ኢሳይያስ 44 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ 1 አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ። 2 የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፥ “ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ወዳጄ እስራኤል ሆይ፥ አትፍራ። 3 በደረቅ መሬት ላይ ለሚሄድና ለተጠማ ውኃን እሰጣለሁ፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ፥ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አኖራለሁ፤ 4 በውኃ መካከል እንዳለ ቄጠማ በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች ይበቅላሉ። 5 ይህ፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፤ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል፤ በእስራኤልም ስም ይጠራል።” 6 የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እንዲህ ይላል፥ “እኔ ፊተኛ ነኝ፤ እኔም ኋለኛ ነኝ፤ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። 7 እንደ እኔ ያለ አዳኝ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ፤ ይናገርም፤ ሰውን ከፈጠርሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ የሚሆነውን ያዘጋጅልኝ፤ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይናገር። 8 ራሳችሁን አትደብቁ፤ ከጥንት ጀምሮ አልሰማችሁምን? አልነገርኋችሁምን? ከእኔ ሌላ አምላክ እንደ ሌለ ምስክሮች ናችሁ።” ስለ ጣዖት አምልኮ ከንቱነት 9 ጣዖታትን የሚቀርጹ ያንጊዜ አይኖሩም፤ የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩም ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፤ የማይረባቸውን የራሳቸውን ፍላጎት የሚያደርጉ ሁሉ ያፍራሉ። 10 ጣዖታትን የሚሠሩ፥ የማይጠቅማቸውን ምስል የሚቀርጹና በእነርሱም የተሠሩ ሁሉ ይደርቃሉ። 11 ከሰዎች መካከል ደንቆሮዎች ሁሉ ይሰብሰቡ፤ በአንድነትም ይቁሙ፤ በአንድነትም ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም። 12 ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይስላል፤ ጣዖቱን በመጥረቢያ ይቀርጸዋል፤ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል፤ በክንዱም ኀይል ይሠራዋል፤ እርሱም ይራባል፤ ይደክምማል፤ ውኃም አይጠጣም። 13 ጠራቢውም እንጨት ቈርጦ በልኩ ያቆመዋል፤ በማጣበቂያም ያያይዘዋል፤ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል፤ በቤትም ውስጥ ያቆመዋል። 14 እግዚአብሔር ያበቀለውን፥ በዝናምም ያሳደገውን ዛፍ ከዱር ይቈርጣል። 15 ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፤ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም የተረፈውን ጣዖታትን አበጅቶ ይሰግድላቸዋል። 16 ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፤ በዚያም በግማሹ ሥጋ ይጠብሳል፤ ጥብሱንም ይበላና ይጠግባል፤ ይሞቃልና፥ “እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ” ይላል። 17 የቀረውንም እንጨት ጣዖት አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግዳል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፥ “አምላኬ ነህና አድነኝ” ይላል። 18 አያውቁም፤ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸው፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸው ተጋርደዋል። 19 ማንም በልቡ አያስብም፥ “ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፤ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፤ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም ዕውቀትና ማስተዋል የለውም። 20 እንግዲህ ልባቸው አመድ እንደ ሆነና እንደ በደሉ፥ ከእነርሱም ነፍሱን ለማዳን የሚችል ማንም እንደሌለ ዕወቁ፤ በቀኝ እጄ ሐሰት አለ” የሚልም እንደሌለ ተመልከቱ። የእግዚአብሔር አዳኝነት 21 ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ አገልጋዬ ነህና ይህን ዐስብ፤ እኔ ፈጥሬሃለሁ፤ አንተም ባሪያዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ አትርሳኝ። 22 መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኀጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥችሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ። 23 እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ምሕረትን አድርጎአልና ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና የምድር መሠረቶች መለከትን ይንፉ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በውስጣቸው ያሉ ዛፎች ሁሉ፥ እልል ይበሉ። 24 ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሁሉን ለብቻዬ የፈጠርሁ፥ ሰማያትን የዘረጋሁ፥ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ 25 በሟርት ሙት እናስነሣለን የሚሉትን፥ ከልባቸውም አንቅተው ሐሰት የሚናገሩትን ሰዎች ምልክት የሚለውጥ ማን ነው? ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ ይመልሳል፤ ምክራቸውንም ስንፍና ያደርጋል። 26 የባርያውን ቃል ያጸናል፤ የመልእክተኞቹንም ምክር ይፈጽማል። ኢየሩሳሌምን፦ የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፤ የይሁዳንም ከተሞች ትታነጻላችሁ፤ ምድረ በዳዎችዋም ይለመልማሉ፤” ይላል፤ 27 ቀላይዋንም፥ “ደረቅ ሁኚ ፈሳሾችሽም ይድረቁ” ይላል፤ 28 ቂሮስንም፥ “ብልህ ሁን፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን፦ ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስንም እመሠርታለሁ ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል” ይላል። |