ኤርምያስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየንስሓ ጥሪ 1 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደ እኔ ለመመለስ ከፈለጋችሁ እነዚያን አጸያፊ ጣዖቶችን አስወግዳችሁ ለእኔ ብቻ ታማኞች ብትሆኑ፥ 2 በእውነትና በቅንነት ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብላችሁ ብትምሉ ሕዝቦች ይባረካሉ፤ በዚህም ይመካሉ።” 3 እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “እዳሪውን መሬት እረሱ፤ ዘራችሁን በሾኽ መካከል አትዝሩ! 4 እናንተ የይሁዳ ሕዝብና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሆይ! የልባችሁን ክፋት ገርዛችሁ አእምሮአችሁን በማንጻት ሁለንተናችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ይህን ባታደርጉ ግን በክፉ ሥራችሁ ምክንያት ቊጣዬ እንደ እሳት ይነዳል፤ ቊጣዬም ከነደደ ማንም ሊያጠፋው አይችልም።” ይሁዳን ለመውረር የጠላት ዛቻ 5 በምድሪቱ ሁሉ ላይ መለከት ንፉ! ድምፃችሁንም ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ! የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ወደተመሸጉ ከተሞች እንዲሸሹ ንገሩአቸው። 6 ለጽዮን መንገዱን አመልክቱአት! ሳትዘገዩ የደኅንነት ዋስትና ወደሚገኝበት ስፍራ ሽሹ! እግዚአብሔር ከሰሜን በኩል መቅሠፍትና ታላቅ ጥፋት ሊያመጣ ነው። 7 አንበሳ ከተሸሸገበት ደን እንደሚወጣ፥ ሕዝብን ሁሉ የሚያጠፋ ይነሣል፤ እርሱም ይሁዳን ለማጥፋት ይመጣል፤ የይሁዳ ከተሞች ይፈራርሳሉ፤ የሚኖርባቸውም አይገኝም። 8 የእግዚአብሔር ብርቱ ቊጣ ከይሁዳ ስላልተለየ፥ ማቅ ለብሳችሁ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ቀን ንጉሡና ባለሟሎቹ ፍርሀት ያድርባቸዋል፤ ካህናት ይንቀጠቀጣሉ፤ ነቢያትም ይደነግጣሉ።” 10 እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ማታለል አይሆንብህምን? ‘ሰላም ይሆንላችኋል’ ብለሃቸው ነበር፤ እነሆ አሁን ሰይፍ በአንገታቸው ላይ ተቃጥቶአል” አልኩ። 11 በዚያን ጊዜ ለዚህ ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ተብሎ ይነገራቸዋል፥ “በሕዝቤ ላይ የሚያቃጥል ነፋስ በበረሓ ካሉት ኰረብቶች ተነሥቶ ይነፍስባቸዋል፤ ይህም የሚያበጥር ወይም የሚያጠራ ነፋስ አይደለም። 12 በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚመጣ ነፋስ ስለ ሆነ ከሁሉ የበረታ ነው፤ ይህን ፍርድ በሕዝቡ ላይ የሚያስተላልፍ ራሱ እግዚአብሔር ነው።” የይሁዳ በጠላት መከበብ 13 “እነሆ የጠላት ሠራዊት እንደ ደመና አንዣቦአል፤ የጦር ሠረገሎቹ እንደ ዐውሎ ነፋስ ፈጣኖች ናቸው፤ ፈረሶቹም ከንስር ይበልጥ ይበራሉ፤ ለእኛ ወዮልን! ጠፍተናል! 14 “ኢየሩሳሌም ሆይ! መዳን ከፈለግሽ ክፋትን ሁሉ ከልብሽ አጥበሽ አስወግጂ፤ ለመሆኑ የኃጢአት ሐሳብ ከአእምሮሽ የማይጠፋው እስከ መቼ ነው? 15 “ከዳን ከተማና ከኤፍሬም ኰረብቶች ክፉ አዋጅ የሚያውጅ ድምፅ ይሰማል፤ 16 በይሁዳ ከተሞች ላይ ጦርነትን እያወጁ ወራሪዎች ከሩቅ አገር በመምጣት ላይ መሆናቸውን ለሕዝቦች አሳውቁ! ለኢየሩሳሌም ሕዝብም ንገሩ! 17 ሕዝብዋ በእግዚአብሔር ላይ ስለ ዐመፁ፥ እንደ መከር እህል ጠባቂ ኢየሩሳሌምን ጠላት ይከባታል፤” ይህን የተናገረ እግዚአብሔር ነው። 18 ይሁዳ ሆይ! ይህ ሁሉ የደረሰብሽ በአካሄድሽና በክፉ ሥራሽ ምክንያት ነው፤ ይህም ሁሉ የመረረ መከራ የመጣብሽ በኃጢአትሽ ምክንያት ስለ ሆነ ወደ ሰውነትሽ ዘልቆ ልብሽን አቊስሎታል። ኤርምያስ ለሕዝቡ ማዘኑ 19 ወይ ሥቃይ! ይህን ሁሉ ሥቃይ እንዴት መታገሥ እችላለሁ! ወይ ልቤ! የልቤ አመታት እንዴት ፈጠነ? የጥሩምባ ድምፅና የጦርነት ድምፅ እየሰማሁ፥ ዝም ብዬ መታገሥ አልችልም። 20 መቅሠፍት በመቅሠፍት ላይ ይደራረባል፤ አገሪቱ በሙሉ ፈራርሳ ጠፍ ሆናለች፤ ድንኳኖቻችን በድንገት ወደሙ፤ መጋረጃዎቻቸውም በቅጽበት ተቀደዱ። 21 የሰልፍ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ፥ የጦርነት ድምፅ ሲያስገመግም፥ የጥሩምባም ድምፅ ሲያስተጋባ የምሰማው እስከ መቼ ነው? 22 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ እኔን የማያውቁ ሞኞች ሆነዋል፤ ማስተዋል ስለ ጐደላቸው እንደ ሕፃናት የሚታለሉ ናቸው፤ ክፉ ነገር ለመሥራት የተራቀቁ ብልኆች ናቸው፤ መልካም ነገር ማድረግ ግን ከቶ አይሆንላቸውም።” ስለሚመጣው ጥፋት ኤርምያስ ያየው ራእይ 23 ምድርን ተመለከትኩ፤ እነሆ ባድማ ሆናለች፤ ሰማይንም ተመለከትኩ፤ እነሆ ብርሃን አይታይበትም። 24 ተራራዎችን ተመለከትኩ፤ እነርሱም በመንቀጥቀጥ ላይ ናቸው፤ ኰረብቶችንም አየሁ፤ እነሆ ወዲያና ወዲህ በመናጥ ላይ ናቸው። 25 ሕዝብ አለመኖሩን አየሁ፤ ወፎችም በረው ጠፍተዋል። 26 ለምለሚቱ ምድር ወደ በረሓነት ተለውጣለች፤ ከእግዚአብሔር ብርቱ ቊጣ የተነሣ፥ ከተሞችዋ ሁሉ ፈራርሰዋል። 27 እነሆ እግዚአብሔር፥ ምድሪቱ ወደ ምድረ በዳነት እንደምትለወጥ፥ እስከ መጨረሻው ግን እንደማይደምስሳት ተነግሮአል። 28 ምድር ታለቅሳለች፤ ሰማይም በጨለማ ይጋረዳል፤ ይህን እግዚአብሔር ተናግሮአል፤ ሐሳቡም አይለወጥም፤ ቊርጥ ውሳኔ አድርጎአል፤ ወደ ኋላም አይመለስም። 29 ከፈረሰኞችና ከቀስት ወርዋሪዎች ድንፋታ የተነሣ፥ የከተማ ሰው ሁሉ ይሸሻል፤ አንዳንዶቹ ወደ ጫካ ይሮጣሉ፤ የቀሩት በየአለቱ ላይ ይወጣሉ፤ እያንዳንዱ ከተማ ሰው የማይኖርበት ወና ይሆናል፤ የሚኖርበትም አያገኝም። 30 ለጥፋት የተዳረግሽ ኢየሩሳሌም ሆይ! ወዮልሽ! ቀይ ልብስ የለበስሽበት ምክንያት ምንድን ነው? ጌጣጌጥ ማድረግሽና ዐይንሽንስ መኳልሽ ለምንድነው? ውሽሞችሽ ጠልተውሽ ሊገድሉሽ ስለሚፈልጉ ውበትሽን የምትንከባከቢው በከንቱ ነው። 31 ምጥ የያዛት ሴት የምታሰማውን ጩኸት የመሰለ ድምፅ ሰማሁ፤ የመጀመሪያ ልጅዋን የምትወልድ በካር ሴት የምታሰማውን ድምፅ የመሰለ ኡኡታም አዳመጥኩ፤ ይህም ድምፅ ኢየሩሳሌም ትንፋሽ አጥሮአት እጅዋን ዘርግታ “ወዮልኝ! ጠፋሁ! እነሆ ሊገድሉኝ መጡ!” እያለች የምታሰማው ጩኸት ነበር። |