ኤርምያስ 51 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበባቢሎን ላይ የሚደርስ ተጨማሪ ቅጣት 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ባቢሎንና ሕዝብዋን ጠራርጎ የሚያጠፋ ብርቱ ነፋስ አስነሣለሁ፤ 2 እኔ እንደ እህል የሚያበጥሯትና ምድርዋን የሚያጠፉ የውጪ ጠላቶችን ወደ ባቢሎን እልካለሁ፤ እነርሱም የምትጠፉበት ጊዜ ሲደርስ ከየአቅጣጫው አደጋ ይጥሉባታል። 3 ወታደሮችዋ ቀስታቸውን እስኪገትሩና ወይም የጦር ልብሳቸውን እስኪለብሱ ጊዜ አትስጡአቸው፤ ለወጣቶችዋ በመራራት ምሕረት አታድርጉ፤ ሠራዊትዋን በሙሉ ደምስሱ። 4 ወታደሮችዋ በከተሞቻቸው መንገዶች ላይ ቈስለው ይሞታሉ፤ 5 ምድራቸው በእኔ በእስራኤል ቅዱስ ዘንድ በበደል የተሞላች ብትሆንም እንኳ እኔ የሠራዊት ጌታ አምላካቸው እስራኤልንና ይሁዳን አልረሳኋቸውም። 6 ከባቢሎን ሽሹ! ሕይወታችሁንም ለማትረፍ አምልጡ! ባቢሎን በሠራችው ኃጢአት ምክንያት በከንቱ አትለቁ! እኔ ለእርስዋ የሚገባትን ቅጣት በመስጠት የምበቀልበት ጊዜ ነው። 7 መላው ዓለም ከእርስዋ ጠጥቶ ይሰክር ዘንድ ባቢሎን በእኔ እጅ እንደ ወርቅ ዋንጫ ነበረች፤ አሕዛብ ሁሉ የእርስዋን ወይን ጠጅ ጠጥተው አእምሮአቸውን ሳቱ። 8 ባቢሎን በድንገት ወድቃ ተሰብራለችና አልቅሱላት፤ ምናልባት ይፈወስ እንደ ሆነ ለቊስልዋ የሚቀባ መድኃኒት ፈልጉ። 9 በዚያ የሚኖሩ የውጪ አገር ሰዎች እንዲህ አሉ፦ ‘ባቢሎንን ልንፈውሳት ሞከርን፤ እርሷ ግን ልትፈወስ አልቻለችም፤ የተፈረደባት ፍርድ እስከ ደመና ድረስ ከፍ ስላለና ከዚያም በላይ እስከ ሰማይ ድረስ ስለ ደረሰ ትተናት እያንዳንዳችን ወደየሀገራችን እንሂድ።’ ” 10 እስራኤላውያን እንዲህ ተባባሉ፦ “እግዚአብሔር ለእኛ ትክክለኛ ፍርዱን ስለ ሰጠን ኑ! ወደ ኢየሩሳሌም ሄደን እግዚአብሔር አምላካችን ያደረገውን ሁሉ እንናገር።” 11 የእግዚአብሔር ዓላማ ስለ ቤተ መቅደሱ የበቀል ዕርምጃ ለመውሰድ ስለ ሆነ ባቢሎንን ለማጥፋት የሜዶንን ነገሥታት አነሣሥቶአል፤ ስለዚህ ፍላጻችሁን ሳሉ! ጋሻችሁንም አንሡ! 12 በባቢሎን ቅጥር ላይ አደጋ ጣሉ የሚል ምልክት አሳዩ! ጥበቃውን አጠናክሩ! ሰላዮችን መድቡ! ደፈጣ ተዋጊዎችንም አዘጋጁ፤ ይህንንም የምታደርጉት እግዚአብሔር በባቢሎን ሕዝብ ላይ ያቀደውንና የተናገረውን ተግባራዊ ስለሚያደርግ ነው። 13 አንቺ በታላላቅ ወንዞች አጠገብ የምትኖሪ ሀብታሚቱ ባቢሎን ሆይ! የተወሰነብሽ የመጥፊያሽ ዘመን ደርሶአል። 14 የሠራዊት አምላክ በባቢሎን ላይ ብዛቱ እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ሠራዊት እንደሚያመጣባት በስሙ ምሎአል፤ ያም ሠራዊት ድልን በመቀዳጀት ይደነፋል። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምስጋና መዝሙር 15 እግዚአብሔር በኀይሉ ምድርን፥ በጥበቡም ዓለምን ፈጠረ፤ በማስተዋሉም ሰማያትን ዘረጋ፤ 16 በሰማይ ያለው ውሃ በእርሱ ትእዛዝ ይናወጣል፤ እርሱ ደመናትን ከምድር ዳርቻ ያመጣል፤ ከዝናብ ጋርም መብረቅ እንዲበርቅ ያደርጋል፤ ከማከማቻው በማውጣት ነፋስ እንዲነፍስ ያደርጋል። 17 ሰዎች ሁሉ ሞኞችና አላዋቂዎች ሆኑ፤ የሠሩአቸው ምስሎች አሳፋሪ ስለ ሆኑና ሕይወትም ስለሌላቸው አንጥረኛው በሠራቸው ጣዖቶች አፍሮባቸዋል። 18 እነዚህ አማልክት ዋጋቢሶችና የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤ እግዚአብሔር ለፍርድ በሚገለጥበት ጊዜ ይደመሰሳሉ። 19 የያዕቆብ አምላክ ግን እንደ እነርሱ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው፤ ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንዲሆን እስራኤልን መርጦታል፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። የእግዚአብሔር መዶሻ 20 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ባቢሎን ሆይ! አንቺ የእኔ መዶሻና የጦር መሣሪያዬ ነበርሽ፤ በአንቺ ሕዝቦችን ለመጨፍጨፍ ተጠቅሜብሻለሁ፤ 21 ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፥ ሠረገሎችንና በሠረገሎች ላይ የሚቀመጡትን ለመሰባበር ተጠቀምኩብሽ፤ 22 በአንቺ ሴቶችንና ወንዶችን ሽማግሌውንና ወጣቱን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ሰባብሬአለሁ። 23 እረኛውንና መንጋውን፥ ገበሬውንና ጥማድ በሬዎቹን፥ ገዢዎችንና ታላላቅ ባለሥልጣኖችን ለማጥፋት መሣሪያ አደረግሁሽ።” የባቢሎን መቀጣት 24 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ባቢሎንና ሕዝብዋ በኢየሩሳሌም ስላደረጉት ክፉ ሥራ ሁሉ በመበቀል ብድራታቸውን ስከፍላቸው ታያላችሁ። 25 ባቢሎን ሆይ! ምድርን በመላ የምታጠፊ አንቺ አጥፊ ተራራ ሆይ፥ እኔ ተቃዋሚሽ ነኝ፤ በአንቺ ላይ እጄን ዘርግቼ ከገደሉ ጫፍ ላይ አንከባልልሻለሁ፤ እንደ ተቃጠለ ተራራም አደርግሻለሁ። 26 ለማእዘን ወይም ለመሠረት የሚያገለግል ድንጋይ አይገኝብሽም፥ አንቺ ለዘለዓለሙ ምድረ በዳ ትሆኚአለሽ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 27 “አደጋ ለመጣል የሚያስችል ምልክት ስጡ! ሕዝቦች ሁሉ መስማት እንዲችሉ እምቢልታ ንፉ! ባቢሎንን ይወጉ ዘንድ ሕዝቦችን አዘጋጁ! የአራራት፥ የሚኒና የአሽኬናዝ መንግሥታት አደጋ እንዲጥሉ ንገሩአቸው፤ የጦር አዛዥ የሚሆን ሰው ሹሙ፤ ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ፈረሶችን አምጡ። 28 ባቢሎንን ይወጉ ዘንድ ሕዝቦችን አዘጋጁ፤ መድቡ፤ ወደ ሜዶን ነገሥታት፥ ወደ መሪዎቻቸውና ጦር አዛዦቻቸው እንዲሁም እነርሱ በሚቈጣጠሩአቸው አገሮች ወደሚኖሩ ሠራዊት ሁሉ መልእክት ላኩ። 29 ባቢሎንን ማንም የማይኖርባት ምድረ በዳ እንድትሆን ለማድረግ እግዚአብሔር ያቀደውን የሚፈጽምበት ጊዜ ከመሆኑ የተነሣ፥ ምድር በመናወጥ ትንቀጠቀጣለች። 30 የባቢሎን ወታደሮች ጦርነቱን አቁመው በምሽጋቸው ተቀመጡ፤ የጀግንነትን ወኔ አጥተው እንደ ሴቶች ሆኑ፤ የከተማይቱ የቅጽር በሮች መወርወሪያዎች ተሰባብረዋል፤ ቤቶችም በእሳት ተቃጥለዋል። 31 የእርሱ ከተማ ከዳር እስከ ዳር የተያዘች መሆንዋን ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር አንዱ ሩዋጭ ለሌላው ሩዋጭ፥ አንዱ መልእክተኛ ለሌላው መልእክተኛ መልእክቱን ለማስተላለፍ ይሯሯጣሉ። 32 የጠላት ሠራዊት የወንዙን መሸጋገሪያ ይዞ የዘብ መጠበቂያዎቹን አቃጠለ፤ የባቢሎን ወታደሮች በመሸበር ተርበደበዱ፤ 33 ባቢሎን እንደ እህል መውቂያ አውድማ ትሆናለች፤ ሕዝብዋንም እንደሚወቃ እህል ጠላት ያበራያቸዋል። እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ።” 34 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በዘበዘ አደቀቃትም እንደ ባዶ ዕቃም አደረጋት፤ እንደ ዘንዶ ሕዝብዋን ዋጠ፤ ምርጥ ምርጡን ወስዶ የቀሩትን እንደሚተፋ ምግብ ጣላቸው። 35 ስለዚህ የጽዮን ከተማ ሕዝብ “በእኛ ላይ የደረሰው ሥቃይ በባቢሎን ላይ ይድረስ!” ይላሉ፤ የኢየሩሳሌምም ሕዝብ “የእኛ ደም እንደ ፈሰሰ የባቢሎናውያንም ደም ይፍሰስ!” ይላሉ። 36 ስለዚህ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “እኔ እናንተን እረዳለሁ፤ ባቢሎናውያንንም እበቀልላችኋለሁ፤ የባቢሎን የውሃ ምንጭና ወንዞችዋ ሁሉ እንዲደርቁ አደርጋለሁ። 37 ያቺ አገር የፍርስራሽ ክምርና የቀበሮዎች መፈንጫ ትሆናለች፤ ለማየትም የምታሰቅቅ ትሆናለች፤ ማንም አይኖርባትም፤ የሚያያትም ሁሉ ይሳለቅባታል። 38 ባቢሎናውያን ሁሉ እንደ አንበሳ ያገሣሉ፤ እንደ አንበሳ ደቦልም ያጒረመርማሉ። 39 ሞቅ ባላቸው ጊዜ የመጠጥ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ፤ እስኪሰክሩ ድረስም አጠጣቸዋለሁ፤ ከዚያም ዘለዓለማዊ እንቅልፍ ያንቀላፋሉ፤ እስከ መቼም አይነቁም። 40 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ በግ ጠቦቶችና እንደ አውራ ፍየሎች ወደ ዕርድ ቦታ እንዲወሰዱ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” 41 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎን ከተማ እንዴት ተወረረች! ያቺ የዓለም መመኪያ የነበረችው እርስዋ እንዴት ተያዘች! ባቢሎንስ በሕዝብ ዘንድ ምንኛ አስደንጋጭ ሆነች! 42 የባቢሎን ጠላቶች እንደ ውቅያኖስ ማዕበል ወጥተው ከተማይቱን አጥለቀለቋት። 43 ከተሞቹ ውሃ የማይገኝባቸውና ማንም ሊኖርባቸውም ሆነ ሊተላለፍባቸው የማይችል ምድረ በዳ ሆነዋል። 44 የባቢሎን ጣዖት የሆነውን ቤልን እቀጣለሁ፤ የተሰረቁ ዕቃዎቹንም ከእጁ አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህም አሕዛብ አይሰግዱለትም።” “የባቢሎን ቅጽሮች ወድቀዋል፤ 45 ሕዝቤ ሆይ! ከዚያ ሸሽታችሁ ውጡ! ከሚያስፈራውም ቊጣዬ ሕይወታችሁን ለማትረፍ አምልጡ! 46 ከምትሰሙትም የጒምጒምታ ወሬ የተነሣ በመፍራት ወኔአችሁ አይቀዝቅዝ፤ በየዓመቱ ልዩ ልዩ የጒምጒምታ ወሬ ይነዛል፤ በምድሪቱ ላይ አንዱ ንጉሥ ሌላውን እንደሚወጋ የሚገልጥ የዐመፅ ጒምጒምታ ወሬ ይሰማል። 47 ስለዚህም የባቢሎንን ጣዖቶች የማስወግድበት ጊዜ ይመጣል፤ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ኀፍረት ይደርሳል፤ የተገደሉባት ልጆችዋ ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ። 48 ባቢሎን ከሰሜን በሚመጡ አጥፊዎች እጅ በወደቀች ጊዜ በሰማይና በምድር የሚገኝ ሠራዊት ሁሉ በደስታ እልል ይላል። 49 ባቢሎን ለዓለም ሕዝብ እልቂት ምክንያት ሆናለች፤ ለብዙ እስራኤላውያን እልቂት ምክንያት በመሆንዋም እነሆ ባቢሎን ራስዋ መውደቅ አለባት፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” በባቢሎን ላሉት እስራኤላውያን የተላከ መልእክት 50 እግዚአብሔር በባቢሎን ላሉት ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ ከሞት የተረፋችሁ ሕዝቤ! ሳትዘገዩ ሂዱ! በሩቅ ሀገር ሆናችሁ እኔን እግዚአብሔርን አስታውሱ! ኢየሩሳሌምን በልባችሁ አስቡ! 51 ‘ስለ ተሰደብን አፈርን፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደ ተቀደሱ ስፍራዎች ባዕዳን ሰዎች ስለ ገቡ ተዋርደን አንገታችንን ደፋን።’ በሉ። 52 እኔ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው። በባቢሎን ጣዖቶች ላይ የምፈርድበትና በሀገሪቱም የሚገኙ ቊስለኞች የጭንቀት ድምፅ የሚያሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ 53 ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣ ከፍተኛውን ምሽግዋን ብታጠናክር እንኳ የሚደመስሳትን አጥፊ እልካለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” በባቢሎን ላይ የሚደርስ ተጨማሪ ጥፋት 54 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከባቢሎን ጩኸት፥ ከከለዳውያን ምድርም የታላቅ ጥፋት ድምፅ ይሰማል። 55 እንደ ባሕር ሞገድ የሚያስገመግም ሠራዊት በድንገት በባቢሎን ላይ ደርሶ እየደነፋ አደጋ ይጥልባታል፤ በዚህም እኔ አጠፋታለሁ፤ ጸጥም አደርጋታለሁ። 56 አጥፊዎች በባቢሎን ላይ ስለ ዘመቱ ወታደሮችዋ ተማረኩ፤ ቀስታቸውም ተሰባበረ፤ እኔ ለሁሉም እንደየሥራው ዋጋውን የምከፍል አምላክ ስለ ሆንኩ፥ ባቢሎን በፈጸመችው ግፍ መጠን ፍዳዋን እከፍላታለሁ። 57 መሳፍንትዋ፥ የጥበብ ሰዎችዋ፥ መሪዎችዋ፥ የጦር አዛዦችዋና ወታደሮችዋ ጠጥተው እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይተኛሉ፤ እስከ ዘለዓለም አይነቁም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ንጉሡ ነኝ፤ ስሜም የሠራዊት አምላክ ነው። 58 ሰፊው የባቢሎን ቅጽር ወድቆ ከመሬት ይደባለቃል፤ ከፍ ብለው የተሠሩ የቅጽር በሮችዋ በእሳት ይጋያሉ። የሕዝብዋ ድካም ከንቱ ይሆናል፤ ሕዝቦች የደከሙበት ነገር ሁሉ በእሳት ይወድማል። እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ።” ኤርምያስ ወደ ባቢሎን የላከው መልእክት 59 የማሕሴያ የልጅ ልጅ የሆነው የኔሪያ ልጅ ሠራያ የንጉሥ ሴዴቅያስ የቅርብ አገልጋይ ነበር፤ ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ሠራያ ከእርሱ ጋር ወደ ባቢሎን ወረደ፤ እኔም ኤርምያስ በዚያን ጊዜ መመሪያዎችን ሰጠሁት፤ 60 በባቢሎን ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንዲሁም ስለ እርስዋ የተነገረውን ቃል በመጽሐፍ ጻፍኩ፤ 61 ሠራያንም እንዲህ አልኩት “ባቢሎን እንደ ደረስህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ለሕዝቡ አንብብላቸው፤ 62 ከዚያም በኋላ ‘ጌታ ሆይ! አንተ ይህን ስፍራ እንደምታጠፋ ተናግረሃል፤ ስለዚህም ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ፍጥረት አይኖርባትም፤ ሰውም እንስሳም ስለሚጠፋ ለዘለዓለም ምድረ በዳ ሆና ትቀራለች’ በል። 63 ሠራያ ሆይ! ይህን መጽሐፍ ለሕዝቡ አንብበህ ከጨረስክ በኋላም መጽሐፉን ከድንጋይ ጋር አስረህ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወርውረህ ጣለው። 64 እንዲህም በል፦ ‘ባቢሎንም እንደዚሁ እግዚአብሔር በእርስዋ ላይ ከሚያመጣው ጥፋት የተነሣ ወድቃ ትቀራለች እንጂ እንደገና መነሣት አትችልም።’ ” ኤርምያስ የተናገረው ቃል እዚህ ላየ ተፈጸመ። |