ኢሳይያስ 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በባቢሎን፥ በኤዶምያስና በዐረቢያ የተነገረ ትንቢት 1 ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ቃል፤ ዐውሎ ነፋስ በምድረ በዳ እንደሚያልፍ፥ እንዲሁ ከሚያስፈራ ሀገር ከምድረ በዳ ይመጣል። 2 ከባድ ራእይ ተነገረኝ፤ ወንጀለኛው ይወነጅላል፤ በደለኛውም ይበድላል። የኤላም ሰዎችና የሜዶን መልእክተኛ በእኔ ላይ ይመጣሉ። ዛሬ ግን እጨነቃለሁ፤ እረጋጋለሁም። 3 ስለዚህም ወገቤ ሕማም ተሞላ፤ እንደምትወልድ ሴትም ምጥ ያዘኝ፤ ከሕማሜ የተነሣ አልሰማም፤ ከድንጋጤም የተነሣ አላይም። 4 ልቤ ሳተ፤ ኀጢአቴም አሰጠመኝ፤ ሰውነቴም ደነገጠብኝ። 5 ማዕዱን አዘጋጁ፤ ብሉ፤ ጠጡ፤ እናንተ አለቆች ሆይ፥ ተነሡ፤ ጋሻውንም አዘጋጁ። 6 እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛልና፥ “ፈጥነህ ሂድ፤ ጕበኛንም አቁም፤ የሚያየውንም ይናገር፤ የሚሰማውንም ያውራ። 7 ሁለት ፈረሰኞችን ሲጋልቡ አየሁ፤ አንዱ በአህያ ላይ፥ ሁለተኛውም በግመል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ድምፃቸው ግን እንደ ብዙዎች ፈረሰኞች ድምፅ ነበረ።” 8 የእግዚአብሔር ጕበኛ ኦርያስ ተጠራ፤ እርሱም፥ “እነሆ እኔ አለሁ፤ መላ መዓልቱንና መላ ሌሊቱን በማማ ላይ ቆሜ አለሁ። 9 እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሆነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ” ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ፥ “ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! ጣዖቶችዋም ሁሉ፥ የእጆችዋም ሥራዎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ” አለ። 10 እናንተ የተረፋችሁና መከራ የምትቀበሉ ሆይ፥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የነገረኝንና የሰማሁትን ስሙ። 11 ስለ ኤዶምያስ የተነገረ ነገር። አንዱ ከሴይር፥ “ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው?” ብሎ ጠራኝ። 12 ጕበኛውም፥ “ይነጋል፤ ደግሞም ይመሻል፤ ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ፥” አለ። 13 ሌሊትም በዲዳናውያን ጎዳና በዛፎች ውስጥ ታድራለህ፤ 14 በቴማን የምትኖሩ ሆይ፥ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ፤ 15 እንጀራ ይዛችሁ ከሰልፍ ከሸሹ ከብዙ ሰዎችና በጦር ከጠፉ ከብዙ ሰዎች፥ ፍላጻ ከያዙ ከብዙ ሰዎችና ጦር ከያዙ ከብዙ ሰዎች፥ ቀስቶቻቸው ከተሳቡና በሰልፍ ከወደቁ ከብዙ ሰዎች ያመለጡትን ተቀበሏቸው። 16 እግዚአብሔር እንደ ገና እንዲህ ብሎኛልና፥ “እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ልጆች ክብር ሁሉ ይጠፋል፤ 17 ከቀስተኞች ቍጥር የቀሩት፥ የቄዳር ልጆች ኀያላን፥ ያንሳሉ፤” የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና። |