ሚክያስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚሆን የለቅሶ ዋይታ 1 ኢዮአታም፥ አካዝና ሕዝቅያስ በተከታታይ በይሁዳ በነገሡበት ዘመን እግዚአብሔር ለሞሬታዊው ለሚክያስ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም በራእይ በገለጠለት ጊዜ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ 2 እናንተ ሕዝቦች ሁላችሁም ይህን ስሙ! በምድር ላይ የምትኖሩ ሁሉ ይህን አድምጡ! ጌታ እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ ሆኖ ያጋልጣችኋል። 3 እነሆ፥ እግዚአብሔር ከቦታው ወጥቶ ይመጣል፤ ወርዶም በምድር ከፍታ ቦታዎች ላይ ይራመዳል። 4 በዚያን ጊዜ ሰም በእሳት እንደሚቀልጥና፥ ውሃም ከከፍተኛ ቦታ ወደ ታች እንደሚወርድ እንዲሁም ተራራዎች ከእርሱ ሥር ይቀልጣሉ፤ ሸለቆዎችም ይከፈታሉ። 5 ይህ ሁሉ የሆነው እስራኤላውያን በፈጸሙት በደል ምክንያት ነው፤ የእስራኤል ሕዝብ እንዲያምፁ ምክንያት የሆነው ማን ነው? ዋና ከተማዋ ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ ሕዝብ ጣዖት በማምለክ ኃጢአት እንዲሠሩ ያደረገ ማን ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን? 6 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ሰማርያን በሜዳ ላይ እንደሚታይ የቤት ፍርስራሽ ክምር አደርጋለሁ፤ የወይን መትከያ ቦታ ትሆናለች፤ የከተማይቱንም ፍርስራሽ ድንጋይ ወደ ሸለቆ አፈሰዋለሁ፤ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ። 7 ምስሎችዋ ሁሉ ይሰባበራሉ፤ ለመቅደስዋ አመንዝሮች የተከፈለውም ሁሉ በእሳት ይቃጠላሉ፤ ጣዖቶችዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ ሰማርያ እነዚህን ምስሎች የሰበሰበቻቸው የዝሙት ዋጋ መቀበያ ለማድረግ ነበር፤ አሁንም ጠላቶችዋ የዝሙት መጠቀሚያ ያደርጉአቸዋል።” በይሁዳ ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት 8 ከዚህ በኋላ ሚክያስ እንዲህ አለ፦ “በዚህ ምክንያት ‘ዋይ! ዋይ!’ እያልኩ አለቅሳለሁ፤ ሐዘኔንም ለመግለጥ ራቊቴንና ባዶ እግሬን እሄዳለሁ፤ እንደ ቀበሮ እጮኻለሁ፤ እንደ ሰጎንም የዋይታ ድምፅ አሰማለሁ። 9 የሰማርያ ቊስል ሊፈወስ የሚችል አይደለም፤ ይህም ሥቃይ ወደ ይሁዳ ደርሶአል፤ ሕዝቤ ወደሚሰበሰቡበት ወደ ኢየሩሳሌም አደባባይም ተዛምቶአል።” 10 በጌት ላሉት ጠላቶቻችን የደረሰብንን መከራ አትንገሩአቸው፤ በዚያም ፈጽሞ አታልቅሱ፤ በቤትዖፍራ በሚገኙት ወገኖቻችን መካከል ግን በትቢያ ላይ እየተንከባለላችሁ አልቅሱ! 11 እናንተ የሻፊር ሕዝቦች ራቊታችሁን ምርኮኞች ሆናችሁ በዕፍረት ዕለፉ፤ የጻእናን ኗሪዎች ከከተማው ለመውጣት አይደፍሩም፤ ቤትኤጼል ራስዋ የለቅሶ ቦታ ስለ ሆነች ለእናንተ መጠጊያ ልትሆን አትችልም። 12 የማሮት ሕዝብ “መልካም ነገር ይመጣልናል” ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ግን ጥፋትን በኢየሩሳሌም ላይ አውርዶአል። 13 የእስራኤል በደል በእናንተ ስለ ተገኘና ለኢየሩሳሌም የኃጢአት መጀመሪያ ስለ ሆናችሁ የላኪሽ ነዋሪዎች ሆይ፥ የሠረገላውን ፈረሶች ለጒሙ። 14 የይሁዳ ሕዝብ ሆይ፥ እናንተ እንግዲህ ለሞሬሼት ጋት የመሰነባበቻ ስጦታ ትሰጣላችሁ፤ የአክዚብም ሕዝብ የእስራኤልን ነገሥታት ያታልላሉ። 15 የመሪሳ ሕዝብ ሆይ! ወራሪ ጠላት አመጣባችኋለሁ፤ የተከበሩ የእስራኤል መሪዎችም በዐዱላም ዋሻ ይሸሸጋሉ። 16 እናንተ የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ልጆቻችሁ ተማርከው ስለሚወሰዱ፥ ስለ ነዚህ ስለምትወዱአቸው ልጆቻችሁ ሐዘን ጠጒራችሁን ተላጩ፤ ራሳችሁም እንደ ጥንብ አንሣ ራስ መላጣ ይሁን። |