ኤርምያስ 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤርምያስ በባቢሎን ለሚኖሩ አይሁድ የላከው ደብዳቤ 1 ነቢዩ ኤርምያስ ወደ ተረፉት የምርኮ ሽማግሌዎች፥ ወደ ካህናቱም፥ ወደ ሐሰተኞች ነቢያቱም፥ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ወዳፈለሰውም ሕዝብ ሁሉ ከኢየሩሳሌም የላከው የደብዳቤው ቃል ይህ ነው። 2 ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያንና እቴጌዪቱ፥ ጃንደረቦቹም፥ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም አለቆች ነጻዎችና እሥረኞች፥ ብልሃተኞችና ብረት ሠራተኞችም ከኢየሩሳሌም ከወጡ በኋላ ነው። 3 ኤርምያስም የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን በላካቸው በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ደብዳቤውን እንዲህ ሲል ላከው፦ 4 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረክኋቸው ምርኮኞች ሁሉ እንዲህ ይላል፦ 5 “ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አታክልትም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ፤ ተጋቡ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ውለዱ፤ 6 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁንም አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ከዚያም ተባዙ፤ ጥቂቶችም አትሁኑ። 7 በእርስዋ ሰላም፥ ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማረክኋችሁ ሀገር ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ።” 8 የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “በመካከላችሁ ያሉት የሐሰት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፤ ሕልም አላሚዎች አለምንላችሁ የሚሉአችሁን አትስሙ፥ 9 በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና፤ እኔም አልላክኋቸውም፥” ይላል እግዚአብሔር። 10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። 11 ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። 12 እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። 13 እናንተ ትሹኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። 14 እገለጥላችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፤ ከአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እናንተንም ከበተንሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ። 15 “እናንተም፦ እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል ብላችኋልና፤ 16 እግዚአብሔር በዳዊት ዙፋን ስለ ተቀመጠ ንጉሥ፥ ከእናንተም ጋር ስላልተማረኩት ወንድሞቻችሁ፥ በዚህች ከተማ ስለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ይላልና፦ 17 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሰይፍንና ራብን፥ ቸነፈርንም እሰድድባቸዋለሁ፤ ከመጐምዘዙም የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉ በለስ አደርጋቸዋለሁ። 18 በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም አሳድዳቸዋለሁ፤ ባሳደድሁባቸውም አሕዛብ ሁሉ ዘንድ ለርግማንና ለጥፋት፥ ለማፍዋጫም፥ ለመሰደቢያም እንዲሆኑ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 19 ይህም የሆነው ቃሌን ስላልሰሙ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በማለዳ ባሪያዎችን ነቢያትን ወደ እነርሱ ሰድጃለሁና፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም፤ ይላል እግዚአብሔር። 20 ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።” 21 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚናገሩላችሁ ስለ ቆልያ ልጅ፥ ስለ አክዓብና ሰለ ማሴው ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል፥ “እነሆ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ በዐይኖቻችሁም ፊት ይገድላቸዋል። 22 ከእነርሱም የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፦ የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ እግዚአብሔር ያድርግህ የምትባል ርግማንን ያነሣሉ፤ 23 በእስራኤል ዘንድ ክፉ አድርገዋልና፥ ከባልንጀሮቻቸውም ሚስቶች ጋር አመንዝረዋልና፥ ያላዘዝኋቸውንም ቃል በስሜ በሐሰት ተናግረዋልና። እኔም አውቃለሁ፤ ምስክርም ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።” 24 ለአሔልማዊው ለሸማያ እንዲህ በል፦ 25 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌም ወደ አለው ሕዝብ ሁሉ፥ ወደ ካህኑም ወደ ማሴው ልጅ ወደ ሶፎንያስ፥ ወደ ካህናቱም ሁሉ ደብዳቤዎችን በስሜ እንዲህ ስትል ልከሃል፦ 26 ትንቢት የሚናገረውን ሰው ሁሉ፥ የሚለፈልፈውንም ሰው ሁሉ በግዞት ታኖረውና በፈሳሽም ታሰጥመው ዘንድ በእግዚአብሔር ቤት አለቃ እንድትሆን እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ፋንታ ካህን አድርጎሃል። 27 አሁንስ ትንቢት ተናጋሪውን የአናቶቱን ሰው ኤርምያስን ስለ ምን አትዘልፈውም? 28 እርሱ፦ ምርኮው የረዘመ ነውና ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አታክልትም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ ብሎ ወደ እኛ ወደ ባቢሎን ልኮአልና።” 29 ካህኑም ሶፎንያስ ይህን ደብዳቤ በነቢዩ በኤርምያስ ጆሮ አነበበው። 30 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 31 “እግዚአብሔር ስለ አሔልማዊው ስለ ሸማያ እንዲህ ይላል ብለህ ወደ ምርኮኞች ሁሉ ላክ፦ እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችኋልና፥ በሐሰትም እንድትታመኑ አድርጓችኋልና። 32 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሔልማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ እኔም ለሕዝቤ የማደርገውን መልካሙን ነገር የሚያይ ሰው በመካከላችሁ አይኖርላቸውም፤ ይላል እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ላይ ዐመፃን ተናግሮአልና።” |