መዝሙር 143 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጎልያድ የዳዊት መዝሙር። 1 ለእጆቼ ጠብን፥ ለጣቶቼም ሰልፍን ያስተማራቸው አምላኬ እግዚአብሔር ይመስገን፤ 2 የሚምረኝ፥ መሸሸጊያዬ፥ መጠጊያዬና አዳኜ፤ መታመኛዬም፤ እርሱን ታመንሁ፤ ሕዝቡንም ከእኔ በታች የሚያስገዛልኝ። 3 አቤቱ፥ ለእርሱ ትገለጥለት ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ታስበው ዘንድስ የሰው ልጅ ምንድን ነው? 4 ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል፤ ዘመኑም እንደ ጥላ ያልፋል። 5 አቤቱ፥ ሰማዮችህን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው፥ ውረድም፤ ተራሮችን ዳስሳቸው፥ ይጢሱም። 6 መብረቆችህን ብልጭ አድርጋቸው፥ በትናቸውም፤ ፍላጾችህን ላካቸው፥ አስደንግጣቸውም። 7 እጅህን ከአርያም ላክ፥ ከብዙ ውኃም አድነኝ፤ ከባዕድ ልጆችም እጅ፥ 8 አፋቸው ከንቱ ነገርን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የዐመፃ ቀኝ ከሆነ አስጥለኝ። 9 አቤቱ፥ በአዲስ ምስጋና አመሰግንሃለሁ፤ ዐሥር አውታር ባለው በገናም እዘምርልሃለሁ። 10 ለነገሥታት መድኀኒትን የሚሰጥ፥ ባሪያው ዳዊትን ከክፉ ጦር የሚያድነው እርሱ ነው። 11 አፋቸውም ከንቱ ነገርን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የዐመፃ ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አድነኝ፥ አስጥለኝም። 12 ልጆቻቸው በጐልማስነታቸው እንደ አዲስ ተክል የሆኑ፥ ሴቶች ልጆቻቸውም እንደ እልፍኝ ያማሩና ያጌጡ፤ 13 ዕቃ ቤቶቻቸውም በያይነቱ ዕቃ የተሞሉ ናቸው፥ በጎቻቸውም ብዙ የሚወልዱ፥ በመሰማርያቸውም የሚበዙ፥ 14 ላሞቻቸውም የሰቡ፤ ለቅጥራቸውም መፍረስ የሌለው፥ የሚገባባቸውም የሌለ፥ በአደባባዮቻቸውም ዋይታ የሌለባቸው፤ 15 እንደዚህ ያለውን ሕዝብ አመስግኑት፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ብፁዕ ነው። |