ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዓለም ፍጻሜ 1 “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል። 2 በምድርም ትቢያ ውስጥ ከአንቀላፉት ብዙዎች እኩሌቶቹ ለዘለዓለም ሕይወት፥ እኩሌቶቹም ለእፍረትና ለዘለዓለም ጕስቍልና ይነሣሉ። 3 ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ከጻድቃንም ብዙዎች እንደ ከዋክብት ለዘለዓለም ያበራሉ። 4 ዳንኤል ሆይ! አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፤ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፤ እውቀትም ይበዛል።” 5 እኔም ዳንኤል አየሁ፤ እነሆም ሁለት ሌሎች ቆመው ነበር፤ አንዱ በዚህ በወንዙ ዳር፥ ሌላውም በዚያ በወንዙ ዳር። 6 አንዱም ከወንዙ ውኃ በላይ የነበረውን በፍታም የለበሰውን፥ “የዚህ ምልክት ፍጻሜ እስከ መቼ ነው?” አለው። 7 ከወንዙም ውኃ በላይ የነበረው፥ በፍታም የለበሰው ሰው ቀኝና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ፥ “ለዘመንና ለዘመናት፥ ለዘመንም እኩሌታ ነው ፤ የተቀደሰውም ሕዝብ ኀይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል” ብሎ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ሲምል ሰማሁ። 8 ሰማሁም፤ ነገር ግን አላስተዋልሁም፤ የዚያን ጊዜም፥ “ጌታዬ ሆይ! የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድን ነው?” አልሁ። 9 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ዳንኤል ሆይ! ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤ 10 ብዙ ሰዎችም ሰውነታቸውን ያጠራሉ፤ ያነጡማል፤ ይፈተኑማል፤ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፤ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፤ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ። 11 ለጥፋት ርኵሰት ለመስጠት የዘወትሩ መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፥ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል። 12 የሚታገሥ፥ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን ነው። 13 አንተ ግን ሂድና እረፍ፤ ለፍጻሜው ገና ቀንና ዘመን አለ፤ በቀኑም መጨረሻ ትነሣለህ፤ በዕጣ ክፍልህም ትቆማለህ።” |