የልደት ቀን እግዚአብሔር የሰጠንን ተጨማሪ ዓመት ለማክበርና በረከቱን ለማስታወስ የሚሆን አጋጣሚ ነው። ይህንን የሕይወት ስጦታ ስለተቀበልክ እጅግ ደስ ይለኛል። እግዚአብሔር አስደናቂ ተስፋዎችን ሰጥቶናል፤ ይህ የደስታ ጊዜ እነዚህን ተስፋዎች ለማስታወስና ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር የእግዚአብሔርን ቃል ለመጋራት ተስማሚ ወቅት ነው።
በዚህ የልደት ቀንህ በየእለቱ ጤናን እና ከእግዚአብሔር የሚገኘውን እውነተኛ ጥበብ እመኝልሃለሁ። እግዚአብሔር መላእክቱን ልኮ እንዲጠብቅህ፣ እንዲሁም በእርሱ ፍጹም ፈቃድ መሠረት የልብህን ፍላጎት እንዲፈጽምልህ እጸልያለሁ። "በእኔ ዘንድ ዕድሜህ ይረዝማል፥ የሕይወትህም ዓመታት ይበዛሉ።" (ምሳሌ 9:11)
“ ‘ “እግዚአብሔር ይባርክህ፤ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፤ ይራራልህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ይመልስልህ፤ ሰላሙንም ይስጥህ።” ’
አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።” “ስለ ክብረ በዓላት መተጓጐል የተከዝሽበትን፣ የስድብሽን ሸክም፤ ከአንቺ አስወግዳለሁ።
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ ነፍስህንም ይንከባከባታል። እግዚአብሔር ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መውጣትህንና መግባትህን ይጠብቃል።
ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ እንዲሁም ዛሬ እኔ በማዝዝህ ሁሉ መሠረት አንተና ልጆችህ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመልሳችሁ በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ እርሱን ስትታዘዙ፣ ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከርሱ ጋራ እንድትጣበቅ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወትህ ነው፤ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ ሊሰጣቸው በማለላቸው ምድር ረዥም ዕድሜ ይሰጥሃል።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
በሕይወት ሳለሁ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ቆሜ እስከ ሄድሁ ድረስም አምላኬን እወድሳለሁ። እኔ በእግዚአብሔር ደስ እንደሚለኝ፣ የልቤ ሐሳብ እርሱን ደስ ያሠኘው።
እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በርሱ ኑሩ፤ በርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ እንደ ተማራችሁት በእምነት ጸንታችሁ፣ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ።
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ! ገርነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።