ዕብራውያን 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢየሱስ ከሙሴ በላይ ነው 1 እንግዲህ የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፤ የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ። 2 ሙሴ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ ታማኝ እንደ ነበር፣ እርሱም ለሾመው ታማኝ ነበር። 3 ቤትን የሚሠራ ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው፣ ኢየሱስም ከሙሴ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተገኝቷል። 4 እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው። 5 “ሙሴ ወደ ፊት ስለሚነገረው ነገር እየመሰከረ፣ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ እንደ አንድ ታማኝ አገልጋይ ነበር።” 6 ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን። ስለ አለማመን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 7 ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፣ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ 8 በምድረ በዳ በፈተና ቀን፣ በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣ ልባችሁን አታደንድኑ። 9 አባቶቻችሁ በዚያ ተፈታተኑኝ፤ መረመሩኝ፤ ያደረግሁትንም ሁሉ ለአርባ ዓመት አዩ። 10 በዚያም ትውልድ ላይ የተቈጣሁት ለዚህ ነበር፤ እንዲህም አልሁ፤ ‘በልባቸው ዘወትር ይስታሉ፤ መንገዴንም አላወቁም።’ 11 ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤ ‘ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም።’ ” 12 ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያስኰበልል፣ ኀጢአተኛና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ። 13 ነገር ግን ከመካከላችሁ ማንም በኀጢአት ተታልሎ ልቡ እንዳይደነድን፣ “ዛሬ” እየተባለ ሳለ በየቀኑ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ። 14 በመጀመሪያ የነበረንን እምነት እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንይዝ ከክርስቶስ ጋራ ተካፋዮች እንሆናለን። 15 ይኸውም፣ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣ አሁንም ልባችሁን አታደንድኑ” እንደ ተባለው ነው። 16 ሰምተው ያመፁት እነማን ነበሩ? ሙሴ ከግብጽ መርቶ ያወጣቸው ሁሉ አይደሉምን? 17 አርባ ዓመት የተቈጣውስ እነማንን ነበር? ኀጢአት ሠርተው ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረውን አይደለምን? 18 ያልታዘዙትን ካልሆነ በቀር ወደ ዕረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? 19 እንግዲህ ሊገቡ ያልቻሉት ካለማመናቸው የተነሣ እንደ ሆነ እንረዳለን። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.