ኢሳይያስ 14:1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፤ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፤ በሀገራቸውም ያርፋሉ፤ መጻተኞችም ከእነርሱ ጋር አንድ ይሆናሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጨመራሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር ለያዕቆብ ይራራለታል፤ እስራኤልን እንደ ገና ይመርጠዋል፤ በራሳቸውም አገር ያኖራቸዋል። መጻተኞች ዐብረዋቸው ይኖራሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋራ ይተባበራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ ግን ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፤ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተሳሰራል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤል እንደገና ምሕረትን ያደርጋል፤ የራሱ ወገኖችም አድርጎ ይመርጣቸዋል፤ እንደገናም በአገራቸው እንዲኖሩ ይፈቅድላቸዋል፤ መጻተኞችም እንኳ መጥተው ከእነርሱ ጋር ተስማምተው አብረው ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፥ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃል። |
በዚያ ቀን አምስት የግብፅ ከተሞች በከነዓን ቋንቋ ይናገራሉ፤ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም ስም ይጠሩ ዘንድ ከተሞች አንድ ይሆናሉ፤ ከእነዚህም አንዲቱ የጽድቅ ከተማ ተብላ ትጠራለች።
ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ቃል፤ ዐውሎ ነፋስ በምድረ በዳ እንደሚያልፍ፥ እንዲሁ ከሚያስፈራ ሀገር ከምድረ በዳ ይመጣል።
አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ፥ ከማዕዘንዋም የጠራሁህ ነህና፦ አንተ ባሪያዬ ነህ፤ መርጬሃለሁ፤ አልጥልህም፤ ያልሁህ ሆይ፥
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ግብፅና የኢትዮጵያ ንግዶች ደከሙ፤ ቁመተ ረዥሞች የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይገዙልሃል፤ እጆቻቸውን ታስረው በኋላህ ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፤ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል።
አንቺ ድንግል የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ውረጂ፤ በትቢያም ላይ ተቀመጪ፤ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ ለስላሳና ቅምጥል አትባዪምና ያለ ዙፋን በመሬት ላይ ተቀመጪ።
የሚራራላቸውም ያጽናናቸዋልና፥ በውኃ ምንጮችም በኩል ይመራቸዋልና አይራቡም፤ አይጠሙም፤ የፀሐይ ትኩሳትም አይጐዳቸውም።
እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቅር ብሎአልና፥ ከሕዝቡም ችግረኞቹን አጽንቶአልና። ሰማያት ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ምድርም ደስ ይበላት፤ ተራሮችም እልል ይበሉ።
“በውኑ ሴት፥ ልጅዋን ትረሳለችን? ከማኅፀንዋ ለተወለደውስ አትራራምን? ሴት ይህን ብትረሳ፥ እኔ አንቺን አልረሳሽም።
እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፥ “በኀያላን የተማረኩ ይወሰዳሉ፤ የጨካኞችም ብዝበዛ ያመልጣል፤ እኔም ፍርድሽን እፈርድልሻለሁ፤ ልጆችሽንም አድናለሁ።
ታዳጊህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሕይወቱን የሚያስጨንቃትን፥ በአሕዛብ የተጠላውን የአለቆችን ባርያ ቀድሱት፤ ነገሥታት ያዩታል፤ አለቆችም ስለ እግዚአብሔር ብለው ተነሥተው ይሰግዱለታል፤ የእስራኤል ቅዱስ ታማኝ ነውና፥ እኔም መርጨሃለሁና።”
እንደ ገናምበቀኝና በግራ ተስፋፊ፤ ዘርሽ አሕዛብን ይወርሳሉና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ታደርጊያለሽና።
ክፉ ሰው መንገዱን፥ በደለኛም ዐሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ፤ እርሱም ይምረዋል፤ እርሱ ብዙ በደላችሁን ይተውላችኋልና።
ወደ እግዚአብሔርም የተጠጋ መጻተኛ፥ “በእውነት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ይለየኛል” አይበል፤ ጃንደረባም፥ “እነሆ፥ እኔ እንደ ደረቀ ዛፍ ነኝ” አይበል።
የአስጨናቂዎችሽም ልጆች እየተንቀጠቀጡ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእስራኤል ቅዱስ የእግዚአብሔር ከተማ፥ ጽዮን ተብለሽም ትጠሪያለሽ።
የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን በምስጋና ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁ ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎዎች፥ በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰችው ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።
ነገር ግን፥ “የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር፥ ከተሰደዱበትም ምድር ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
እገለጥላችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፤ ከአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እናንተንም ከበተንሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።
በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፤ እስራትህንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለሌላ አትገዛም።
የእስራኤል ድንግል ሆይ እንደ ገና እሠራሻለሁ፤ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ትወጫለሽ።
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ተገፍተዋል፤ የማረኩአቸውም ሁሉ በኀይል ይይዙአቸዋል፤ ይለቅቁአቸውም ዘንድ እንቢ ብለዋል።
ስድባችንን ስለ ሰማን አፍረናል፤ ባዕዳን ሰዎችም ወደ ቤተ መቅደሳችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብተዋልና ውርደት ፊታችንን ከድኖታል።
ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ የዘለዓለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ።
ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ፥ በእናንተም መካከል ልጆችን ለሚወልዱ መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንደ አሉ የሀገር ልጆች ይሆኑላችኋል፤ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ።
ደግሞም እንዲህ ስትል ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል።
ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፣ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፣ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።