ኢሳይያስ 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ እስራኤል ሕዝብ ከስደት መመለስ 1 እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፤ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፤ በሀገራቸውም ያርፋሉ፤ መጻተኞችም ከእነርሱ ጋር አንድ ይሆናሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጨመራሉ። 2 አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል፤ የእስራኤልም ወገኖች ይካፈሏቸዋል፤ በዚያም ሀገር ይበዛሉ፤ በዚያም ወንዶች ባሮችና ሴቶች ባሮች ይሆናሉ። ማርከው የወሰዷቸውም ለእነርሱ ምርኮኞች ይሆናሉ፤ የገዙአቸውም ይገዙላቸዋል። 3 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከኀዘንህና ከመከራህ፥ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል። 4 ይህንም ሙሾ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ፤ እንዲህም ትላለህ፥ “አስጨናቂ እንዴት ዐረፈ! አስገባሪም እንዴት ጸጥ አለ! 5 እግዚአብሔር የኀጢአተኞችን ቀንበርና የአለቆችን ቀንበር ሰብሮአልና። 6 እግዚአብሔር በቍጣው መቅሠፍት አሕዛብን ገርፎአቸዋልና፥ ከቍጣውም መቅሠፍት አልራራላቸውምና። 7 ምድርም ሁሉ ዐርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች፤ እልልም ብላለች። 8 የሊባኖስ ዛፎች፦ አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው። 9 “ሲኦልም በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የአሕዛብን ነገሥታት ሁሉ ከዙፋናቸው ያስነሡ፥ ምድርን የገዙአት አርበኞች ሁሉ በአንድነት በአንተ ላይ ተነሡ። 10 እነዚህ ሁሉ፦ አንተ ደግሞ እንደ እኛ ተይዘሃል፤ እንደ እኛም ተቈጥረሃል። 11 ከክብርህ ወደ ሲኦል ወደቅህ፤ በበታችህም ብል ተነጥፎአል፤ ትልም መደረቢያህ ሆኖአል” ብለው ይመልሱልሃል። 12 “አንተ በንጋት የሚወጣ የአጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! ወደ አሕዛብም መልእክትን የላክህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቀጠቀጥህ! 13 አንተም በልብህ፦ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤ ዙፋኔንም ከሰማይ ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤ በሰሜንም ዳርቻ በረዣዥም ተራሮች ላይ እቀመጣለሁ፤ 14 ከደመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። 15 ዛሬ ግን ወደ ሲኦል ትወድቃለህ፤ ወደ ምድር ጥልቅም ትወርዳለህ። 16 የሚመለከቱህም ይደነቃሉ፤ እንዲህም ይላሉ፦ በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትንም ያናወጠ፥ 17 ዓለሙን ሁሉ ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ፥ ምርኮኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልሰደደ ሰው ይህ ነውን? 18 “የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል። 19 አንተ ግን በጦር ተወግተው ወደ መቃብር ከሚወርዱ ብዙ ሙታን ጋር እንደ ረከሰ ሬሳ በተራሮች ላይ ትጣላለህ። 20 ንጹሕ እንዳልሆነና በደም እንደ ረከሰ ልብስ አንተም ንጹሕ አይደለህም። ምድሬን አጥፍተሃልና፥ ሕዝቤንም ገድለሃልና ክፉ ዘር አንተ እንግዲህ ለዘለዓለም አትኖርም። 21 እንዳይነሡም፥ ምድርንም እንዳይወርሱ፥ የዓለሙንም ፊት በጦርነት እንዳይሞሉ በአባቶቻቸው በደል ይገድሉአቸው ዘንድ ልጆችህን አዘጋጅ።” 22 “በእነርሱ ላይ እነሣለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ “ስምንና ቅሬታን፥ ዘርንና ትውልድንም አጠፋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። 23 “ባቢሎንን የወፎች መኖሪያ አደርጋታለሁ፤ እንደ ኢምንትም ትሆናለች፤ በጥፋትም እንደ ረግረግ ጭቃ አደርጋታለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። በአሦር ላይ የተነገረ ትንቢት 24 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል፥ “እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፤ እንደ መከርሁም እንዲሁ ይጸናል። 25 አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፤ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሣል፤ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል።” 26 በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው ዐሳብ ይህ ነው፤ በአሕዛብም ሁሉ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት። 27 ቅዱስ እግዚአብሔር ይህን መክሮአል፤ የእግዚአብሔርን ምክር የሚመልስ ማን ነው? የተዘረጋች እጁንስ የሚመልሳት ማን ነው? በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት 28 ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት ይህ ነገር ሆነ። 29 ፍልስጥኤም ሆይ፥ ከእባቡ ዘር እፉኝት ይወጣልና፥ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና፥ የኀይላችሁ ቀንበር ተሰብሮአልና ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ። 30 ድሆችም በውስጣችሁ ይሰማራሉ፤ ድሆች ሰዎችም በሰላም ያርፋሉ፤ ዘራችሁንም ረኃብ ያጠፋቸዋል፤ ከእናንተም የቀሩት ያልቃሉ። 31 እናንተ የከተሞች በሮች ሆይ፥ ወዮ በሉ፤ እናንተም ከተሞች ሆይ፥ ደንግጡ፥ ጩኹም፤ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይወጣልና፥ እንግዲህም አትኖሩምና። 32 የአሕዛብ ነገሥታት ምን ይመልሳሉ? እግዚአብሔር ጽዮንን መሠረታት፤ ትሑታን የሆኑትንም ሕዝብ አዳናቸው። |