ኢሳይያስ 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ግብፅ የተነገረ ትንቢት 1 ስለ ግብፅ የተነገረ ራእይ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፤ የግብፅም የእጆቻቸው ሥራዎች በፊቱ ይዋረዳሉ፤ የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል። 2 “ግብፃውያን በግብፃውያን ላይ ይነሣሉ፤ ወንድምም ወንድሙን፥ ሰውም ባልንጀራውን ይገድላል፤ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል። 3 የግብፅም መንፈስ በውስጣቸው ትደነግጣለች፤ ምክራቸውን አጠፋለሁ፤ እነርሱም አማልክቶቻቸውንና ጣዖቶቻቸውን፥ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎቻቸውንም ይጠይቃሉ። 4 ግብፃውያንንም በጨካኝ ጌቶች እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ጨካኞች ነገሥታትም ይገዟቸዋል” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 5 ግብፃውያን ከባሕር ውኃን ይጠጣሉ፤ ወንዙም ያንሳል፤ ደረቅም ይሆናል። 6 ወንዞችም ይነጥፋሉ። ቦዮችና መስኖች ያንሳሉ፤ ይደርቃሉም፤ ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ። 7 በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ፥ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ በነፋስ ይመታል፤ ይደርቃልም፤ 8 ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፤ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፤ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ያለቅሳሉ። 9 የተቈራረጠውንም መረብ የሚጠግኑ፥ ነጩንም ልብስ የሚሠሩ ሸማኔዎች ያፍራሉ። 10 በእነርሱም የሚሠሩ ይሠቃያሉ፤ በሐር ኩብ የሚነግዱ ሁሉ ይቀልጣሉ፤ ልቡናቸውም ያዝናል። 11 የጣኔዎስ አለቆች ሰነፎች ይሆናሉ፤ ነገሥታትን የሚመክሩ ጥበበኞችም ምክራቸው ስንፍና ትሆናለች። ንጉሥን፥ “እኛ የጥበበኞች ልጆች፥ የቀደሙ ነገሥታትም ልጆች ነን እንዴት ትሉታላችሁ?” 12 አሁን ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ያብስሩህ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በግብፅ ላይ ያሰበውን እስኪ ይንገሩህ። 13 የጣኔዎስ አለቆች አለቁ፤ የሜምፎስም አለቆች ከፍ ከፍ አሉ፤ ግብፃውያን በየወገናቸው ተሳሳቱ። 14 እግዚአብሔር የሚያስት መንፈስን ልኮባቸዋልና፤ ሰካርም፥ ደም ያዞረውም እንዲስት እንዲሁ ግብፃውያን በሥራቸው ሁሉ ሳቱ። 15 ለግብፃውያን ራስ ወይም ጅራት፥ መጀመሪያ ወይም መጨረሻ ያለው ሥራ የላቸውም። 16 በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከሚያወርድባቸው ፍርሀትና መንቀጥቀጥ የተነሣ ግብፃውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ። 17 የይሁዳም ምድር ግብፅን የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከመከረባት ምክር የተነሣ ስምዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል። 18 በዚያ ቀን አምስት የግብፅ ከተሞች በከነዓን ቋንቋ ይናገራሉ፤ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም ስም ይጠሩ ዘንድ ከተሞች አንድ ይሆናሉ፤ ከእነዚህም አንዲቱ የጽድቅ ከተማ ተብላ ትጠራለች። 19 በዚያ ቀን በግብፅ ምድር መካከል አንዲቱ ከተማ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ትሆናለች፤ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔርዐምድ ይሆናል። 20 ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብፅ ምድር ለዘለዓለም ምልክት ይሆናል፤ ከሚያስጨንቋቸው የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉና፥ እርሱም የሚያድናቸውን ሰው ይልክላቸዋል፤ ይፈርዳል፤ ያድናቸዋልም። 21 በዚያም ቀን እግዚአብሔር በግብፅ የታወቀ ይሆናል፤ በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ መሥዋዕትም ያቀርቡለታል፤ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ፤ መባኡንም ያገባሉ። 22 እግዚአብሔርም ግብፅን በታላቅ መቅሠፍት ይመታታል፤ ይፈውሳታልም፤ ከዚያም በኋላ ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ እርሱም ይሰማቸዋል፤ ይፈውሳቸውማል። 23 በዚያም ወራት ከግብፅ ወደ አሦር መንገድ ይሆናል፤ አሦራዊውም ወደ ግብፅ፥ ግብፃዊውም ወደ አሦር ይገባል፤ ግብፃውያንም ለአሦራውያን ይገዛሉ። 24 በዚያም ወራት እስራኤል ለግብፅና ለአሦር ሦስተኛ ይሆናል፤ በምድርም መካከል በረከት ይሆናል። 25 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ “በግብፅ ውስጥ ያለ ሕዝቤ፥ በአሦር መካከልም ያለ ሕዝቤ፥ ርስቴም እስራኤል የተባረከ ይሁን” ብሎ ይባርካቸዋልና። |