ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለዕዝራ ጥያቄ የተሰጠ መልስ 1 መልአኩም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ልዑል ይህን ዓለም፥ አዳምንና ከእርሱ የተወለዱትንም ሁሉ በፈጠራቸው ጊዜ ቍርጥ ፍርድንና ቅጣቱን አስቀድሞ አዘጋጀ። 2 አሁንም ከቃልህ የተነሣ አስተውል፤ እንዲህ ብለሃልና፦ ‘ክፉ ልብ ከእኛ ጋር ያድጋል፤ 3 በምድር የሚኖሩም ስለ እርሱ ይፈረድባቸዋል፥ አእምሮ ሳላቸው ይበድላሉና፥ ሕጉንም በልቡናቸው ተቀብለው ትእዛዙን አልጠበቁምና፥ ሕጉንም ተምረው የተቀበሉትን ሕጉንና ትእዛዙን ትተዋልና። 4 እንግዲህ በቍርጥ ፍርድ ቀን ምን ይሉ ዘንድ አላቸው? በኋለኛው ዘመንስ ምን ይናገራሉ? 5 ልዑል በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎችን ምን ያህል ታገሣቸው? ነገር ግን ስለ ወሰነው ጊዜ ነው እንጂ ስለ እነርሱ አይደለም።” ከፍርድ በፊት ያለ የሙታን ሁኔታ 6 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “በፊትህ ባለሟልነትን ካገኘሁ ይህንም ለባሪያህ ንገረው፤ በሞትን ጊዜ፥ ከእኛ ከእያንዳንዳችንም ነፍሳችን በምትወጣበት ጊዜ ቍርጥ ፍርዱን የሚያደርግበት ጊዜው እስኪደርስ ድረስ ይጠብቁናል? ወይስ ከዛሬ ጀምሮ ይፈረድብናል?” 7 እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ይህንም እነግርሃለሁ፤ አንተ ግን ከከሓድያን ጋር አትጨመርም፤ ከሚፈረድባቸውም ጋር አትቈጠርም። 8 በልዑል ዘንድ የተዘጋጀ መዝገብ ለአንተ አለህና፥ ነገር ግን እስከ ኋለኛው ቀን ድረስ አልገልጥልህም። 9 የሞትስ ነገር እንዲህ ነው፤ ከልዑል ዘንድ የትእዛዝ ቃል ከመጣ በኋላ፥ እገሌ ይሙት ባለ ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ትለያለች፤ ዳግመኛም ወደ ሰጣት ትመለሳለች፤ ለልዑል ጌትነትም አስቀድማ ትሰግዳለች። 10 የልዑልን መንገዶች ካልጠበቁ፥ የልዑልን ሕግ ካቃለሉ፥ እርሱንም መፍራትን ካላሰቡ ከከሓድያን ወገን ከሆኑ ግን፥ 11 እነዚያ የኃጥኣን ነፍሳት ይዞራሉ እንጂ ወደ ጻድቃን ማደሪያ አይገቡም፤ ከዚህ በኋላ መከራ ይቀበላሉ፤ ይጨነቃሉ፤ ያዝናሉም፤ ሰባቱንም ሥርዐታት ያሳዩአቸዋል። 12 መጀመሪያዪቱ ሥርዐት ይህች ናት፤ የልዑልን ሕግ ክደዋልና። 13 ሁለተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ መመለስ አይቻላቸውምና። 14 ሦስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፥ በልዑል ሥርዐት ላመኑ የተዘጋጀላቸውን ዋጋ ያያሉና። 15 አራተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ በኋላ ዘመን የሚጠብቃቸውን ፍርድ ያያሉና። 16 አምስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ መላእክት የጻድቃንን ነፍስ በማደሪያቸው ውስጥ በብዙ ዕረፍት ሲጠብቋቸው ያያሉና። 17 “ስድስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ ከዛሬ ጀምሮ የሚያገኛቸውን መከራ እያዞሩ ያሳዩአቸዋልና። 18 ከነገርሁህ ሥርዐታት ሁሉ የምትበልጥ ሰባተኛዪቱ ሥርዐት እንዲህ ናት፤ በፊቱ ይፈረድባቸው ዘንድ ያላቸው ዛሬ በሕይወታቸው ሳሉ እርሱን የበደሉ በፊታቸው የልዑልን ጌትነት ባዩ ጊዜ በኀሣር ይቀልጣሉና፥ በኀፍረትም ይጐሳቈላሉና፥ በፍርሀትም ይጠወልጋሉና። 19 “የልዑልን ሕግ የጠበቁ ግን ከመዋቲ ሥጋቸው በሚለዩበት ጊዜ ሥርዐታቸው እንዲህ ናት። 20 በኖረበት ዘመን ሁሉ ያስተማራቸው የልዑልን ሕግ ይፈጽሙ ዘንድ መከራቸውን ታግሠው ሁልጊዜ በድካም ለእግዚአብሔር ተገዝተውለታልና። 21 ስለዚህ ነገራቸው እንዲህ ነው። 22 መጀመሪያ የተቀባያቸውን የእግዚአብሔርን ጌትነት በብዙ ደስታ ያያሉ፤ ወደ ሰባቱም ሥርዐታት ይወስዷቸዋል። 23 መጀመሪያዪቱ ሥርዐት እንዲህ ናት፤ በዛሬው ሕይወታቸው በሞት እንዳያስታቸው በእነርሱ ያለ ክፉ አሳብን ድል ይነሡ ዘንድ በብዙ ድካም ተጋድለዋልና። 24 ሁለተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ የኃጥኣንን ነፍሳት በሚዞሩበት ያዩአቸዋልና፤ የሚጠብቃቸውንም ፍርድ ያያሉና። 25 ሦስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፥ በሕይወት ሳሉ በሃይማኖት የተቀበሉትን ሕጉን እንደ ጠበቁ የፈጠራቸው ምስክር ይሆንላቸዋልና። 26 አራተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፥ መላእክት እየጠበቋቸው ብዙ ደስታ ባለባቸው ማደሪያዎቻቸው ከዛሬ ጀምሮ የሚያርፉትን ዕረፍትና የሚቈያቸውን ክብር ያያሉና። 27 አምስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ ዛሬ ያለውን ሞት እንዴት ድል እንደነሡትና ኋላ ያገኙት ዘንድ ያላቸውን እንደ ወረሱ አይተው ደስ ይላቸዋልና፤ ዳግመኛም ድካምን ከተመላ ከዚህ ከጠባቡ የተነሣ እንደታገሡ፥ ያን ሰፊውን ሕይወት እንደሚያገኙ ያያሉ። ሞት በሌለበትም ለዘለዓለም ደስ ይላቸዋል። 28 ስድስተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ ፊታቸው እንደ ፀሐይ እንደሚያበራ፥ ብርሃናቸውም እንደ ከዋክብት እንደሚያንጸባርቅ ያሳዩአቸው ዘንድ አላቸውና፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይሞቱምና። 29 ከሁሉ የምትበልጥ ሰባተኛዪቱም ሥርዐት እንዲህ ናት፤ በእርሱ ዘንድ ይከብሩና ዋጋ ያገኙ ዘንድ ያላቸው በሕይወት ሳሉ የተገዙለትን ፊቱን ያዩ ዘንድ የሚቸኩሉ ስለ ሆነ ሳያፍሩ በብዙ ደስታ ተማምነው በግልጥ ይመካሉና። 30 “ከዛሬ ጀምሮ ያገኙ ዘንድ ያላቸው የጻድቃን ነፍሳት ሥርዐታቸው ይህ ነው፤ ከሓድያንም መከራ ይቀበሉ ዘንድ የነገርሁህ ሥርዐታቸው፥ መንገዳቸውና ፍርዳቸው ይህ ነው።” 31 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “ከሥጋዋ ከተለየች በኋላ ይህን የነገርኸኝን ታይ ዘንድ ለነፍስ ቀን ይሰጣታልን?” 32 “በእነዚያም በሰባቱ ቀኖች ይህን የነገርሁህን ሥራቸውን ሁሉ ያዩ ዘንድ ለሰባት ቀን ነጻ ናቸው፤ ከዚያም በኋላ ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ” አለኝ። 33 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ በፊትህ ባለሟልነትን ካገኘሁ ይህንም ለባሪያህ ዳግመኛ ንገረው፤ በፍርድ ቀን ጻድቃን በልዑል ዘንድ ለኃጥኣን መለመን ይችላሉን? 34 አባቶችም ለልጆቻቸው፥ ልጆችም ለአባቶቻቸው፥ ወንድሞችም ለወንድሞቻቸው፥ ዘመዶችም ለዘመዶቻቸው፥ ወዳጆችም ለወዳጆቻቸው መለመን ይችላሉን?” 35 እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “በፊቴ ባለሟልነትን አግኝተሃልና ይህንም እነግርሃለሁ፦ የፍርድ ቀንስ ለአንድ ጊዜ ናት፤ በሁሉም ትእዛዝ ላይ የእውነት ማኅተምን ያሳያቸዋል። 36 ዛሬ አባት ልጁን ስለ እርሱ፥ ልጅም አባቱን፥ ጌታም አገልጋዩን፥ ወዳጅም ወዳጁን ስለ እርሱ ታሞ ይተኛ ዘንድ፥ በልቶና ጠጥቶም ደስ ይለው ዘንድ፥ ይፈወስም ዘንድ እንደማይልከው፥ 37 እንደዚሁ አንዱ ለሌላው መለመን ፈጽሞ የሚችል ማንም የለም፤ የራሱንም ሸክም በባልንጀራው ላይ የሚመልስ ማንም የለም። ሁሉም ዋጋውን ያገኛልና፥ ሥራውም የየራሱ ነውና።” 38 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “ቀድሞ አብርሃም ስለ ሰዶምና ገሞራ፥ ሙሴም በምድረ በዳ በበደሉ ጊዜ ስለ አባቶቻችን እንደ ለመነ ዛሬ እንዴት አገኘን? 39 ኢያሱ በአካን ዘመን ስለ እስራኤል፥ ሳሙኤልም በሳኦል ዘመን፥ 40 ዳዊትም ስለ ቸነፈር፥ ሰሎሞንም ስለ ቤተ መቅደስ፥ ኤልያስም ስለ ዝናምና ስለ ሙታን ይድኑ ዘንድ፥ 41 ሕዝቅያስም በሰናክሬም ዘመን ለሕዝቡ፥ ብዙ ሰዎችም ስለ ብዙዎች ለመኑ። 42 እንግዲህ ዛሬ መዋቲው በሕይወት ሳለ፥ ኀጢአትም በዝታ ሳለች ጻድቃን ስለ ኃጥኣን ከለመኑ ያንጊዜስ እንደዚሁ እንደ ምን አይሆንም?” 43 እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “የዚህ የዛሬው ዓለም ፍጻሜው ገና አልሆነምና፤ የእግዚአብሔርም ክብር በውስጡ ለዘለዓለም ተገልጦ የሚኖር አይደለምና-። ስለዚህም ጽኑዓን ለድኩማን ለመኑ። 44 የፍርድ ቀንስ የዚህ ዓለም መጨረሻ ናት፤ መዋቲው ያልፍ ዘንድ፥ የማያልፈውም ይተካ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዓለም መጀመሪያ ናት። 45 ከዚህ በኋላ ድካም ይሻራል፤ ጠብም ይጠፋል፤ ጽድቅም ታብባለች፤ ቅንነት ትጸናለች። 46 ያንጊዜ በፍርድ ድል የተነሣ ሰውን ይቅር ማለት የሚቻለው የለም፤ ድል የነሣውንም መከራ ሊያጸናበት የሚችል የለም።” 47 እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “ቃሌ እንደ ቀደመው ነው፤ አሁንም እንዲህ እላለሁ፦ ምድር አዳምን ባታስገኘው በተሻለ ነበር፤ ከአስገኘችውም እንዳይበድል ባስተማረችው ነበር። 48 ሁላችን የምንኖረው ሕይወት ምን ይጠቅመናል? በኀዘን እንኖራለንና፤ ከሞትንም በኋላ ዳግመኛ ፍርድ ይቈየናልና። 49 አዳም ሆይ! ምን አደረግንህ? አንተ ባትበድል ይህች መከራ በእኛ ላይ ባልመጣችብን ነበር። 50 ተስፋ ያስደረግኸን፥ ሞት የሌለበት የሚመጣው ዓለም ምን ይጠቅመናል? እኛ ግን ሞትን የሚያመጣ ሥራን ሠራን። 51 የነገሩንን በጎውን ተስፋ አልሠራንም፤ እኛ ግን ክፉ ሥራን ሠራን። ዐመፅንም ተከተልን። 52 ኀዘንና ደዌ የሌለባቸውን፥ ለእኛ የተዘጋጁትን ቤቶች አልተከተልንም። እኛ ግን ኀጢአትን ሠራን። 53 ያጸናቸው ዘንድ መከራ የተቀበሉ ጻድቃን የልዑልን ጌትነት ያዩ ዘንድ አላቸውና፤ እኛ ግን በበደላችን ኖርን። 54 ፍሬው የማይጠወልግ ገነት ይገለጣልና፥ በውስጡም የሚገኘው ፍሬ ደስታና ሕይወት ነውና። 55 እኛ ግን አንገባም፤ የማንመሰገንበትን ሥራ እንሠራለንና። 56 ትዕግሥትን ያጸኗት ፊታቸው ይበራልና፥ የእኛ ፊት ግን ከጨለማ ይልቅ ይጠቍራል። 57 እነሆ፥ ከሞትን በኋላ በእኛ ላይ ምን እንዳለ ሳናውቅ እንኖራለን።” 58 መልአኩም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “በዚህ ዓለም ለሚጋደል፥ በምድር ለተወለደ ሰው የታሰበለት ይህ ነው። 59 ድል ያደረገ እኔ ያልሁትን ያገኛል፤ ድል የተነሣ ግን አንተ ያልኸውን ያገኛል። 60 ትድኑ ዘንድ ሕይወትን ምረጧት ብሎ ሙሴ ለሕዝቡ የነገራቸው መንገድ ይህች ናት። ነገር ግን እርሱን አልተቀበሉትም፤ ከእርሱም በኋላ ነቢያትን የተናገርኋቸው እኔንም አልተቀበሉም። 61 በሚያምኑ ሰዎች ደስታ እንዳለ በሚጠፉት ሰዎች ኀዘን የለም።” 62 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ፥ ምንጊዜም እንደ ኢምንት የሆኑትን ይቅር ባላቸው ጊዜ ልዑል ዛሬ ይቅር ባይ እንዲባል ፈጽሜ አውቃለሁ። 63 ይቅር ባይ ነው፤ ወደ ሕጉ የተመለሱትን ይቅር ይላቸዋልና። 64 ታጋሽም ነው፤ የበደሉትን ሰዎች እንደ ልጆች ይታገሣቸዋልና። 65 ለጋስም ነው፤ እንደ ሥራቸው እንደሚገባቸው መጠን ለነገርሁህ ሰዎች ይሰጣቸዋልና። 66 ምሕረቱም የበዛ ነው፤ ላሉት፥ ለሚታዘዙትም፥ ይመሰገኑ ዘንድ ላላቸውም ቸርነቱን ፈጽሞ ያበዛልና። 67 ቸርነቱን ፈጽሞ ካላበዛ ይህ ዓለም ባልኖረ ነበርና፥ በእርሱም ያሉ ባልኖሩ ነበርና። 68 ለጋስም ነው፤ ኃጥኣን ከኀጢአታቸው ይመለሱ ዘንድ ከቸርነቱ ካልሰጣቸው ሰው ሁሉ ባልዳነ ነበርና። 69 ፈራጅም ነው፤ እርሱ የፈጠረውን ፍጥረት ካልጠበቀ የከሓድያን ብዛታቸው ይጠፋልና፤ ከቍጥራቸውም ብዛት አይቀርምና። ያም ባይሆን በጣም ጥቂት ነው።” |