Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሚልክያስ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 “እነሆ፤ በፊቴ መንገድ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ ደስ የምትሰኙበትም የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ይመጣል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

2 እርሱ የሚመጣበትን ቀን ማን ሊቋቋመው ይችላል? በሚገለጥበትስ ጊዜ በፊቱ መቆም የሚችል ማን ነው? እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳት ወይም እንደ ልብስ ዐጣቢ ሳሙና ነውና።

3 ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ ሌዋውያንንም አንጽቶ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ቍርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖሩታል፤

4 በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቍርባን እንዳለፉት ቀናትና እንደ ቀድሞው ዘመን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።

5 “ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።


እግዚአብሔርን መስረቅ

6 “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አልጠፋችሁም።

7 ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዞቼ ፈቀቅ ብላችኋል፤ አልጠበቃችኋቸውምም፤ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “እናንተ ግን፣ ‘የምንመለሰው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ።

8 “ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን ትሰርቁኛላችሁ። “እናንተ ግን፣ ‘እንዴት እንሰርቅሃለን?’ ትላላችሁ። “ዐሥራትና መባ ትሰርቁኛላችሁ፤

9 እናንተም፣ መላው ሕዝባችሁም ስለምትሰርቁኝ የተረገማችሁ ናችሁ።

10 በቤቴ መብል እንዲኖር፣ እኔንም በዚህ እንድትፈትኑኝ ዐሥራቱን ሁሉ ወደ ጐተራ አስገቡ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ “የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ።

11 ስለ እናንተ ተባዩን እገሥጻለሁ፤ አዝመራችሁን አይበላም፤ ዕርሻ ላይ ያለ የወይን ተክላችሁም ፍሬ አልባ አይሆንም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

12 “ከዚያም በኋላ የተድላ ምድር ስለምትሆኑ፣ ሕዝቦች ሁሉ የተባረከ ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

13 “በእኔ ላይ የድፍረት ቃል ተናግራችኋል” ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ ግን፣ ‘በአንተ ላይ የተናገርነው ምንድን ነው?’ ትላላችሁ።

14 “እንዲህም ብላችኋል፤ ‘እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ በማድረግና በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ሐዘንተኞች ሆነን በመመላለስ ምን ተጠቀምን?

15 አሁን ግን ትዕቢተኞችን ቡሩካን እንላቸዋለን፤ ክፉ አድራጊዎች ይበለጽጋሉ፤ እግዚአብሔርን የሚፈታተኑትም ያመልጣሉ።’ ”

16 በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔር አደመጠ። ሰማቸውም፤ እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ስሙን ለሚያከብሩ በርሱ ፊት የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።

17 “እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የገዛ ገንዘቤ ይሆናሉ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ “አባት የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚታደግ ሁሉ እኔም እታደጋቸዋለሁ።

18 በዚያ ጊዜም እንደ ገና በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት ታያላችሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች