ማቴዎስ 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበኢየሱስ ላይ የተደረገ ሤራ ( ማር. 14፥1-2 ፤ ሉቃ. 22፥1-2 ፤ ዮሐ. 11፥45-53 ) 1 ኢየሱስ ይህን ሁሉ ትምህርት አስተምሮ ባበቃ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ 2 “ከሁለት ቀን በኋላ የፋሲካ በዓል እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅ ለመሰቀል ተላልፎ ይሰጣል።” 3 በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች በካህናት አለቃው ግቢ ተሰበሰቡ። 4 እዚያም ኢየሱስን በተንኰል ለመያዝና ለመግደል አሤሩ። 5 ነገር ግን “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” አሉ። አንዲት ሴት ኢየሱስን ሽቶ እንደ ቀባችው ( ማር. 14፥3-9 ፤ ዮሐ. 12፥1-8 ) 6 እነሆ፥ ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበረ። 7 በዚያም ኢየሱስ በማእድ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ሽቶውንም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። 8 ደቀ መዛሙርቱ ይህን አይተው ተቈጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሽቶ ለምን በከንቱ ባከነ? 9 ይህ ሽቶ በብዙ ዋጋ ተሸጦ ለድኾች ሊሰጥ ይችል ነበር!” 10 ኢየሱስም ይህን ማለታቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ 11 ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እዚህ አልገኝም። 12 እርስዋ ይህን ሽቶ በእኔ ላይ ማፍሰስዋ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው። 13 በእውነት እላችኋለሁ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያዋ ይነገርላታል።” ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱ ( ማር. 14፥10-11 ፤ ሉቃ. 22፥3-6 ) 14 በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው አስቀሮታዊው ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ሄደና 15 “ኢየሱስን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አለ። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ሰጡት 16 እርሱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። ኢየሱስ የአይሁድን የፋሲካ ራት ከሐዋርያቱ ጋር እንደ በላ ( ማር. 14፥12-21 ፤ ሉቃ. 22፥7—14፥21-23፤ ዮሐ. 13፥21-30 ) 17 በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “የፋሲካ በዓልን ራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። 18 እርሱም “ወደ ከተማው ስትገቡ ወደምታገኙት ሰው ቤት ሂዱና ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በዓል ራት የምበላው በአንተ ቤት ነው ይላል’ በሉት” አለ። 19 ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ የፋሲካውንም ራት አዘጋጁ። 20 በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። 21 ሲበሉም ኢየሱስ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” አለ። 22 ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር በጣም አዝነው፥ እያንዳንዳቸው ጌታ ሆይ፥ “እኔ እሆን?” እያሉ ይጠይቁት ጀመር። 23 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ከእኔ ጋር በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው። 24 የሰው ልጅ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰው ልጅን አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” 25 አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፥ “መምህር ሆይ! እኔ እሆን?” አለ። ኢየሱስም፥ “አንተ እንዳልከው ነው” አለው። የቅዱስ ቊርባን ሥርዓት ( ማር. 14፥22-26 ፤ ሉቃ. 22፥15-23 ፤ 1ቆሮ. 11፥23-25 ) 26 ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። 27 ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ እንዲህ ሲል ሰጣቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጽዋ ጠጡ፤ 28 ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ 29 በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ፤” 30 ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ እንደ ተናገረ ( ማር. 14፥27-31 ፤ ሉቃ. 22፥31-34 ፤ ዮሐ. 13፥36-38 ) 31 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና በዚህች ሌሊት፥ ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ። 32 ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” 33 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም!” ብሎ ተናገረ። 34 ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮሁ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። 35 ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልግ ቢሆን እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” አለው። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንዲሁ ይሉ ነበር። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ እንደ ጸለየ ( ማር. 14፥32-42 ፤ ሉቃ. 22፥39-46 ) 36 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሱ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ሄጄ እስክጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ” አላቸው። 37 ከእርሱ ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች አስከትሎ ሄደ፤ ያዝንና ይጨነቅም ጀመረ። 38 እንዲህም አላቸው፦ “ለመሞት እስክደርስ ድረስ አዝኛለሁ፤ እናንተ እዚህ ቈዩ፤ ከእኔም ጋር ንቁ።” 39 ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደና፥ በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፥ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ጽዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” 40 ከዚህ በኋላ ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ፥ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር ለአንዲት ሰዓት እንኳ መንቃት አልቻላችሁምን? 41 ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” 42 እንደገናም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ርቆ ሄደና “አባቴ ሆይ! ይህ የመከራ ጽዋ ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ የአንተ ፈቃድ ይሁን” ሲል ጸለየ። 43 ደግሞም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። 44 እንደገናም ትቶአቸው ሄደና ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። 45 ከዚህ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ መጣና እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? ዕረፍትም እያደረጋችሁ ነውን? እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ የሚሰጥበት ሰዓቱ ደርሶአል፤ 46 ተነሡ እንሂድ! እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል!” የኢየሱስ ተላልፎ መሰጠትና መያዝ ( ማር. 14፥43-50 ፤ ሉቃ. 22፥47-53 ፤ ዮሐ. 18፥3-12 ) 47 ኢየሱስ ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች መጡ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆችና ከሕዝብ ሽማግሌዎች የተላኩ ነበሩ። 48 ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ለሰዎቹ “የምትፈልጉት እኔ የምስመው ነውና እርሱን ያዙት” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 49 ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” ብሎ ሳመው። 50 ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! እንግዲህ የመጣህበትን ጉዳይ ፈጽም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ ቀረቡና ያዙት። 51 በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። 52 ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልሰህ ክተተው። 53 ለመሆኑ እኔ አባቴን ብለምን እርሱ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ የመላእክት ሠራዊት ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? 54 እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ‘መከራ መቀበል አለበት’ የሚለው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዴት ይፈጸማል?” 55 በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ሳለሁ አልያዛችሁኝም ነበር፤ 56 ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው በነቢያት የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ኢየሱስ ወደ ፍርድ ሸንጎ መወሰዱ ( ማር. 14፥53-65 ፤ ሉቃ. 22፥54-55 ፤ ዮሐ. 18፥13—14፥19-24) 57 ከዚህ በኋላ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ወሰዱት፤ በዚያም የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ነበር። 58 ጴጥሮስ ግን እስከ ካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ተከተለው፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የነገሩን ፍጻሜ ለማየት ከዘበኞች ጋር ተቀመጠ። 59 የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባሎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር። 60 ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም፥ ሞት የሚያስፈርድበት ምስክርነት አላገኙም፤ በመጨረሻ ሁለት ምስክሮች ቀርበው፥ 61 “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሎአል” ሲሉ ተናገሩ። 62 የካህናት አለቃውም ተነሣና “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል ጠየቀው። 63 ኢየሱስ ግን ዝም አለ። የካህናት አለቃውም እንደገና ኢየሱስን “በሕያው እግዚአብሔር ስም ይዤሃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ መሲሕ እንደ ሆንክ ንገረን!” አለው። 64 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ እንዳልከው ነው፤ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታዩታላችሁ፤ እንዲሁም በሰማይ ደመና ሆኖ ሲመጣ ታዩታላችሁ እላችኋለሁ።” 65 በዚህ ጊዜ የካህናት አለቃው በብስጭት ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል! እናንተም ስድቡን ሰምታችኋል! ከዚህ የበለጠ ምን ምስክር ያስፈልጋል! 66 ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ሲሉ መለሱ። 67 በዚያን ጊዜ ምራቃቸውን ተፉበት፤ ጎሸሙት፤ በጥፊም እየመቱት፥ 68 “መሲሕ ሆይ! ማን ነው የመታህ? እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር። ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደ ካደ ( ማር. 14፥66-72 ፤ ሉቃ. 22፥56-62 ፤ ዮሐ. 18፥15—18፥25-27 ) 69 ጴጥሮስ ከቤት ውጪ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ በዚያን ጊዜ አንዲት ገረድ ወደ እርሱ ቀርባ “አንተም ከገሊላዊው ኢየሱስ ጋር ነበርክ!” አለችው። 70 እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቅም!” ሲል በሁሉም ፊት ካደ። 71 ሊወጣ ወደ በሩ ሲሄድ አንዲት ሌላ ገረድ አየችውና እዚያ ለነበሩት ሰዎች “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር!” አለች። 72 ጴጥሮስም “ይህን የምትዪውን ሰው አላውቀውም!” ሲል በመማል እንደገና ካደ። 73 ከጥቂት ጊዜ በኋላ እዚያ ቆመው የነበሩ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ጠጋ ብለው፦ “አነጋገርህ ያስታውቃል፤ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። 74 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፦ “እኔ ይህን ሰው አላውቀውም!” እያለ ራሱን መራገምና መማል ጀመረ። ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። 75 ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። ወደ ውጭም ወጣና ምርር ብሎ አለቀሰ። |