እግዚአብሔርን በሁሉም ነገር ማሳተፍ እንዴት ያስደስታል! ሠርግ ይሁን፣ የልደት በዓል፣ ምረቃ… ለማንኛውም ዝግጅትህ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ጥቅስ ማካተት እጅግ በጣም ደስ የሚል ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በዝግጅታችን ላይ ማካተት እንዴት መታደል ነው! እዚህ ለማንኛውም ዝግጅት የሚሆን ጥቅስ ታገኛለህ። በረከት እንደሚሆንህና እንደሚረዳህ ተስፋ አደርጋለሁ።
በልብህ እንዳለ፣ በክንድህም እንደምትይዘው ማኅተም አስቀምጠኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች፣ ቅናቷም እንደ መቃብር ጨካኝ ናትና፤ እንደሚንቦገቦግ እሳት፣ እንደ ኀይለኛም ነበልባል ትነድዳለች።
ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋራ እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።
በልብህ እንዳለ፣ በክንድህም እንደምትይዘው ማኅተም አስቀምጠኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች፣ ቅናቷም እንደ መቃብር ጨካኝ ናትና፤ እንደሚንቦገቦግ እሳት፣ እንደ ኀይለኛም ነበልባል ትነድዳለች። የውሃ ብዛት ፍቅርን ሊያጠፋ አይችልም፤ ፈሳሾችም አያሰጥሟትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይናቃል።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ። እናንተ ግን ክርስቶስን ያወቃችሁት እንደዚህ ባለ መንገድ አይደለም፤ በርግጥ ስለ እርሱ ሰምታችኋል፤ በኢየሱስም እንዳለው እውነት በርሱ ተምራችኋል። ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጐደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤ ደግሞም በአእምሯችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣ እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋራ እውነትን ተነጋገሩ፤ ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ነንና። “ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤” በቍጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት። ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም። እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎችን የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ። በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።
ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤ በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤ በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው። ምንም ጕዳት ሳያደርስብህ፣ ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ። በክፉ ሰው አትቅና፤ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ። እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል። የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤ የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል። እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል። በዚያ ጊዜ ሞገስንና ማስተዋልን፣ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ።
ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤
ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ አንድ ሐሳብ ይስጣችሁ፤ ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።
ባሎች ሆይ፤ እናንተም ደግሞ ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ በኑሯችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ ዐስቡላቸው፤ ደካሞች ስለ ሆኑና የሕይወትንም በረከት ዐብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው።
ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው።
ከእነርሱ ጥቂት ዕልፍ እንዳልሁ፣ ውዴን አገኘሁት፤ ያዝሁት፤ ወደ እናቴ ቤት እስካመጣው፣ በማሕፀን ወደ ተሸከመችኝም ዕልፍኝ እስካገባው ድረስ አልለቀውም።
የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ እግዚአብሔር ስላደረገልን ሁሉ፣ ስለሚመሰገንበት ሥራው፣ እንደ ፍቅሩና እንደ ቸርነቱ መጠን፣ ለእስራኤል ቤት ያደረገውን፣ አዎን፣ ስላደረገው መልካም ነገር እናገራለሁ።
ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣ የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ፣ ከቅዱሳን ሁሉ ጋራ የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው። እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር፣ አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፣ እርስ በርሳችሁም እንድትስማሙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።
እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
እኅቴ ሙሽራዬ፣ ፍቅርሽ እንዴት ደስ ያሰኛል! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ ምንኛ የሚያረካ ነው፤ የሽቱሽም መዐዛ ከቅመም ሁሉ ይልቅ የቱን ያህል ይበልጥ!
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል።
እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ስለዚህ፣ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ነኝ። ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅ ዐስብ ነበር፤ እንደ ልጅም አሰላ ነበር። ከጐለመስሁ በኋላ ግን የልጅነትን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቻለሁ። አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው፤ በዚያ ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያ ጊዜ እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የታወቅሁትን ያህል ዐውቃለሁ። እንግዲህ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። የትንቢት ስጦታ ቢኖረኝ፣ ምስጢርን ሁሉና ዕውቀትን ሁሉ ባውቅ፣ ተራራንም ከቦታው የሚነቅል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ያለኝን ሁሉ ለድኾች ብሰጥ፣ ሰውነቴንም እንዲቃጠል ለእሳት ብዳርግ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።