መዝሙር 84 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔርን ቤት መናፈቅ 1 የሠራዊት አምላክ ሆይ! ቤተ መቅደስህ ምንኛ ተወዳጅ ነው! 2 የቤተ መቅደስህን አደባባይ በጣም እናፍቃለሁ፤ ለሕያው አምላክ በሙሉ ልቤ በደስታ እዘምራለሁ። 3 ንጉሤና አምላኬ የሠራዊት ጌታ ሆይ! ድንቢጦች ለመኖሪያቸው ጎጆ ሠርተዋል፤ ዋኖሶችም ጫጩቶቻቸውን የሚያኖሩበት በመሠዊያዎችህ አጠገብ ቤት አላቸው። 4 ዘወትር የምስጋና መዝሙር ለአንተ እያቀረቡ በመቅደስህ የሚኖሩ እንዴት የተባረኩ ናቸው! 5 ወደ ጽዮን ተራራ መንፈሳዊ ጒዞ ለማድረግ የሚፈልጉና የአንተን ርዳታ የሚያገኙ እንዴት የተባረኩ ናቸው? 6 ባካ በተባለው ደረቅ ሸለቆ በሚያልፉበት ጊዜ እግዚአብሔር ምንጭን ያፈልቅላቸዋል፤ የበልግም ዝናብ ኩሬዎችን ይሞላቸዋል። 7 በመጓዝ ላይ ሳሉ ብዙ ብርታትን ያገኛሉ፤ የአማልክትንም አምላክ በጽዮን ያዩታል። 8 የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ጸሎቴን ስማ፤ የያዕቆብ አምላክ ሆይ! አድምጠኝ። 9 አምላክ ሆይ! መርጠህ የቀባኸውን ንጉሣችንን ባርከው፤ ጋሻችን ስለ ሆነም ተመልከተው። 10 በሌላ ስፍራ አንድ ሺህ ቀን ከመቈየት በመቅደስህ አንድ ቀን መዋል የተሻለ ነው፤ በክፉዎች ቤት ከምኖር ይልቅ በእግዚአብሔር ቤት ዘበኛ ሆኜ መኖርን እመርጣለሁ። 11 ጌታችንና አምላካችን ሆይ! አንተ እንደ ፀሐይና እንደ ጋሻ ነህ፤ በቸርነትና በክብር ትጠብቀናለህ፤ ደግ ለሚሠሩ ሰዎች ማናቸውንም መልካም ነገር አትከለክላቸውም። 12 የሠራዊት አምላክ ሆይ! በአንተ የሚታመኑ እንዴት የተባረኩ ናቸው! |