Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘካርያስ 7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ፍትሕና ምሕረት የተወደደ ነው

1 ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ካሴሉ በተባለው በዘጠነኛው ወር፣ በአራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

2 የቤቴል ሰዎች እግዚአብሔርን ለመለመን ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን ዐብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች ጋራ ላኩ፤

3 እነርሱም የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤት ካህናትና ነቢያት፣ “ብዙ ዓመት እንዳደረግሁት፣ በዐምስተኛው ወር ማዘንና መጾም ይገባኛልን?” ብለው ጠየቁ።

4 ከዚያም የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

5 “የምድሩን ሕዝብ ሁሉና ካህናቱን እንዲህ በላቸው፤ ‘ባለፉት ሰባ ዓመታት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር የጾማችሁትና ያዘናችሁት በርግጥ ለእኔ ነበርን?

6 ትበሉና ትጠጡ የነበረውስ ለራሳችሁ አይደለምን?

7 ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች በሰላምና በብልጽግና ላይ ሳሉ፣ የደቡብና የምዕራብ ኰረብቶች ግርጌ የሰው መኖሪያም በነበሩበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት የተናገረው ቃል ይህ አልነበረምን?’ ”

8 የእግዚአብሔር ቃል እንደ ገና ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

9 “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እውነተኛ ፍትሕ አስፍኑ፣ እርስ በርሳችሁ ምሕረትና ርኅራኄን አድርጉ፤

10 መበለቲቱን ወይም ድኻ አደጉን፣ መጻተኛውን ወይም ድኻውን አታስጨንቁ፤ በልባችሁም አንዳችሁ በአንዳችሁ ላይ ክፉ አታስቡ።’

11 “እነርሱ ግን ማስተዋል አልፈለጉም፤ በእልኸኝነት ጀርባቸውን አዞሩ፤ ጆሯቸውንም ደፈኑ።

12 ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት በኩል በመንፈሱ የላከውን ቃል ወይም ሕግ አልሰሙም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ጸባኦት እጅግ ተቈጣ።

13 “ ‘ስጠራቸው አልሰሙም፤ ስለዚህ ሲጠሩኝ አልሰማም’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

14 ‘በማያውቋቸው በባዕዳን አሕዛብ መካከል በዐውሎ ነፋስ በተንኋቸው፤ ከእነርሱ በኋላ ማንም እስከማይመጣባትና እስከማይሄድባት ድረስ ምድሪቱ ባድማ ሆነች፤ መልካሚቱን ምድር ባድማ ያደረጓት በዚህ ሁኔታ ነው።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች