ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ኢዮስያስ ለፈጣሪው የፋሲካውን በግ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፤ በመጀመሪያው ወርም በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ ሠዋ። 2 ካህናቱንም የአገልግሎት ልብሳቸውን አልብሶ አቆማቸው፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ በየሰሞናቸው ሠራቸው። 3 ሌዋውያንንም አላቸው፥ “ለእስራኤል ካህናት ተገዙ፤ የንጉሡ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤተ መቅደስም በእግዚአብሔር ታቦት ቅድስና ሥርዐት አክብሯቸው። 4 ታቦቱንም በጫንቃችሁ መሸከም አይገባችሁም። አሁንም ፈጣሪያችን እግዚአብሔርን አምልኩት፤ የእስራኤልንም ሕዝብ አገልግሉ። 5 እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት መጽሐፍና እንደ ልጁ ሰሎሞንም ገናናነት በየሀገራችሁና በየነገዳችሁ ተዘጋጁ፤ ሌዋውያንም በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት በቤተ መቅደስ በየቦታችሁና በየሀገራችሁ ግዛት በየሹመታችሁ ቁሙ። 6 የፋሲካውንም በግ ሠዉ፤ ለወንድሞቻችሁም መሥዋዕቱን አዘጋጁ፤ ለሙሴ በተሰጠው በእግዚአብሔርም ሕግ ፋሲካን አድርጉ።” 7 ኢዮስያስም በዚያ ለነበሩ ሰዎች ሠላሳ ሺህ ፍየሎችንና በጎችን፥ ሦስት ሺህ በሬዎችንም ሰጣቸው፤ እንደዚሁም ለሕዝቡ፥ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም ከንጉሥ ቤት አዝዞ ሰጠ። 8 የቤተ መቅደሱም ሹሞች ኬልቅያስ፥ ዘካርያስና ሲሉያስ ለካህናቱ ለፋሲካ በዓል ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችንና ሦስት መቶ በሬዎችን ሰጧቸው። 9 መሳፍንቱም ኢኮንያስና ሳሚያስ፥ ወንድሙ ናትናኤልና ሲብያስ፥ ኪያሎስና ኢዮራም ለሌዋውያን ለፋሲካቸው ሺህ በጎችንና ሰባት መቶ በሬዎችን ሰጧቸው። 10 ካህናቱና ሌዋውያኑም እንደ ሕጉ እንዲሁ መልካም አደረጉ፤ ቂጣውንም በየነገዳቸው ተመገቡ። 11 በሙሴ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ በሕዝቡ ፊት በየአባቶቻቸው ሹመት መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር አቀረቡ። 12 በነጋውም እንደዚሁ እንደ ሥርዐታቸው የፋሲካውን በግ በእሳት ሠዉ፤ መሥዋዕቶችንም በጋንና በብረት ምጣድ አበሰሉ። 13 ለሕዝቡም ሁሉ በጎ መዓዛ ያለውን መሥዋዕት ሠሩላቸው፤ ከዚህም በኋላ ለራሳቸውና ለወንድሞቻቸው ለአሮን ልጆች ካህናት አዘጋጁላቸው። 14 ካህናቱ ግን ቀኑ እስኪመሽ ድረስ የሰባውን መሥዕዋት ሠዉ፤ ሌዋውያኑም ለራሳቸውና ለወንድሞቻቸው ለአሮን ልጆች ሠዉ። 15 መዘምራኑ የአሳፍ ልጆችም ዳዊት በሠራው ሥርዐት በሹመታቸው ነበሩ፤ ከንጉሡ የተሾሙ አሳፍና ዘካርያስ፥ ዐዲኑስም ነበሩ። 16 የበሩ ሁሉ ጠባቂዎችም ነበሩ፤ ከሰሞኑም የሚያጓድል አልነበረም፤ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና። 17 ያንጊዜም የእግዚአብሔርን መሥዋዕት አቅርበው ጨረሱ። 18 ንጉሡ ኢዮስያስ እንዳዘዘም ፋሲካቸውን አደረጉ፤ ወደ እግዚአብሔርም መሠዊያ መሥዋዕታቸውን አቀረቡ። 19 በእነዚያም ወራቶች የነበሩ የእስራኤል ልጆች ፋሲካንና የቂጣውን በዓል ለሰባት ቀን አደረጉ። 20 ከነቢዩ ከሳሙኤልም ዘመን ወዲህ በእስራኤል ዘንድ እንደ እርሱ ያለ በዓል አልተደረገም። 21 የእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስ እንዳደረገው ፋሲካን አላደረጉም፤ ሌዋውያንና ካህናት፥ አይሁድና ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በዚያ የነበሩ እስራኤልም ሁሉ አላደረጉም። 22 ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ይህን ፋሲካ አደረገ። የኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ 23 የኢዮስያስም ሥራው እግዚአብሔርን መፍራት በተመላበት ልቡና በፈጣሪው ፊት የቀና ነበር። 24 በቀድሞው ዘመን ከአሕዛብና ከመንግሥታት ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽመው ስለ በደሉትና ስለ አሳዘኑት ሰዎች እንደ ተጻፈ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ቃሉን አጸና። 25 ከዚህም ከኢዮስያስ ሥራ ሁሉ በኋላ፦ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን በኤፍራጥስ ወንዝ በከርከሚስ ሠራዊቱን ይዞ ዘመተ፤ ኢዮስያስም ወጥቶ ተቀበለው። 26 የግብፅ ንጉሥም፥ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ እኔ ካንተ ጋራ ምን አለኝ?” ብሎ ላከበት። 27 “ከጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ በአንተ ላይ የተላክሁ አይደለም፥ እኔ የምወጋ ኤፍራጥስን ነውና፥ አሁንም እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ እግዚአብሔር በእኔ ዘንድ አለ፤ እርሱም ይረዳኛል፤ ገለል በል፤ ከእግዚአብሔርም ጋር አትከራከር” አለው። 28 ኢዮስያስም በሠረገላዎቹ ሆኖ ገለል አልልም አለ፤ ይዋጋም ዘንድ ጀመረ፤ ከእግዚአብሔርም አፍ በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረውን ቃል መስማት እንቢ አለ። 29 ነገር ግን መጊዶስ በሚባል ምድረ በዳ ይዋጋቸው ዘንድ ጸና፤ አለቆችም ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮስያስ ወረዱ። 30 ንጉሡም ብላቴኖቹን አላቸው፥ “እጅግ ደክሜአለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ፥” ብላቴኖቹም ወዲያውኑ ከሰልፉ ውስጥ አወጡት። 31 በሌላ ሰረገላውም ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፤ በዚያም ሞተ፤ በአባቱ መቃብርም ተቀበረ። 32 በይሁዳም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱለት፤ ኤርምያስም ለኢዮስያስ አለቀሰለት፤ እስከዚች ቀን ድረስም ወንዶች ሁሉ ከሴቶች ጋር አለቀሱለት፤ ለዘለዓለምም እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ ለእስራኤል ወገኖች ሥርዐት ሆኖ ተሰጠ። 33 ይህም በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጻፈ፤ ኢዮስያስም የሠራው ሥራ ሁሉ፥ ክብሩም፥ የእግዚአብሔርንም ሕግ ማወቁ፥ በፊትም፥ በኋላም የሠራው ሥራ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፏል። የመጨረሻዎቹ የይሁዳ ነገሥታት 34 ሕዝቡም የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በተወለደ በሃያ ሦስት ዓመት ዕድሜው በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ አነገሡት። 35 ለእስራኤልም በኢየሩሳሌም ሦስት ወር ነገሠ፤ የግብፅ ንጉሥም በኢየሩሳሌም ከመንግሥት አወረደው። 36 ሕዝቡንም ሁለት መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ አስገበራቸው። 37 የግብፅ ንጉሥም ወንድሙን ኢዮአቄምን የይሁዳ ንጉሥ አድርጎ በኢየሩሳሌም አነገሠው። 38 ኢዮአቄምም መሳፍንቱን አሰራቸው፤ ወንድሙ ዛርዮንንም ይዞ ወደ ግብፅ አገባው። 39 ኢዮአቄምም በይሁዳ በኢየሩሳሌም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ሆኖት ነበር፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 40 ከዚህም በኋላ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ እርሱ ዘመተ፤ በብረት ሰንሰለትም አስሮ ወደ ባቢሎን ሰደደው። 41 ናቡከደነፆርም የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ወስዶ ወደ ባቢሎን አገባው፤ በጣዖቱም ቤት አኖረው። 42 ይህም በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 43 ከዚህም በኋላ ልጁ ኢኮንያስ ነገሠ፤ ዕድሜውም ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበረ። 44 ሦስት ወር ከዐሥር ቀን በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 45 ከዓመትም በኋላ ናቡከደነፆር ከእግዚአብሔር ንዋየ ቅድሳት ጋር ልኮ ወደ ባቢሎን አገባው። 46 ሴዴቅያስንም በተወለደ በሃያ አንድ ዓመቱ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አነገሠው፤ ዐሥራ አንድ ዓመትም ነገሠ። 47 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በነቢዩ በኤርምያስ አፍ ከተነገረው ከእግዚአብሔርም ቃል የተነሣ አልፈራም። 48 ንጉሡ ናቡከደነፆርም በእግዚአብሔር ስም አማለው፤ እርሱ ግን ከዳው፤ አንገቱንም አደነደነ፤ ልቡናውንም አስታበየ፤ የእስራኤል ፈጣሪ የእግዚአብሔርንም ሕግ ተላለፈ። 49 የሕዝቡና የካህናቱ መሪዎችም ብዙ ተላለፉ፤ ከአሕዛብም ርኵሰት ይልቅ እጅግ በደሉ፤ በኢየሩሳሌምም የተቀደሰችውን የእግዚአብሔርን መቅደስ አሳደፉ። የኢየሩሳሌም ጥፋት 50 የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔርም ይገሥጻቸውና ይመልሳቸው ዘንድ መልእክተኛውን ላከ፤ ለእነርሱና ለመቅደሳቸው ይራራልና። 51 እነርሱ ግን በመልእክተኞቹ ዘበቱባቸው፤ እግዚአብሔርም በተናገራቸው ጊዜ በሕዝቡ እስኪቈጣ ድረስ በነቢያት ይስቁባቸው ነበር። 52 ጣዖቱን እጥፍ አድርገው ያመልኩ ነበርና የከላውዴዎን ክፍል የአሦር ነገሥታትም ይዘምቱባቸው ዘንድ አዘዘ። 53 መጥተውም በቤተ መቅደሱ አደባባይ ጐልማሶቻቸውን በሰይፍ ገደሉ፤ ለጐልማሳውም፥ ለቆንጆዋም፥ ለትልቁም፥ ለትንሹም ቢሆን አልራሩም፤ ሁሉንም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 54 የእግዚአብሔርንም ንዋየ ቅድሳት ትልቁንም ትንሹንም ሁሉ፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ ዘርፈው ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 55 የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሯን አፈረሱ፤ ግንቧንም በእሳት አቃጠሉ። 56 ያማረውንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ፤ ከጦር የቀሩትንም ማርከው ወደ ባቢሎን ወሰዱአቸው። 57 በነቢዩ በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይደርስ ዘንድ፥ ፋርሳውያን መግዛት እስከ ጀመሩበት ድረስ ለእርሱና ለልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ። 58 ምድርም በማረፍዋ ደስ ይላታል፤ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ ሰብዓው ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ታርፋለች። |