ልጅነትህን በሙሉ ኃይልህ ተደሰትበት፤ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ በየቀኑ ተሳተፍ። በወጣትነትህ ዘመን ያለህን ብርታት ተጠቀምበት፤ በወጣትነትህ አትናቀፍ። ብዙ ጊዜ ወጣቶች ስለወደፊቱ ሕይወት ሲያስቡ ተስፋ መቁረጥ ሊሰማቸው ይችላል፤ አንዳንዴም ጭንቀት ሊሰማህ ይችላል። ነገር ግን በፈጣሪህ በእግዚአብሔር ተጽናና። የሕይወትህን መሪነት እሱ ይዟልና በፍጹም ልብህ ፈልገው። በየቀኑ በእሱ ጸጋ እየተቀደስክ ሂድ።
በየቀኑ በምትሄድበት ቦታ ሁሉ በፍቅር፣ በንግግር፣ በአኗኗር፣ በእምነትና በንጽሕና ምሳሌ ሁል። እግዚአብሔር በቃሉ "ወጣት መንገዱን በቃሉ ያጠራል" ይላል። በየቀኑ ቃሉን ፈልግ፤ በሕይወትህም ድል ታገኛለህ።
እግዚአብሔር ያለህን ብርታትና ጊዜ የማታገኝባቸው፣ እንዲሁም እንደ ዛሬው ደስታ የማታገኝባቸው ቀናት ከመምጣታቸው በፊት ከሰማያዊው አባትህ ጋር ለመቅረብ ጊዜህን ተጠቀምበት። አንተ ለእግዚአብሔር አስፈላጊ ነህ። እሱ ለሕይወትህ ፍጹም ዕቅድ አለው፤ ያንንም ዕቅድ በአንተ ሕይወት ውስጥ ለማስፈጸም ይፈልጋል። ፈልገው፤ ዕቅዱንም በአንተ ውስጥ ያሳድራል። (1ኛ ጢሞቴዎስ 4:12) "ማንም ቢሆን ወጣትነትህን አይናቅ፤ ነገር ግን ለምእመናን በንግግር፣ በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና ምሳሌ ሁን።"
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል።
በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ። አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማንኛውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድድ የአብ ፍቅር በርሱ ዘንድ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።
እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። አባቶቻችን መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል። ስለዚህ የዛለውን ክንዳችሁንና የደከመውን ጕልበታችሁን አበርቱ። ዐንካሳው እንዲፈወስ እንጂ የባሰውኑ እንዳያነክስ “ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ።” ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም። ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ። ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኵርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው፣ ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላም ይህንኑ በረከት ሊወርስ በፈለገ ጊዜ እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም ለንስሓ ስፍራ ሊያገኝ አልቻለም። ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፣ ወደ ጨለማው፣ ወደ ጭጋጉና ወደ ዐውሎ ነፋሱ አልደረሳችሁም፤ ወደ መለከት ድምፅ ወይም ቃልን ወደሚያሰማ ድምፅ አልመጣችሁም፤ የሰሙትም ሌላ ቃል ተጨምሮ እንዳይናገራቸው ለመኑ። የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።
ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ እንግዲያው፣ በትንሹ ነገር ላይ ለመፍረድ አትበቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።
እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤
ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እርሱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሣሣ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤
ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ ትእዛዞቼን በልብህ ጠብቅ፤ ይህን ብታደርግ፣ ጐተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤ መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል። ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር፤ አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና። ብፁዕ ነው፤ ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው፤ እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና። ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም። በቀኝ እጇ ረዥም ዕድሜ አለ፤ በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች። መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤ ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል።
እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።
“እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና።
እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤
ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሏል። ስለዚህ በሙሉ ልብ፣ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።
“ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣ መንገዴ እንደ መንገዳችሁ አይደለምና” ይላል እግዚአብሔር። “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።
ልጆች ሆይ፤ በጌታ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ። የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ። ምክንያቱም ተጋድሏችን ከሥጋና ከደም ጋራ ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋራ ነው። ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣ በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ። ከእነዚህም ሁሉ ጋራ፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንን ራስ ቍር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ። የወንጌልን ምስጢር ለመግለጥ አፌን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በድፍረት እንድናገር ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ጸልዩልኝ። “አባትህንና እናትህን አክብር” በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ።
እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ።
በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ በሁሉን ቻይ አምላክ ጥላ ሥር ያድራል። ክፉ ነገር አያገኝህም፤ መቅሠፍትም ወደ ድንኳንህ አይገባም፤ በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይሰናከል፤ በእጆቻቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል። በአንበሳና በእፉኝት ላይ ትጫማለህ፤ ደቦሉን አንበሳና ዘንዶውን ትረግጣለህ። “ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ። ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ። ረዥም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።” እግዚአብሔርን፣ “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” እለዋለሁ።
በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።
ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋራ እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።
አሁን ግን፣ ያዕቆብ ሆይ የፈጠረህ፣ እስራኤል ሆይ! የሠራህ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ፤ “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደ ሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም። ገልጫለሁ፤ አድኛለሁ፤ ተናግሬአለሁ፤ በመካከላችሁ እኔ እንጂ ባዕድ አምላክ አልነበረም። እኔ አምላክ እንደ ሆንሁ፣ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከጥንት ጀምሮ እኔው ነኝ፤ ከእጄም ማውጣት የሚችል የለም፤ እኔ የምሠራውን ማን ማገድ ይችላል?” የእስራኤል ቅዱስ፣ የሚቤዣችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ እናንተ በባቢሎን ላይ ሰራዊት እሰድዳለሁ፤ በሚመኩባቸውም መርከቦች፣ ባቢሎናውያንን ሁሉ እንደ ኰብላይ አመጣለሁ። እኔ እግዚአብሔር፣ የእናንተ ቅዱስ፣ የእስራኤል ፈጣሪ፣ ንጉሣችሁ ነኝ።” በባሕር ውስጥ መንገድ፣ በማዕበል ውስጥ መተላለፊያ ያበጀ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እንደ ገና ላይነሡ እዚያው እንዲተኙ፣ እንደ ጧፍ ኵስታሪ ረግፈው እንዲጠፉ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን፣ ሰራዊቱንና ደጀኑን በአንድነት ያወጣ እንዲህ ይላል፤ “የቀደመውን ነገር አታስቡ፤ ያለፈውን እርሱ። እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ! እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤ በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
ጻድቃን ሲጮኹ፣ እግዚአብሔር ይሰማቸዋል፤ ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።
“አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”
“ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። “ግብዞች በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በየጐዳናውና በየምኵራቡ እንደሚያደርጉት፣ አንተም ለድኾች ምጽዋት በምትሰጥበት ጊዜ ይታይልኝ ብለህ ጥሩንባ አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።
ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።
የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት ርቃችሁ እንድትቀደሱ ነው፤ ደግሞም እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤
እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ክብር ይሁን! አሜን።
ብፁዓን ናቸው፤ መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ፤ በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ ከትእዛዞችህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ። መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ። አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም። ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው። ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው። የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ። እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በከንፈሬ ያቀረብሁትን የበጎ ፈቃድ ስጦታ ተቀበል፤ ሕግህንም አስተምረኝ። ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም። አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም። ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና። ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣ ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ። መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ። የአምላኬን ትእዛዞች እጠብቅ ዘንድ፣ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ራቁ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር። ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ። መሠሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው። የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ ፍርድህንም እፈራለሁ። ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤ እብሪተኞች እንዲጨቍኑኝ አትፍቀድላቸው። ዐይኖቼ ማዳንህን፣ የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። እኔ ባሪያህ ነኝ፤ ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣ ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው። ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ ትእዛዞችህን ወደድሁ። መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤ ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች። ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣ በከንፈሬ እናገራለሁ። የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤ አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል። ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣ አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም። ስምህን ለሚወድዱ ማድረግ ልማድህ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ወደ እኔ ተመልሰህ ምሕረት አድርግልኝ። አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ። ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣ ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ። በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። ሕግህ ባለመከበሩ፤ እንባዬ እንደ ውሃ ይፈስሳል። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ፍርድህም ትክክል ነው። ምስክርነትህን በጽድቅ አዘዝህ፤ እጅግ አስተማማኝም ነው። ጠላቶቼ ቃልህን ዘንግተዋልና፣ ቅናት አሳረረኝ። ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል። ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፤ ባሪያህም ወደደው። እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም። ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤ ሕግህም እውነት ነው። መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤ ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው። ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤ በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤ ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ። ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ፤ ምስክርነትህንም እጠብቃለሁ። ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ። ቃልህን አሰላስል ዘንድ፣ ዐይኔ ሌሊቱን ሙሉ ሳይከደን ያድራል። እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ሕግህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ። ደባ የሚያውጠነጥኑ ወደ እኔ ቀርበዋል፤ ከሕግህ ግን የራቁ ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህም ሁሉ እውነት ናቸው። ለዘላለም እንደ መሠረትሃቸው፣ ከጥንት ምስክርነትህ ተረድቻለሁ። ሕግህን አልረሳሁምና፣ ሥቃዬን ተመልከት፤ ታደገኝም። ተሟገትልኝ፤ አድነኝም፤ እንደ ቃልህም ሕያው አድርገኝ። ሥርዐትህን ስለማይሹ፣ ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ እንደ ሕግህ ሕያው አድርገኝ። የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ከምስክርህ ዘወር አላልሁም። ቃልህን አይጠብቁምና፣ ከዳተኞችን አይቼ አርቃቸዋለሁ። መመሪያህን እንዴት እንደምወድድ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ። በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልዘነጋም። ቃልህ በሙሉ እውነት ነው፤ ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው። ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤ ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ። ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፣ በቃልህ ደስ አለኝ። ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፣ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን የሚወድዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ትእዛዝህንም እፈጽማለሁ። ነፍሴ ምስክርነትህን ትጠብቃለች፤ እጅግ እወድደዋለሁና። መንገዴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነውና፣ ሕግህንና ምስክርነትህን እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ። ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣ ለአገልጋይህ መልካም አድርግ። ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ታደገኝ። ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣ ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ። ትእዛዞችህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዞች ናቸውና፣ አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር። ትእዛዝህን መርጫለሁና፣ እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ደስታዬ ነው። አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤ ሕግህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዞችህን አልረሳሁምና፣ ባሪያህን ፈልገው። ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት። እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር። ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔር ሕግ፤ ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት፤
ሰውየውም መልሶ፣ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው።
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
ስለዚህ እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ በዚህ ፈንታ ግን በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቍርጥ ሐሳብ አድርግ።
በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ። ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል፤ እነርሱ ዐላፊ ጠፊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ይደክማሉ፤ እኛ ግን ለዘላለም የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት እንደክማለን።
ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏል።
እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።
እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች።
ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደ ያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ።
“በጠባቡ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይገባሉ። ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው።
ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው። ስለዚህ የጨለማን ሥራ ጥለን፣ የብርሃንን ጦር ዕቃ እንልበስ። በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን። ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በዐሳባችሁ አትመቻቹለት።
ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ ለምኑት።”
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
ደግሞም፣ “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤” እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው።
እኛም ሁላችን ባልተሸፈነ ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያንጸባረቅን፣ የርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው መንፈስ ከሆነ ጌታ ነው።
“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤ ሰዎችም መብራት አብርተው ከእንቅብ በታች አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ። እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።
በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣ በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣ በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።