መዝሙር 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምቅን ፈራጅ ለሆነው አምላክ የሚቀርብ ምስጋና 1 አምላክ ሆይ! በሙሉ ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ ያደረግኸውንም ድንቅ ነገር ሁሉ እናገራለሁ! 2 በአንተ ደስ ይለኛል፤ ሐሴትም አደርጋለሁ፤ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ለስምህ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ። 3 አንተ በምትገለጥበት ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላ ይመለሳሉ፤ ተሰናክለውም ከፊትህ ይጠፋሉ። 4 በዙፋንህ ላይ ተቀምጠህ ትክክለኛ ፍርድን ፈራጅ ነህ። የእኔንም ጉዳይ በማየት መብቴን ጠብቀህ በቅን ትፈርድልኛለህ። 5 አሕዛብን ገሠጽክ፤ ክፉዎችንም አጠፋህ፤ ስማቸውንም ለዘለዓለም ደመሰስህ። 6 ጠላቶቻችን ለዘለዓለም ጠፍተዋል፤ ከተሞቻቸውንም ደምስሰሃል፤ መታሰቢያቸውም ጠፍቶአል። 7 እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፤ ዙፋኑንም ለፍርድ አዘጋጅቶአል። 8 ዓለምን በፍትሕ ያስተዳድራል፤ ሕዝቦችንም በትክክል ይዳኛል። 9 እግዚአብሔር ለተጨቈኑት መጠጊያ ነው፤ በመከራ ጊዜም መከላከያ አምባ ነው። 10 አምላክ ሆይ! በአንተ የሚተማመኑትን ሁሉ ስለማትተዋቸው ስምህን የሚያውቁ ሁሉ ይተማመኑብሃል። 11 በጽዮን ለሚኖር እግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር አቅርቡ! ያደረገውንም ድንቅ ሥራ ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ! 12 እግዚአብሔር የተጨቈኑትን ያስታውሳል ጩኸታቸውን አይረሳም የሚበድሉአቸውንም ይቀጣል። 13 እግዚአብሔር ሆይ! ምሕረትን አድርግልኝ! ጠላቶቼ የሚያደርሱብኝን መከራ ተመልከት! ከሞትም አድነኝ። 14 ይህን ብታደርግልኝ፥ በጽዮን አደባባይ፥ ምስጋናህን ሁሉ ለሕዝብ እናገራለሁ፤ ስላዳንከኝም ደስታዬን እገልጣለሁ። 15 አሕዛብ በቈፈሩት ጒድጓድ ወደቁ፤ በደበቁት ወጥመድ ተያዙ። 16 እግዚአብሔር በእውነተኛ ፍርዱ ተገለጠ፤ ክፉ ሰዎችም በክፉ ሥራቸው ወጥመድ ተያዙ። 17 ክፉዎች ወደ ሙታን ዓለም ይወርዳሉ። እግዚአብሔርንም ከረሱ ሕዝቦች ጋር ይቀላቀላሉ። 18 ችግረኞች ዘወትር እንደ ተረሱ አይቀሩም፤ የድኾችም ተስፋ ከንቱ ሆኖ ለዘለዓለም አይጠፋም። 19 አምላክ ሆይ! ሰዎች በብርታታቸው እንዳይጓደዱብህ ተነሥ፤ በአሕዛብም ላይ ፍረድ። 20 እግዚአብሔር ሆይ! እንዲፈሩህና ሰብአዊ ፍጡሮች መሆናቸውንም እንዲያውቁ አድርጋቸው። |