1 ዮሐንስ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዓለምን ስለ ማሸነፍ 1 ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያምን ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ አባቱን የሚወድ ሁሉ ልጁንም ይወዳል። 2 የእግዚአብሔርን ልጆች የምንወድ መሆናችንን የምናውቀው እግዚአብሔርን ስንወድና ትእዛዞቹንም ስንፈጽም ነው። 3 እግዚአብሔርንም መውደድ ማለት ትእዛዞቹንም መፈጸም ነው፤ ትእዛዞቹም ከባዶች አይደሉም። 4 የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል፤ ዓለምን የምናሸንፈውም በእምነታችን ነው። 5 ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ከሚያምን ሰው በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው? ስለ ክርስቶስ የተሰጠ ምስክርነት 6 ጥምቀቱን በሚያመለክት ውሃና ሞቱን በሚያመለክት ደም የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ የመጣው በውሃ ብቻ ሳይሆን በውሃና በደም ነው። ይህም እውነት ስለ ሆነ ይህ ነገር እውነት መሆኑን መንፈስ ቅዱስ ይመሰክራል፤ 7 ሦስት ምስክሮች አሉ፤ 8 እነርሱም መንፈስ፥ ውሃና ደም ናቸው፤ እነዚህም ሦስቱ በምስክርነት ይስማማሉ። 9 ሰዎች የሚሰጡትን ምስክርነት እንቀበላለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ምስክርነት ከሁሉ ይበልጣል። እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውም ምስክርነት ይህ ነው። 10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ይህ ምስክርነት በልቡ ውስጥ አለ፤ እግዚአብሔርን የማያምን ግን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውን ምስክርነት ባለማመኑ ሐሰተኛ አድርጎታል። 11 ምስክርነቱም እግዚአብሔር የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሰጠንና ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ የሚመሰክር ነው። 12 የእግዚአብሔር ልጅ ያለው ሕይወት አለው። የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ግን ሕይወት የለውም። የዘለዓለም ሕይወት 13 እናንተ በእግዚአብሔር ልጅ ስም የምታምኑ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ያላችሁ መሆኑን እንድታውቁ ይህን ሁሉ ጽፌላችኋለሁ። 14 ማንኛውንም ነገር እንደ እርሱ ፈቃድ ብንለምን እንደሚሰማን እንተማመናለን። 15 የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን ከእርሱ የምንለምነውን ሁሉ አሁኑኑ እንደምንቀበል እናውቃለን። 16 ማንም ሰው ወንድሙ ለሞት የማያደርስ ኃጢአት ሲሠራ ቢያየው ይጸልይለት፤ የሰውዬው ኃጢአት ለሞት የማያደርስ ከሆነ እግዚአብሔር ሕይወትን ይሰጠዋል። ነገር ግን ለሞት የሚያደርስ ኃጢአት አለ። ለእንዲህ ዐይነቱ ኃጢአት ይጸልይ አልልም። 17 ክፉ ሥራ ሁሉ ኃጢአት ነው። ይሁን እንጂ ለሞት የማያደርስ ኃጢአት አለ። 18 የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚጠብቀው የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሁሉ ኀጢአት እንደማይሠራ እናውቃለን፤ ሰይጣንም አይነካውም። 19 እኛ የእግዚአብሔር መሆናችንን እናውቃለን። ዓለም ግን በሞላው የሰይጣን ተገዢ ሆኖአል። 20 የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣና እውነተኛውን አምላክ እንድናውቅ አስተዋይ ልቡና እንደ ሰጠን እናውቃለን በልጁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእርሱ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ኅብረት አለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው። 21 ልጆች ሆይ! ጣዖቶችን ከማምለክ ራሳችሁን ጠብቁ። |