ሶስና1 በባቢሎን የሚኖር ስሙ ኢዮአቄም የሚባል አንድ ሰው ነበረ። 2 የኬልቅዩ ልጅ ስሟ ሶስና የምትባል ሚስት አግብቶ ነበር። እጅግም መልከ መልካምና እግዚአብሔርን የምትፈራ ነበረች። 3 ወላጆችዋም ደጋግ ሰዎች ነበሩ። ለልጃቸውም የሙሴን ሕግ አስተምረዋት ነበር። 4 ባሏ ኢዮአቄምም እጅግ ባለጸጋ ነበር፤ በቤቱም አጠገብ የተክል ቦታ ነበረው፤ ከሁሉ እርሱ ይከብር ነበርና አይሁድም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። 5 ኀጢአት ከባቢሎን፥ ሕዝቡን እንጠብቃቸዋለን ከሚሉ ግብዞች መምህራንም እንደ ወጣች እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የተናገረባቸው ሁለት ግብዞች መምህራን በዚያ ወራት በሕዝቡ መካከል ታዩ። 6 እነርሱም በኢዮአቄም ቤት ያገለግሉ ነበር፥ የሚፈራረዱ ሰዎችም ሁሉ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። 7 ሕዝቡ ሁሉ ወደ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ቀትር በሆነ ጊዜ ሶስና ወደ ባሏ ተክል ቦታ እየገባች በዚያ ትመላለስ ነበር። 8 እነዚያም ሁለት መምህራንበዚያ እየገባች ስትመላለስ ሁልጊዜ ያይዋት ነበር። እርሷንም ተመኙአት። 9 ልቡናቸውንም ለወጡ፤ ሰማይንም እንዳያዩ ዐይናቸውን ከደኑ፤ እውነተኛ ሕግንም አላሰቡም። 10 ሁለቱም ሁሉ በፍቅሯ ተነደፉ፤ እርስ በርሳቸውም በልቡናቸው ያለውን ነገር አልተነጋገሩም። 11 ምኞታቸውን መናገር አፍረዋልና። ከእርስዋም ጋር ይተኙ ዘንድ ይፈልጉ ነበር። 12 ያገኝዋትም ዘንድ ሁልጊዜ ይጠብቋት ነበር። 13 አንዱ ሁለተኛውን፥ “የምሣ ጊዜ ነውና ወደ ቤታችን እንግባ አለው፤” 14 እየራሳቸውም ተለያይተው ሄዱ። ተመልሰውም በዚያ በአንድነት ተገናኙ፤ ሁለቱም ሁሉ ተያዩ፤ ያንጊዜም ምኞታቸውን ተነጋገሩ። እርስዋንም ብቻዋን የሚያገኙበትን ጊዜ ተቃጠሩ። 15 ከዚህ በኋላ ቀን ሲጠብቋት ሶስና ሁልጊዜም ትገባ እንደ ነበር ከሁለቱ ደንገጥሮችዋ ጋር ገባች፤ አልቧትም ነበርና በተክል ቦታ ውስጥ ትታጠብ ዘንድ ወደደች። 16 ተሰውረውም ከሚጠብቋት ከሁለቱ መምህራን በቀር በዚያ ማንም አልነበረም። 17 ትታጠብም ዘንድ ደንገጥሮችዋን ሽቱና ዘይት እንዲያመጡና የተክሉን ቦታ በር እንዲዘጉ አዘዘቻቸው። 18 እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ፤ የተክሉንም ቦታ በር ዘግተው ያዘዘቻቸውን ያመጡ ዘንድ በስርጥ ጎዳና ወጡ፤ የተሰወሩ እነዚያን መምህራን ግን አላዩአቸውም ነበር። 19 እነዚያም ደንገጥሮች ከወጡ በኋላ ሁለቱ መምህራን ተነሥተው ወደ እርስዋ ሮጡ። 20 “እነሆ የተክሉ ቦታ በር ተዘግትዋል፤ የሚያየንም የለም፤ ከአንቺ ጋር እንተኛ ዘንድ እንወዳለንና እሺ በዪን። 21 ይህ ከአልሆነ ግን ከአንቺ ጋር ወንድ እንደ አገኘን ተናግረን እናጣላሻለን፤ ስለዚህም ነገር ደንገጥሮችሽን ከአንቺ አስወጥተሽ ሰደድሽ” አሏት። 22 ሶስናም አለቀሰች፤ ”በሁሉም ፈጽሜ ተቸነፍሁ፤ ባደርገውም እሞታለሁ፤ ባላደርገውም አልድንም፤ ከእጃቸው ማምለጥንም አልችልም። 23 በእግዚአብሔር ፊት ከምበድል ኀጢአት ሳልሠራ በእጃችሁ መውደቅ ይሻለኛል” አለች። 24 ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች፤ እነዚያም መምህራን ከእርሷ ጋር ጮኹ። 25 አንዱም ሮጦ የተክሉን ቦታ በር ከፈተ። 26 በቤትዋም ያሉ ሰዎች በተክል ቦታW መካከል ጩኸትን ሰምተው ወጡ፤ ምንም እንደ ሆነ ያዩ ዘንድ በሥርጥ ጎዳና ሮጡ። 27 እነዚህም ሁለቱ መምህራን ይህን ነገር በተናገሩ ጊዜ በሶስና እንደዚህ ያለ ነገር ፈጽሞ ተሰምቶ አያውቅም ነበርና ዘመዶችዋና አገልጋዮችዋ እጅግ አፈሩ። 28 በማግሥቱም ሕዝቡ በባሏ በኢዮአቄም ዘንድ በተሰበሰቡ ጊዜ እነዚያ ሁለት መምህራን ሶስናን ያስገድሏት ዘንድ ከአመፀኛ ልቡናቸው ጋር መጡ። 29 “በሕዝቡ ሁሉ ፊት ያመጧት ዘንድ ወደ ኢዮአቄም ሚስት ወደ ሶስና ላኩ” አሉ ወደሷም ላኩባት። 30 እርሷም ከእናትና ከአባትዋ፥ ከልጆችዋና ከዘመዶችዋም ሁሉ ጋር መጣች። 31 ሶስናም እጅግ ደመ ግቡና መልከ መልካም ነበረች። 32 እነዚያም ዐመፀኞች መምህራን መልኳን ለመጥገብ ክንብንቧን ይገልጧት ዘንድ አዘዙ፤ ክንብንቧንም ገለጧት። 33 አባትዋና እናትዋ፥ ቤተ ሰቦችዋም፥ የሚያውቋትም ሰዎች ሁሉ አለቀሱላት። 34 እነዚያም ሁለቱ መምህራን በሕዝቡ መካከል ተነሥተው እጆቻቸውን በራሷ ላይ አኖሩ። 35 እሷ ግን ልቡናዋ በእግዚአብሔር አምኗልና እያለቀሰች ወደ ሰማይ ተመለከተች። 36 እነዚያም መምህራን፥ “ብቻችንን በተክል ቦታ ውስጥ ስንመላለስ ይህች ሴት ከሁለቱ ደንገጥሮችዋ ጋር ገባች፤ ደንገጥሮችዋም ልካቸዋለችና የተክሉን ቦታ በር ዘግተው ሄዱ። 37 ደንገጥሮችዋንም ከላከቻቸው በኋላ አንድ ጎልማሳ ከተሰወረበት መጥቶ ከእርስዋ ጋር ተኛ። 38 እኛም በዚያ ተክል ቦታ ዳርቻ ሆነን ኀጢአታቸውን አየን፤ ወደ እነርሱም ሮጠን ሄድን፤ በአንድነትም ተኝተው አገኘናቸው። 39 እኛም እርሱን መያዝ ተሳነን፤ እሱ በርትቶብናልና አመለጠን፤ የተክል ቦታውንም በር ከፍቶ ወጣ። 40 እርስዋን ግን ያዝናት፤ ሰውየውም ማን እንደ ሆነ ጠየቅናት፤ ነገር ግን አልነገረችንም፤ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን” አሉ። 41 የሕዝብ መምህራን ነበሩና ፈራጆችም ነበሩና በአደባባይ የተሰበሰቡ ሰዎች ነገራቸውን አመኗቸው፤ ትሞትም ዘንድ ፈረዱባት። 42 ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች፥ “ዘለዓለማዊ የሆንህ፥ የተሰወረውን የምታውቅ፥ ከመሆኑ በፊት ሁሉን የምታውቅ አምላክ ሆይ! 43 በሐሰት እንደ መሰከሩብኝ አንተ ታውቃለህ፤ እነዚህ መምህራን ክፉ ነገርን ስለአደረጉብኝ የሠራሁት ነገር ሳይኖር እነሆ እሞታለሁ” አለች። 44 እግዚአብሔርም ቃሏን ሰማት። 45 ይገድሏትም ዘንድ ሲወስዷት እግዚአብሔር ስሙ ዳንኤል የሚባል የአንድ ወጣት ልጅ ልቡናን አነሣሣ። 46 እርሱም፥ “እኔ ከዚች ሴት ደም ንጹሕ ነኝ” ብሎ ቃሉን አሰምቶ ተናገረ። 47 ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ተመልሰው፥ “አንተ የምትናገረው ይህ ነገር ምንድን ነው?” አሉ። 48 ዳንኤልም በመካከላቸው ቆሞ፥ “አላዋቂዎች የምትሆኑ እናንት የእስራኤል ልጆች! ሳትመረምሩ፥ ነገሩንም ሳትረዱ በእስራኤል ሴት ልጅ ላይ እንደዚህ ትፈርዳላችሁን? 49 እነዚህ መምህራን በሐሰት መስክረውባታልና ወደ አደባባይ ተመለሱ” አላቸው። 50 ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ወደ አደባባይ ተመለሱ፤ አለቆችም ዳንኤልን፥ “እግዚአብሔር አንተን አልቆሃልና በመካከላችን ተቀምጠህ ንገረን” አሉት። 51 ዳንኤልም፥ “እየራሳቸው አራርቃችሁ አቁሟቸው፤ እኔም ልመርምራቸው” አላቸው። 52 እያንዳንዳቸውንም አራርቀው አቆሟቸው፤ እርሱም አንዱን ጠርቶ፥ “አንተ በክፋት ያረጀህ፥ ቀድሞ የሠራሃቸው ኀጢአቶችህ ደረሱብህ። 53 የሐሰት ፍርድን ፈርደሃልና ጻድቁንና ንጹሑን አትግደል ብሎ እግዚአብሔር ቢከለክል በደለኛውን አዳንህ፤ ንጹሑንም ገደልህ። 54 አሁንም ይህቺን ሴት ከአየሃት ሁለቱን ሁሉ በምን ዐይነት ዛፍ ሥር ሲጫወቱ አየህ? ንገረኝ” አለው “በኮክ ዛፍ ሥር ሲጫወቱ አየኋቸው” አለ። 55 ዳንኤልም፥ “በእውነት ሐሰትን ተናገርህ፤ ደምህ በራስህ ላይ ነው፤ ከመካከልህ ይሰነጥቅህ ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ እነሆ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዘዘ” አለው። 56 እርሱንም እልፍ አደረገው፤ ሁለተኛውንም ያመጡት ዘንድ አዘዘ፤ አመጡትም፤ “አንተ የይሁዳ ዘር ያይደለህ የከነዓን ዘር ነህ፤ ውበት አሳተህ፤ ክፉ ፈቃድም ልቡናህን ገለበጠው። 57 እርስዋ እናንተን መከራከር አልቻለችምና፥ የይሁዳ ሴት ልጅ እናንተን ፈርታለችና፥ ዐመፃችሁንም ታግሣለችና የእስራኤልን ሴት ልጅ እንዲህ ታደርጓታላችሁን። 58 አሁንም ሁለቱ ሲጫወቱ ያየህበት ዛፍ ምንድን ነው? ንገረኝ” አለው። እርሱም፥ “ሮማን በሚባል ዛፍ ሥር አየኋት” አለው። 59 ዳንኤልም፥ “አንተም በእውነት ሐሰትን ተናገርህ፤ ደምህም በራስህ ላይ ነው፤ በሰይፍ ከሁለት ይሰነጥቅህ ዘንድ፥ ፈጽሞም ያጠፋህ ዘንድ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ይጠብቅሃል” አለው። 60 ሕዝቡም ሁሉ ቃላቸውን አሰምተው ጮኹ፤ ያመነችበት፥ ሶስናን ያዳናት እግዚአብሔርንም አመሰገኑ። 61 ከቃላቸው የተነሣ ዳንኤል ነቅፏቸዋልና፥ ምስክርነታቸውንም ሐሰት አድርጎባቸዋልና በእነዚያ በሁለቱ መምህራን ላይ በጠላትነት ተነሡባቸው። 62 እንደ ሙሴም ሕግ በባልንጀራቸው ላይ ክፉ እንደ አደረጉ በእነርሱም ላይ አደረጉባቸው። ገደሉአቸውም፤ በዚያችም ቀን ንጹሕ ደምን አዳኑ። 63 በእርሷ ላይ ክፉ ሥራ አልተገኘምና ስለ ልጃቸው ስለ ሶስና ኬልቅዩና ሚስቱ ከባልዋ ከኢዮአቄምና ከዘመዶችዋ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን አመሰገኑት። 64 ዳንኤልም ከዚያች ቀን ጀምሮ ሁልጊዜ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት ገናና ሆነ። |