ኢሳይያስ 60 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የወደፊቱ የኢየሩሳሌም ክብር 1 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ብርሃን በአንቺ ላይ ወጥቶአልና አብሪ፤ አብሪ። 2 እነሆ፥ ጨለማ ምድርን፥ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይገለጣል፤ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ 3 ነገሥታት በብርሃንሽ፥ አሕዛብም በፀዳልሽ ይሄዳሉ። 4 ዐይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ ልጆችሽም እንደ ተሰበሰቡ እነሆ፥ እዪ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፤ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል። 5 በዚያ ጊዜ አይተሽ ትፈሪያለሽ፤ የአሕዛብና የሀገሮች ብልጽግና ወደ አንቺ ይመለሳልና፥ ልብሽ ይደነግጣል። 6 የግመሎች መንጋ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የምድያምና የኤፋ ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ወርቅንና ዕጣንን ይዘው ይመጣሉ፤ የእግዚአብሔርንም ማዳን ያበሥራሉ። 7 የቄዳር በጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ፤ የነባዮትም አውራ በጎች ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ በመሠዊያዬ ላይም የተመረጠው መሥዋዕት ይቀርባል፤ የጸሎቴ ቤትም ይከብራል። 8 እንደ ደመና፥ ከጫጩቶችዋ ጋር ወደ መስኮቷ እንደምትገባ ርግብም የሚበርሩ እነዚህ እነማን ናቸው? 9 ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤ የተርሴስም መርከቦች አስቀድመው ይመጣሉ፤ ልጆችሽ ስለ ከበረው ስለ እስራኤል ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ስም ወርቅና ብር ይዘው ከሩቅ ሀገር ይመጣሉ። 10 በቍጣዬ ቀሥፌ በይቅርታዬ አቅርቤሻለሁና መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም በፊትሽ ይቆማሉ። 11 በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጽግና፥ የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ ሌሊትና ቀን አይዘጉም። 12 ለአንቺም የማይገዙ ነገሥታት ይሞታሉ፤ እነዚያም አሕዛብ ፈጽመው ይጠፋሉ። 13 የመቅደሴንም ስፍራ ያከብሩ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው፥ ባርሰነቱም ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ 14 የአስጨናቂዎችሽም ልጆች እየተንቀጠቀጡ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእስራኤል ቅዱስ የእግዚአብሔር ከተማ፥ ጽዮን ተብለሽም ትጠሪያለሽ። 15 የተተውሽና የተጠላሽ ሆነሻልና የሚረዳሽ አጣሽ፤ ነገር ግን የዘለዓለም ደስታን ለልጅ ልጅ እሰጥሻለሁ። 16 የአሕዛብንም ወተት ትጠጫለሽ፤ የነገሥታትንም ብልጽግና ትበያለሽ፤ እኔም እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ፥ መድኀኒትሽና ታዳጊሽ እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ። 17 በናስ ፋንታ ወርቅን፥ በብረትም ፋንታ ብርን፥ በእንጨትም ፋንታ ናስን፥ በድንጋይም ፋንታ ብረትን እሰጥሻለሁ። ለአለቆችሽም ሰላምን፥ ለመኳንንትሽም ፍርድን አደርጋለሁ፤ 18 እንግዲህ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥሮችሽ ድኅነት ይባላሉ፤ በሮችሽም በጥርብ ድንጋይ ይሠራሉ። 19 ፀሐይ በቀን የሚያበራልሽ አይደለም፤ በሌሊትም ጨረቃ የሚወጣልሽ አይደለም፤ ለአንቺስ እግዚአብሔር የዘለዓለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽ ይሆናል። 20 እግዚአብሔር የዘለዓለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ያልፋልና፤ ፀሐይሽ ከዚህ በኋላ አትጠልቅም፤ ጨረቃሽም አይቋረጥም። 21 ሕዝብሽ ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ ምድርንም ለዘለዓለም ይወርሳሉ፤ እርሱንም ለማመስገን የእጆቹን ሥራ ይጠብቃሉ። 22 ታናሹ ሺህ፥ የሁሉም ታናሽ ታላቅ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመናቸው ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ። |