ኤርምያስ 51 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በባቢሎን ላይ ተጨማሪ ቅጣት 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ በባቢሎን ላይና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ የሚያቃጥልና የሚያጠፋ ነፋስን አስነሣለሁ። 2 በባቢሎንም ላይ ተሳዳቢ ሰዎችን እሰድዳለሁ፤ እነርሱም ይሰድቧታል፤ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፤ በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል። 3 በቀስት ወርዋሪው ላይ፥ በጥሩርም በሚነሣው ላይ ቀስተኛው ቀስቱን ይገትር፤ ለጐበዛዝቷ አትዘኑ፤ ሠራዊቷንም ሁሉ አጥፉ። 4 የተገደሉት በከለዳውያን ምድር ይወድቃሉ፤ የቈሰሉትም በውጭ ይወድቃሉ። 5 “ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል የተሞላች ብትሆንም፥ እስራኤል መበለት አልሆነችም፤ ይሁዳም ከአምላኩ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ አልራቀም። 6 ከባቢሎን መካከል ሽሹ፤ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ፤ በበደልዋ አትጥፉ፤ የእግዚአብሔር በቀል ጊዜ ነውና፥ እርሱም ብድራቷን ይከፍላታልና። 7 ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ ነበረች፤ አሕዛብም ከጠጅዋ ጠጥተዋል፤ ስለዚህ አሕዛብ ተንገዳግደዋል። 8 ባቢሎን በድንገት ወድቃ ተሰባብራለች፤ አልቅሱላት፤ ትፈወስም እንደ ሆነ ለቍስልዋ መድኀኒት ውሰዱላት። 9 ባቢሎንን ፈወስናት፥ እርስዋ ግን አልተፈወሰችም፤ ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፥ እስከ ከዋክብትም ድረስ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ እንተዋት፤ ሁላችንም ወደ ሀገራችን እንሂድ። 10 እግዚአብሔር ፍርዳችንን አውጥቶአል፤ ኑ በጽዮን የአምላካችን የእግዚአብሔርን ሥራ እንናገር። 11 “ፍላጾችን አዘጋጁ፤ ጕራንጕሬዎችንም ሙሉ፤ እግዚአብሔር ያጠፋት ዘንድ ቍጣው በባቢሎን ላይ ነውና የሜዶንን ንጉሥ መንፈስ አስነሥቶአል፤ የእግዚአብሔር በቀል የመቅደሱ በቀል ነውና። 12 በባቢሎን ቅጥሮች ላይ ዓላማውን አንሡ፤ ከጕራንጕሬአችሁ ጋር ጽኑ፤ ተመልካቾችን አቁሙ፤ መሣሪያችሁን አዘጋጁ። እግዚአብሔር በባቢሎን በሚኖሩት ላይ የተናገረውን ያደርግ ዘንድ ጀምሮአልና። 13 አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፥ በመዝገብም የበለጠግሽ ሆይ! እንደ ስስትሽ መጠን ፍጻሜሽ ደርሶአል። 14 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፦ በእውነት ሰዎችን እንደ አንበጣ እሞላብሻለሁ፤ እነርሱም እየሮጡ ይወርዱብሻል።” 15 ምድርን በኀይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 16 ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፤ ከምድርም ዳር ደመናትን ያወጣል፤ ለዝናብም ጊዜ መብረቅን ያደርጋል፤ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 17 ሰው ሁሉ ዕውቀትን አጥቶአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ሐሰተኞች ጣዖታትን ሠርተዋልና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። 18 ሥራቸው ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርም በጐበኛቸው ጊዜ ይጠፋሉ። 19 የያዕቆብ ዕድል ፋንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና። እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው። ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። 20 “አንቺ የጦር መሣሪያን በተንሽብኝ፤ እኔም ሕዝቡን እበትንብሻለሁ፤ ከአንቺም ነገሥታትን አስወግዳለሁ። 21 በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እበትናለሁ፤ በአንቺም ሰረገላውንና በላዩ የሚቀመጠውን እበትናለሁ። 22 በአንቺም ወንድና ሴትን እበትናለሁ፤ በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እበትናለሁ፤ በአንቺም ጐልማሳውንና ቆንጆዪቱን እበትናለሁ፤ 23 በአንቺም እረኛውንና መንጋውን እበትናለሁ፤ በአንቺም አራሹንና ጥማዱን እበትናለሁ፤ በአንቺም አለቆችንና መሳፍንትን እበትናለሁ። 24 በጽዮን በዐይናችሁ ፊት ስለ ሠሩት ክፋታቸው ሁሉ በባቢሎንና በከለዳውያን ምድር የሚኖሩትን ሁሉ እበቀላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 25 “አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊ ተራራ ሆይ! እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እጄንም እዘረጋብሃለሁ፤ ከድንጋዮቹም ላይ አንከባልልሃለሁ፤ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ። 26 ከአንተም ለማዕዘን የሚሆን ድንጋይንና ለመሠረት የሚሆን ድንጋይን አይወስዱም፤ ለዘለዓለምም አጠፋሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 27 “በምድር ላይ ዓላማን አንሡ፤ በአሕዛብም መካከል መለከትን ንፉ፤ አሕዛብንም ለዩባት፤ የአራራትንና የሚኒን የአስከናዝንም መንግሥታት እዘዙባት፤ ጦረኞችንም በላይዋ አቁሙ፤ ብዛታቸው እንደ አንበጣ የሆኑ ፈረሶችን በላይዋ አውጡ። 28 አሕዛብንም፥ የሜዶንንም ነገሥታት፥ አለቆችንም፥ መሳፍንትንም ሁሉ፥ የግዛታቸውንም ምድር ሁሉ ለዩባት። 29 ማንም እንዳይቀመጥባት የባቢሎንን ምድር ባድማ ያደርጋት ዘንድ የእግዚአብሔር ዐሳብ በባቢሎን ላይ ጸንቶአልና ምድር ተናወጠች፤ ታመመችም። 30 የባቢሎን ተዋጊዎች መዋጋትን ትተዋል፤ በአምባዎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኀይላቸውም ጠፍቶአል፤ እንደ ሴቶችም ሆነዋል፤ ማደሪያዎችዋም ነድደዋል፤ መወርወሪያዎችዋም ተሰብረዋል። 31 ለባቢሎን ንጉሥ ይነግር ዘንድ ሯጩ ሯጩን ለመገናኘት፤ መልእክተኛውም መልእክተኛውን ለመገናኘት ይሮጣል፤ ከተማዋ ከዳር እስከ ዳር ተይዛለችና፤ 32 መሻገሪያዎችዋም ተይዘዋልና፥ ቅጥርዋም በእሳት ተቃጥሎአልና፥ ሰልፈኞችም ተማርከዋልና።” 33 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “የባቢሎን ንጉሥ ቤት እንደ ተረገጠ አውድማ ናት፤ ጥቂት ቈይታ የመከር ጊዜ ይደርስባታል። 34 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላኝ፤ ከፋፈለኝም፤ እንደ ባዶ ዕቃም አደረገኝ፤ እንደ ዘንዶም ዋጠኝ፤ ከሚጣፍጠውም ሥጋዬ ሆዱን ሞላ። 35 በጽዮን የምትኖር በእኔ ላይ የተደረገ ግፍና ሥቃይ በባቢሎን ላይ ይሁን ትላለች፤ ኢየሩሳሌምም ደሜ በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን ትላለች።” 36 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ የሚገፋሽን እፈርድበታለሁ፤ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ፤ ባሕርዋንም ድርቅ አደርገዋለሁ፤ ምንጭዋንም አደርቃለሁ። 37 ባቢሎንም ባድማና የቀበሮ ማደሪያ፥ ማፍዋጫም ትሆናለች፤ የሚቀመጥባትም ሰው አይገኝም። 38 በአንድነትም እንደ አንበሶች ያገሣሉ፤ እንደ አንበሳም ደቦሎች ያጕረመርማሉ። 39 በሞቃቸው ጊዜ እንዲዝሉ፥ የዘለዓለምም እንቅልፍ እንዲተኙ መጠጥን አጠጣቸዋለሁ፤ አሰክራቸዋለሁም፤ ከዚያም በኋላ አይነቁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 40 እንደ ጠቦቶችና እንደ አውራ በጎች፥ እንደ አውራ ፍየሎችም ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ። 41 “የምድርም ሁሉ ክብር እንዴት ተያዘች! እንዴትስ ተወሰደች! ባቢሎን በአሕዛብ መካከል እንዴት ለጥፋት ሆነች! 42 ባሕር በባቢሎን ላይ ወጣ፤ በሞገዱም ብዛት ተከደነች። 43 ከተሞችዋ ባድማና ደረቅ ምድር፥ ሰውም የማይቀመጥበት፥ የሰውም ልጅ የማያልፍበት ምድር ሆኑ። 44 በባቢሎንም ላይ እበቀላለሁ፤ የዋጠችውንም ከአፍዋ አስተፋታለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርስዋ አይሰበሰቡም፤ የባቢሎንም ቅጥሮች ይወድቃሉ። 45 “ሕዝቤ ሆይ! ከመካከልዋ ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ራሳችሁን አድኑ። 46 በምድርም ከሚሰማ ወሬ የተነሣ አትፍሩ፤ ልባችሁም የዛለ አይሁን፤ በአንድ ዓመት ወሬ ይመጣል፤ ከዚያም በኋላ በሌላው ዓመት ወሬ ይመጣል፤ በምድርም ላይ ግፍ ይነግሣል፤ አለቃም በአለቃ ላይ ይነሣል። 47 ስለዚህ እነሆ የተቀረጹትን የባቢሎንን ምስሎች የምበቀልበት ዘመን ይመጣል፤ ምድርዋም ሁሉ ትደርቃለች፤ ተዋግተውም የሞቱት ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ። 48 አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር፥ በእነርሱም ያለው ሁሉ ስለ ባቢሎን ደስ ይላቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር። 49 ባቢሎንም በእስራኤል ስለ ተገደሉት ትወድቃለች፤ ስለ ባቢሎንም በምድር ሁሉ የተገደሉት ይወድቃሉ። 50 “ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ! ሂዱ፤ አትቁሙ፤ በሩቅ ያላችሁም እግዚአብሔርን አስቡ፤ ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡ። 51 ስድባችንን ስለ ሰማን አፍረናል፤ ባዕዳን ሰዎችም ወደ ቤተ መቅደሳችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብተዋልና ውርደት ፊታችንን ከድኖታል። 52 ስለዚህ እነሆ የተቀረጹትን ምስሎችዋን የምበቀልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በምድርዋም ሁሉ የተገደሉት ይወድቃሉ። 53 ባቢሎንም ወደ ሰማይ ብትወጣ፥ ቅፅሮችዋንም በኀይልዋ ብታጸና፥ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል፥ ይላል እግዚአብሔር። 54 “ከባቢሎን የጩኸት ድምፅ፥ ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰምቶአል። 55 እግዚአብሔር ባቢሎንን አጥፍቶአታልና፥ ከእርስዋም ሞገዱ እንደ ብዙ ውኃዎች የሚተመውን ታላቁን ድምፅ ዝም አሰኝቶአልና፤ የድምፃቸው ጩኸት ተሰምቶአል። 56 ጥፋት በባቢሎን ላይ መጥቶባታልና፥ ተዋጊዎችዋ ተያዙ፤ ቀስታቸውም ተሰባበረ፤ እግዚአብሔር ተበቅሎአቸዋልና፥ እግዚአብሔርም ፍዳን ከፍሎአቸዋልና። 57 መሳፍንቶችዋንና ጥበበኞችዋንም፥ አለቆችዋንና ሹሞችዋን፥ ኀያላኖችዋንም አሰክራለሁ፤ ለዘለዓለምም አንቀላፍተው አይነቁም ይላል ስሙ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ። 58 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰፊው የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል፤ ረጃጅሞች በሮችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፤ ሕዝቡ ለከንቱ ይደክማሉ፤ አሕዛብም በመጀመሪያ በእሳት ያልቃሉ።” ነቢዩ ኤርምያስ ወደ ባቢሎን መልእክት እንደ ላከ 59 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ከእርሱ ዘንድ ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ ለማሴው ልጅ ለኔርዩ ልጅ ለሠራያ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘው ቃል ይህ ነው። 60 ሠራያም የቤቱ አዛዥ ነበረ፤ በባቢሎንም ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ ኤርምያስ በአንድ መጽሐፍ ላይ ጻፈው። 61 ኤርምያስም ሠራያን እንዲህ አለው፥ “ወደ ባቢሎን በገባህ ጊዜ እይ፤ ይህንም ቃል ሁሉ አንብብና፦ 62 አቤቱ! ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት፥ ለዘለዓለምም ባድማ እንድትሆን ታጠፋት ዘንድ በዚች ስፍራ ላይ ተናግረሃል በል። 63 ይህንም መጽሐፍ ማንበብ ከፈጸምህ በኋላ፥ ድንጋይን እሰርበት፤ በኤፍራጥስም ወንዝ ውስጥ ጣለው። 64 አንተም፦ እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች፤ አትነሣምም በል።” የኤርምያስ ቃል እስከዚህ ድረስ ነው። |