ኤርምያስ 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ኤርምያስ ሕይወት የእግዚአብሔር ፈቃድ 1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም አትውለድ። 3 እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ስለ ተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ ስለ ወለዱአቸውም ስለ እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር ስለ ወለዱአቸው ስለ አባቶቻቸው እንዲህ ይላልና፦ 4 “በክፉ ሞት ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ አይቀበሩምም፤ ነገር ግን በመሬት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ፤ በሰይፍም ይወድቃሉ፤ በራብም ይጠፋሉ፤ ሬሳዎቻቸውም ለሰማይ ወፎችና ለዱር አራዊት መብል ይሆናሉ።” 5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰላሜን፥ ቸርነቴንና ምሕረቴን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ ታለቅስና ታዝንም ዘንድ አትሂድ። 6 ታላላቆችና ታናናሾች በዚች ምድር ይሞታሉ ፥ አይቀበሩም ሰዎችም አያለቅሱላቸውም፤ ስለ እነርሱም ፊት አይነጩላቸውም፤ ራስንም አይላጩላቸውም፤ 7 ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የእዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፤ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። 8 ትበላና ትጠጣ ዘንድ ከእነርሱ ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ።” 9 ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በዐይናችሁ ፊት በዘመናችሁም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ። 10 “ለዚህም ሕዝብ ይህን ቃል ሁሉ በተናገርህ ጊዜ፦ ይህን ሁሉ ትልቅ የሆነ ክፉ ነገርን ስለ ምን እግዚአብሔር ተናገረብን? በደላችንስ ምንድን ነው? በአምላካችንስ በእግዚአብሔር ፊት ያደረግነው ኀጢአት ምንድን ነው? ቢሉህ፥ 11 አንተ እንዲህ ትላቸዋለህ፦ አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተዉ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ፤ አመለኩአቸውም፤ ሰገዱላቸውም፤ እነርሱም ትተውኛል፤ ሕጌንም አልጠበቁም፤ 12 እናንተም ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፤ እነሆም ሁላችሁ እንደ ክፉ ልባችሁ ፍላጎት ሄዳችኋል፤ እኔንም አልሰማችሁም። 13 ስለዚህ ከዚች ምድር እናንተና አባቶቻችሁ ወደ አላወቃችኋት ምድር እጥላችኋለሁ፤ በዚያም ምሕረትን ለማያደርጉላችሁ ሌሎች አማልክት ቀንና ሌሊት ታገለግላላችሁ።” ከምርኮ ስለ መመለስ 14 ስለዚህ እነሆ፥ “የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር፤ 15 ነገር ግን፥ “የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር፥ ከተሰደዱበትም ምድር ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ። ስለሚመጣው ቅጣት 16 “እነሆ፥ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እልካለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ያጠምዱአቸዋል፤ ከዚያም በኋላ ብዙ አድዳኞችን እልካለሁ፤ እነርሱም ከየተራራውና ከየኮረብታው ሁሉ ከየድንጋዩም ስንጣቂ ውስጥ ያድድኑአቸዋል። 17 ዐይኖች በመንገዳቸው ሁሉ ይመለከታሉ፤ ከፊቴም አልተሰወሩም፤ ኀጢአታቸውም ከዐይኖች አልተሸሸገም። 18 ምድሬንም በተጠሉ በጣዖቶቻቸው ሬሳዎች አርክሰዋልና፥ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና አስቀድሜ የበደላቸውንና የኀጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ።” የኤርምያስ ጸሎት 19 ጌታ ሆይ! አንተ ኀይሌና ረዳቴ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ ነህ፤ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው፥ “በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር ለምንም የማይረባቸውን ጣዖትን ሠርተዋል” ይላሉ። 20 በውኑ ሰው አማልክት ያልሆኑትን ለራሱ አማልክትን አድርጎ ይሠራልን? 21 “ስለዚህ እነሆ በዚህ ወራት አስታውቃቸዋለሁ፤ እጄንና ኀይሌንም አሳያቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቃሉ።” |