ አስደንጋጭና በጣም ኀይለኛ ነበር፤ ይህም አውሬ የሚቦጫጭቅባቸውና የሚሰባብርባቸው ታላላቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት። የተረፈውንም በእግሮቹ ይረግጠው ነበር፤ ካለፉትም አውሬዎች ሁሉ የተለየ ሆኖ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት።

8 እኔም ስለ ቀንዶቹ በማሰላሰል ላይ ሳለሁ ከቀንዶቹ መካከል ሌላ አንድ ትንሽ ቀንድ ወጣ፤ ለእርሱም ቦታ ለመልቀቅ ከፊተኞቹ ቀንዶች ሦስቱ ተነቀሉ፤ ይህም ትንሽ ቀንድ የሰው ዐይኖችና በትዕቢት የሚናገር አንደበት ነበረው።


ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖረው የተገለጠ ራእይ

9 “እኔም እየተመለከትኩ ሳለሁ ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ያ ጥንታዊው በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ፥ ጠጒሩም እንደ ነጭ ሱፍ ነበር፤ ዙፋኑና የዙፋኑ መንኰራኲር እንደሚነድ እሳት ይንበለበሉ ነበር።

10 የእሳትም ምንጭ ከዙፋኑ ፊት ይፈልቅ ነበር፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ አገልጋዮች ነበሩት፤ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ችሎት ተጀመረ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ።

11 “ቀንዱ የሚናገረውን የዕብሪታዊ ንግግር ድምፅ ሰምቼ ተመለከትኩ፤ እየተመለከትኩም ሳለ አውሬው ተይዞ ከተገደለ በኋላ ወደ እሳት በመጣል አካሉ እንዲጠፋ ተደረገ።

12 ሌሎቹም አውሬዎች ሥልጣናቸውን ተነጠቁ፤ ይሁን እንጂ ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው።

13 “በሌሊትም ራእይ የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ተከቦ ሲመጣ አየሁ፤ ወደዚያ ወደ ዘለዓለማዊው ፊት አቀረቡት።

14 በልዩ ልዩ አገር የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ያገለግሉት ዘንድ ሥልጣን፥ ክብርና ንጉሥነት ተሰጠው፤ ግዛቱም የማይጠፋ ዘለዓለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።


የራእዩ ትርጒም

15 “እኔ ዳንኤል ባየሁት ራእይ ተጨንቄ መንፈሴ ታወከ።

16 እዚያም ቆመው ከነበሩት ወደ አንዱ ቀረብ ብዬ የዚህን ሁሉ እውነት ትርጒም ጠየቅሁት፤ እርሱም የዚህን ሁሉ ትርጒም ነገረኝ።

17 እንዲህም አለኝ፦ ‘እነዚህ አራት ታላላቅ አውሬዎች በምድር ላይ የሚነሡ አራት መንግሥታት ናቸው።

18 ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን መንግሥቱን ወርሰው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የራሳቸው እንዲሆን ያደርጉታል።’

19 “ከዚህ በኋላ ከሌሎቹ አውሬዎች ሁሉ ልዩ ስለ ነበረው ስለ አራተኛው አውሬ በይበልጥ ለማወቅ ፈለግኹ፤ ይህ አውሬ እጅግ አስፈሪ የሆነ፥ ዐድኖ ያገኘውን ሁሉ በብረት ጥርሶቹና በነሐስ ጥፍሮቹ ሰባብሮና ቦጫጭቆ የሚበላ፥ የተረፈውንም በእግሩ የሚረጋግጥ ነበር።

20 ደግሞም በዚህ አውሬ ራስ ላይ ስለ ነበሩት ዐሥር ቀንዶችና በኋላ ስለ በቀለው ትንሽ ቀንድ፥ እንዲሁም ለትንሹ ቀንድ ቦታ ለመተው ተነቃቅለው ስለ ወደቁት ሦስት ቀንዶች ለማወቅ ፈለግኹ። ይህ ትንሽ ቀንድ ዐይኖችና አፍ ነበረው፤ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ አስፈሪ ሆኖ በትዕቢት ይናገር ነበር።

21 “እኔም በመመልከት ላይ ሳለሁ ያ ትንሽ ቀንድ በእግዚአብሔር ቅዱሳን ላይ ጦርነት አስነሥቶ ድል አደረጋቸው።

22 ይህም የሆነው ዘለዓለማዊው መጥቶ ለልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን ፍትሕ እስከ ሰጠበት ጊዜ ድረስ ነው፤ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወርሱበት ጊዜ ደረሰ።

23 “እርሱም ትርጒሙን እንዲህ ሲል አስረዳኝ፤ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛ መንግሥት ነው፤ ይህ መንግሥት ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ በመሆኑ ምድርን ሁሉ በመውረር ረግጦና ቀጥቅጦ ይገዛል።

24 ዐሥሩ ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡት ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያን በኋላ ከበፊተኞቹ ነገሥታት የተለየ ሌላ ንጉሥ ተነሥቶ ከዐሥሩ መንግሥታት ሦስቱን ይገለብጣል፤

25 በልዑል እግዚአብሔር ላይ በመታበይ ይናገራል፤ የልዑል እግዚአብሔርንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ የተቀደሱ በዓላትንና ሕጉን ለመለወጥ ያቅዳል፤ ቅዱሳኑም ለሦስት ዓመት ተኩል በእርሱ ሥልጣን ሥር ይሆናሉ።

26 ከዚያን በኋላ የፍርድ ዙፋን ይዘረጋል፤ እርሱም መንግሥታዊ ሥልጣኑን ተገፎ ለዘለዓለም ይደመሰሳል፤

27 ከሰማይ ሁሉ በታች በምድር ላይ ያለ የመንግሥት ሥልጣን፥ ኀይልና ገናናነት ሁሉ ለልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን ይሰጣል፤ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የዓለም ግዛቶች ሁሉም ለእነርሱ በመታዘዝ ያገለግሉአቸዋል።’ ”

28 የሕልሙም ትርጒም እዚህ ላይ ይፈጸማል፤ እኔም ዳንኤል እጅግ ሐሳቡ አስፈራኝ፤ በመደንገጥም ፊቴ ገረጣ፤ ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር በልቤ ሰውሬ ያዝኩ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos