ኢሳይያስ 56 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አሕዛብ ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሚሆኑ 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ማዳኔ ሊመጣ ምሕረቴም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን ጠብቁ፤ ጽድቅንም አድርጉ። 2 ይህን የሚያደርግ በእርሱም ጸንቶ የሚኖር፥ ሰንበታትንም የሚጠብቅና የማያረክስ፥ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ሰው ብፁዕ ነው።” 3 ወደ እግዚአብሔርም የተጠጋ መጻተኛ፥ “በእውነት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ይለየኛል” አይበል፤ ጃንደረባም፥ “እነሆ፥ እኔ እንደ ደረቀ ዛፍ ነኝ” አይበል። 4 እግዚአብሔር ለጃንደረቦች እንዲህ ይላል፥ “ሰንበቴን ቢጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ቢመርጡ፥ በቃል ኪዳኔም ጸንተው ቢኖሩ፥ 5 በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምንም እሰጣቸዋለሁ።” 6 ከሌላም ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን ለእርሱም ባሪያዎች የሆኑትን፥ የእግዚአብሔርንም ስም የወደዱትን፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቹ የሆኑትን፥ “ሰንበታቴን የሚጠብቁትንና የማያረክሱትን፥ በቃል ኪዳኔም ጸንተው የሚኖሩትን ሁሉ፥ 7 ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና፥ የሚቃጠለው መሥዋዕታቸውና ቍርባናቸውም በመሠዊያዬ ላይ የተመረጠ ይሆናል። 8 ከእስራኤል የተበተኑትን የሚሰበስብ ጌታ እግዚአብሔር፦ ወደ ተሰበሰቡት ሌሎችን እሰበስብለታለሁ” ይላል። 9 እናንተ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ ኑ፤ እናንተ የዱር አራዊት ሁሉ ብሉ። 10 ሁሉም ዕውራን እንደ ሆኑ ኑና እዩ፤ ሁሉ ያለ ዕውቀት ናቸው፤ ሁሉም ዲዳ የሆኑ ውሾች ናቸው፤ ይጮኹም ዘንድ አይችሉም፤ በመኝታቸውም ሕልምን ያልማሉ፤ ማንቀላፋትንም ይወድዳሉ። 11 ሁሉም ከቶ የማይጠግቡ የረከሱ ውሾች ናቸው፤ እነርሱም ያስተውሉ ዘንድ የማይችሉ ክፉዎች ናቸው፤ ሁሉም እያንዳንዳቸው እንደ ፈቃዳቸው መንገዳቸውን ተከትለዋል። 12 ኑ፤ የወይን ጠጅ እንውሰድ፤ በሚያሰክርም መጠጥ እንርካ፤ ዛሬም እንደ ሆነ እንዲሁ ነገ ይሆናል፤ ከዛሬም ይልቅ እጅግ ይበልጣል ይላሉ። |