እግዚአብሔር ታላቅና የሚያስፈራ ነው፤ ምስጋናም ሁሉ ለእርሱ ይገባዋል። በእርሱ ፊት ተራሮች ይንቀጠቀጣሉ፤ ማንም አመፀኛ ከቅጣት አያመልጥም።
የዘላለም ስሙ ጽኑ ነው፤ የማይወዳደር ኃይል አለው። ስለዚህ በውስጥህ ያለውን ጠማማ ነገር አቅና። በልብህ ክፋት ካለ ከእግዚአብሔር ይቅርታን ፈልግ፤ እርሱ ጻድቅና መሐሪ ነውና።
ቃሉንና ፈቃዱን አትፈታተን፤ በተቃራኒው ብትሰራ በምድር ላይ አትለመልምም። ዛሬ ከእርሱ ጋር የምትታረቅበት፣ ልብህን የምትከፍትበትና በእርሱ ፊት የምትዋረድበት ቀን ነው፤ ትሑት ልብ በእርሱ ዘንድ አይጣልምና።
በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፤ በራስህ አስተሳሰብ አትታበይ፤ ይልቁንም በእግዚአብሔር ታመን፤ በምንም ነገር አትኩራራ፤ አለበለዚያ ነፍስህ ትበላሻለች፤ የፈጠረህንና ሕይወትን የሰጠህን ትቃወማለህ።
የእግዚአብሔር መንገዶች ፍጹማን ናቸው፤ ወደ ዘላለም ሕይወትም ይመራሉ፤ የሰው መንገዶች ግን ጠማማዎች ናቸው፤ ወደ ሞትም ያደርሳሉ።
ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።
ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።”
ከግብጽ ባወጣችሁና ከባርነት ምድር በዋጃችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ላይ እንድታምፁ ተናግሯልና፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንድትከተሉት ካዘዛችሁ መንገድ እንድትመለሱ አድርጓልና፣ ያ ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ይገደል፤ ስለዚህ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።
እግዚአብሔርን የምትፈሩና የምታመልኩ፣ የምትታዘዙትና በትእዛዞቹ ላይ የማታምፁ ከሆነ፣ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ከተከተላችሁ መልካም ይሆንላችኋል።
እግዚአብሔርን የማትታዘዙና በትእዛዞቹም ላይ የምታምፁ ከሆነ ግን፣ እጁ በአባቶቻችሁ ላይ እንደ ነበረች ሁሉ በእናንተም ላይ ትሆናለች።
“ለዐመፀኞች ልጆች ወዮላቸው!” ይላል እግዚአብሔር፤ “የእኔ ያልሆነውን ሐሳብ ይከተላሉ፤ ከመንፈሴ ያልሆነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤ በኀጢአት ላይ ኀጢአት ይጨምራሉ።
ብቻ በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሯቸው። ጥላቸው ተገፍፏል፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋራ ነውና አትፍሯቸው።”
አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቈጣኸው አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ። ከግብጽ ከወጣህበት ዕለት አንሥቶ እዚህ ቦታ እስከ ደረስህበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅህ ነህ።
“ወጥተውም በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤ የሚበሏቸው ትሎች አይሞቱም፤ የሚያቃጥላቸው እሳታቸው አይጠፋም፤ ለሰውም ዘር ሁሉ አስጸያፊ ይሆናሉ።”
ክፋትሽ ቅጣት ያስከትልብሻል፤ ክሕደትሽም ተግሣጽ ያመጣብሻል፤ እግዚአብሔር አምላክሽን ስትተዪ፣ እኔንም መፍራት ችላ ስትይ፣ ምን ያህል ክፉና መራራ እንደሚሆንብሽ አስቢ፤ እስኪ አስተውዪ፤” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤ እኔ ግን በትእዛዙ ላይ ዐመፅ አድርጌ ነበር፤ እናንተ ሕዝቦች ሁሉ ስሙ፤ መከራዬንም ተመልከቱ፤ ወይዛዝርቶቼና ጐበዛዝቴ፣ ተማርከው ሄደዋል።
የሰማርያ ሰዎች በደላቸውን ይሸከማሉ፤ በአምላካቸው ላይ ዐምፀዋልና። በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ሕፃኖቻቸውም በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤ የእርጉዝ ሴቶቻቸውም ሆድ ይቀደዳል።”
የቱን ያህል ዐመፀኞችና ዐንገተ ደንዳኖች እንደ ሆናችሁ ዐውቃለሁና። እኔ በሕይወት ከእናንተ ጋራ እያለሁ በእግዚአብሔር ላይ ካመፃችሁ፣ ከሞትሁ በኋላማ የቱን ያህል ልታምፁ!
በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅሽ፣ ክብርሽንም ለእንግዶች አማልክት፣ በየለምለሙ ዛፍ ሥር አሳልፈሽ በመስጠት፣ ለእኔ ባለመታዘዝሽ፣ በደለኛ መሆንሽን ይህን አንድ ነገር ብቻ እመኚ’ ” ይላል እግዚአብሔር።
ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።”
“ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብጽንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብጽ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር።
በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀናል፤ ሐሰት ተናግረናል፤ አምላካችንን ከመከተል ዘወር ብለናል፤ ዐመፃንና ግፍን አውርተናል፤ ልባችን የፀነሰውን ውሸት ተናግረናል።
“ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር።
እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእኔ ላይ ወደ ዐመፀው፣ ወደ ዐመፀኞቹ የእስራኤል ልጆች እልክሃለሁ፤ እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐምፀውብኛል።
ለዐመፀኛ ሕዝብ፣ መልካም ባልሆኑ መንገዶች ለሚሄዱ፣ የልባቸውን ምኞት ለሚከተሉ፣ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ። ዘወትር በፊቴ የሚያስቈጡኝ ሕዝቦች፣
“ነገር ግን እንቢተኞች ሆኑ፤ ዐመፁብህም፤ ሕግህንም አሽቀንጥረው ጣሉ፤ ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩት ነቢያትህን ገደሉ፤ አስጸያፊ የስድብ ቃልም ተናገሩ።
እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ።
በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጕረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብጽ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው።
“አንተ በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን መልእክት አንሰማም፤
እናደርጋለን ያልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ አባቶቻችን፣ ነገሥታታችንና ባለሥልጣኖቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም ለሰማይዋ ንግሥት እናጥናለን፤ የመጠጥ ቍርባን እናፈስስላታለን። በዚያ ጊዜ የተትረፈረፈ ምግብ ነበረን፤ በመልካም ሁኔታ እንገኝ ነበር እንጂ ምንም ክፉ ነገር አልገጠመንም።
እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሣለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።
ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል። ዕውቀትን ስለ ናቃችሁ፣ እኔም ካህናት እንዳትሆኑ ናቅኋችሁ፤ የአምላካችሁን ሕግ ስለ ረሳችሁ፣ እኔም ልጆቻችሁን እረሳለሁ።
ታዲያ፣ ይህ ሕዝብ ለምን ፊቱን አዙሮ ወደ ኋላ ይሄዳል? ለምንስ ኢየሩሳሌም ዘወትር ወደ ኋላ ትመለሳለች? ተንኰልን የሙጥኝ ብለው ይዘዋል፤ ሊመለሱም ፈቃደኛ አይደሉም።
መስፍኑ ከሞተ በኋላ ግን ሕዝቡ ሌሎችን አማልክት በመከተል፣ እነርሱን በማገልገልና በማምለክ ከአባቶቻቸው ይልቅ ወደ ክፉ መንገድ ተመለሱ፤ ክፉ ሥራቸውንና የእልኸኝነት መንገዳቸውንም አይተውም ነበር።
ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ምድር ውጡ፤ ነገር ግን ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆናችሁ፣ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋራ አልሄድም።”
እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብ ብለው ለማድመጥም አልፈለጉም፤ ይልቁን የክፉ ልባቸውን ሐሳብ በእልኸኝነት ተከተሉ፤ ወደ ፊት በመሄድ ፈንታም ወደ ኋላቸው ተመለሱ።
ይሁን እንጂ እነዚህም አልሰሙም፤ እግዚአብሔር አምላካቸውን እንዳልታመኑበት እንደ አባቶቻቸው ዐንገታቸውን አደነደኑ።
ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋራ የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤ እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዝዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤ እግዚአብሔር እንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።
አልሰማህም ወይም አላወቅህም፤ ጆሮህ ከጥንት የተከፈተ አልነበረም፤ አንተ አታላይ እንደ ነበርህ፣ ከልጅነትህ ጀምሮ ዐመፀኛ መባልህን ዐውቄአለሁና።
“ ‘ልጆቻቸው ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልተከተሉም፤ ሕጌን ለመጠበቅ አልተጉም፤ ሰንበቴንም አረከሱ። እኔም በምድረ በዳ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም አወርድባቸዋለሁ ብዬ ነበር።
ቃሌን መስማት ወዳልፈለጉት ወደ ቀድሞ አባቶቻቸው ኀጢአት ተመለሱ፤ ሊያገለግሏቸውም ሌሎችን አማልክት ተከተሉ። የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋራ የገባሁትን ኪዳን አፈረሱ።
እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንደምትረክሱ፣ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ ዐውቃለሁና። በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ስለምትፈጽሙ፣ እጆቻችሁ በሠሯቸውም ነገሮች እርሱን ለቍጣ ስለምታነሣሡት፣ በሚመጡት ዘመናት ጥፋት ይደርስባችኋል።”
እግዚአብሔር አገልጋዮቹን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሞ ወደ እናንተ ላከ፤ ሆኖም አልሰማችሁም፤ ትኵረትም አልሰጣችሁትም።
እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እንግዲህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣት ምድር ለዘላለም ትቀመጣላችሁ።
ቃሌን መስማት እንቢ ብለው በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ ሊያመልኳቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን ጣዖቶች የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝቦች ከጥቅም ውጭ እንደ ሆነው እንደዚህ መቀነት ይበላሻሉ።
እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ይህ የሆነው የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተው ስላልታዘዙኝና ሥርዐቴን ስላልተከተሉ ነው።
በዚህ ፈንታ፣ በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ አባቶቻቸው ያስተማሯቸውን በኣሊምን ተከተሉ።”
ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዞቼ ፈቀቅ ብላችኋል፤ አልጠበቃችኋቸውምም፤ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “እናንተ ግን፣ ‘የምንመለሰው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ።
እኔን ጥለሽኛል” ይላል እግዚአብሔር፤ “ወደ ኋላም እያፈገፈግሽ ነው፤ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ አጠፋሻለሁም፤ ከእንግዲህም አልራራልሽም።
ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤
ነገር ግን በተጣራሁ ጊዜ እንቢ ስላላችሁኝ፣ እጄንም ስዘረጋ ማንም ግድ ስላልነበረው፣
ምክሬን ሁሉ ስለ ናቃችሁ፣ ዘለፋዬንም ስላልተቀበላችሁ፣
እኔ ደግሞ በመከራችሁ እሥቅባችኋለሁ፤ መዓት በሚወርድባችሁም ጊዜ አፌዝባችኋለሁ፤
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ የሚያመልከኝም፣ ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ነው።
“እነርሱ ግን ማስተዋል አልፈለጉም፤ በእልኸኝነት ጀርባቸውን አዞሩ፤ ጆሯቸውንም ደፈኑ።
ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት በኩል በመንፈሱ የላከውን ቃል ወይም ሕግ አልሰሙም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ጸባኦት እጅግ ተቈጣ።
ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣ ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፣ የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤ አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋልና፤ የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃልለዋል።
እኔም፣ ‘ይህን የምጠላውን አስጸያፊ ነገር አታድርጉ’ በማለት አገልጋዮቼን ነቢያትን ደጋግሜ ላክሁባቸው።
እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ ከክፋታቸው አልተመለሱም፤ ለሌሎችም አማልክት ማጠን አልተውም።
ሰዎች ራሳቸውን የሚወድዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወድዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣
ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወድዱ፣
ከዳተኞች፣ ችኵሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወድዱ ይሆናሉና።
እናንተም ደግሞ ከአባቶቻችሁ የባሰ ክፉ ነገር አድርጋችኋል፤ እያንዳንዳችሁ እኔን በመታዘዝ ፈንታ የልባችሁን ክፋት ምን ያህል በእልኸኝነት እንደምትከተሉ ተመልከቱ።
እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ።
ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ፤
የዘላለም አምላክን ክብር ምዉት በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ በእንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት መልክ መስለው ለወጡ።
ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል የሚለውን ትክክለኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ ቢያውቁም፣ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ የሚያደርጉትንም ያበረታታሉ።
ነገር ግን ወይፈን የሚሠዋልኝ፣ ሰው እንደሚገድል ነው፤ የበግ ጠቦት የሚያቀርብልኝ፣ የውሻ ዐንገት እንደሚሰብር ሰው ነው፤ የእህል ቍርባን የሚያዘጋጅልኝ፣ የዕሪያ ደም እንደሚያቀርብልኝ ሰው ነው፤ የመታሰቢያን ዕጣን የሚያጥንልኝም፣ ጣዖትን እንደሚያመልክ ሰው ነው፤ የገዛ መንገዳቸውን መርጠዋል፤ ነፍሳቸውም በርኩሰታቸው ደስ ይላታል።
ስለዚህ ችግር እንዲደርስባቸው አደርጋለሁ፤ የፈሩትንም አመጣባቸዋለሁ፤ በተጣራሁ ጊዜ የመለሰ፣ በተናገርሁ ጊዜ ያደመጠ ሰው የለምና። በፊቴ ክፉ ነገር አደረጉ፤ የሚያስከፋኝንም መረጡ።”
እኔን ለሚንቁኝ፣ ‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤ የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣ ‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል።
የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆነ ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤
የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው።
ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቃል አቃልለሃል፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህንም ትእዛዞች አልጠበቅህም፤
ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው።
የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በእግዚአብሔርና በመሲሑ ላይ ሊመክሩ ተሰበሰቡ፤
“ሰንሰለታቸውን እንበጥስ፣ የእግር ብረታቸውንም አውልቀን እንጣል” አሉ።
እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ! ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ! የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’
የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይሳካላችሁም፤ እናንተ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቷችኋል’ ” አላቸው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህ እውነትን አይመለከቱምን? አንተ መታሃቸው፤ እነርሱ ግን አልተሰማቸውም፤ አደቀቅሃቸው፤ እነርሱ ግን አልታረሙም፤ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠነከሩ በንስሓ ለመመለስም አልፈለጉም።
ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በርሱ ላይ ማጕረምረማችሁን ሰምቷልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጕረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ” አላቸው።
እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦
ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈስሱ እጆች፣
ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣
በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው።
“ ‘የረከስሽው በብልግናሽ ነው፤ ቍጣዬ በአንቺ ላይ እስኪፈጸም ድረስ ከእንግዲህ ንጹሕ አትሆኚም፤ ከርኩሰትሽ ላነጻሽ ፈልጌ፣ መንጻት አልወደድሽምና።
“ሕዝቤ ሁለት ኀጢአት ፈጽመዋል፤ ሕያው የውሃ ምንጭ የሆንሁትን፣ እኔን ትተዋል፤ ውሃ መያዝ የማይችሉትን ቀዳዳ የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓዶች፣ ለራሳቸው ቈፍረዋል።
“በየከተማው ጥርሳችሁን አጠራለሁ፤ በየመንደሩም የምትበሉትን አሳጣኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም” ይላል እግዚአብሔር።
“መከር ሊደርስ ሦስት ወር ሲቀረውም፣ ዝናብ ከለከልኋችሁ፤ በአንዱ ከተማ ላይ አዘነብሁ፤ በሌላው ላይ ግን እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ አንዱ ዕርሻ ሲዘንብለት፣ ሌላው ዝናብ ዐጥቶ ደረቀ።
ሰዎች ውሃ ፍለጋ ከከተማ ወደ ከተማ ባዘኑ፣ ይሁን እንጂ ጠጥተው አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፤” ይላል እግዚአብሔር።
በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
“የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ዐንገታቸውን በማደንደን ቃሌን ስላልሰሙ በዚህች ከተማና በዙሪያዋ ባሉ መንደሮች ሁሉ ላይ ላደርስ ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ አመጣለሁ።’ ”
ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፣ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀልቁሃልም፦
እንደ አባቶቻችሁም ዐንገተ ደንዳኖች አትሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ እርሱ ለዘላለም ወደ ቀደሰውም መቅደስ ኑ። አስፈሪ ቍጣው ከእናንተ እንዲመለስም፣ እግዚአብሔር አምላካችሁን አገልግሉ።
ሀብታቸውን እንዲዘርፍ፣ ምርኮን እንዲያግበሰብስ፣ እንደ መንገድ ላይ ጭቃም እንዲረግጣቸው፣ አምላክ በሌለው ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፣ በሚያስቈጣኝም ሕዝብ ላይ እሰድደዋለሁ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የይሁዳ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋል፤ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፤ አባቶቻቸው በተከተሏቸው አማልክት፣ በሐሰት አማልክት በመመራት ስተዋልና።