ምሳሌ 17:15 ላይ «ክፉን የሚያጸድቅና ጻድቅን የሚኮንን ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠሉ ናቸው» ይላል። እግዚአብሔር ክፉዎችን የምናጸድቅ ከሆነም ሆነ ጻድቃንን የምንኮንን ከሆነ ሁለቱንም ይጠላል። ፍትሑ ከአድልዎና ከሙስና የጸዳ፣ ሁልጊዜም ሚዛናዊና ፍትሃዊ እንደሆነ ያሳየናል። እርሱ በመንገዱ ሁሉ ቅን ነውና።
በኢሳይያስ 1:17 ላይ ደግሞ እግዚአብሔር ኢፍትሃዊነትን እንድንቃወም ይጠራናል፡- «መልካምን ለማድረግ ተማሩ፤ ፍትሕን ፈልጉ፤ የተገፋውን አቅኑ፤ ለድሀ ፍርድ ስጡ፤ ለመበለቶችም እርዱ።» ይህ ክፍል በቃላችን ብቻ ሳይሆን በተግባራችንም ለፍትህ እንድንታገልና የለውጥ አምጪዎች እንድንሆን ያበረታታናል። ኢፍትሃዊነት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ችግር ነው። ስለዚህ ከክፋትና ከኢፍትሃዊነት ሁሉ እንዲጠብቀን ወደ እግዚአብሔር መጸለይ አለብን።
በሚክያስ 6:8 ላይ «እናንተ ሰዎች፥ መልካም የሆነውን እግዚአብሔር አስቀድሞ ነግሮአችኋል፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ የሚፈልገው ፍትሕን ማድረግ፥ ምሕረትን መውደድ፥ በትሕትናም ከአምላካችሁ ጋር መሄድ ነው።» ክርስቲያኖች እንደመሆናችን የኢየሱስን ፈለግ በመከተል ፍትህ በጎደለው ዓለም ውስጥ የፍትህ መሣሪያዎች ለመሆን መወሰን ኃላፊነታችን ነው።
ፍትህ በእጃችን ሳይሆን በእግዚአብሔር እጅ እንዳለ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። በሉዓላዊነቱ ታምነን ለፍትህ ስንታገል መሪነቱን መፈለግ አለብን።
ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል።
ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
ፍትሕ የጐደለውን ሕግ ለሚያወጡ፣ ጭቈና የሞላበትን ሥርዐት ለሚደነግጉ ወዮላቸው! የጣዖታትን መንግሥታት፣ ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ መንግሥታት የሚበልጡትን እጄ እንደ ያዘች ሁሉ፣ በሰማርያና በጣዖቶቿ ያደረግሁትን፣ በኢየሩሳሌምና በተቀረጹ ምስሎቿስ እንዲሁ አላደርግምን?” ጌታ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ የሚያደርገውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፣ እንዲህ ይላል፤ “የአሦርን ንጉሥ ስለ ልቡ ትዕቢትና ስለ ንቀት አመለካከቱ እቀጣዋለሁ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፤ “ ‘ይህን ሁሉ ያደረግሁት በክንዴ ብርታት ነው፤ ደግሞም በጥበቤ አስተዋይ ነኝና። የመንግሥታትን ድንበር አፈረስሁ፤ ሀብታቸውን ዘረፍሁ፤ ነገሥታታቸውን እንደ አንድ ኀያል ሆኜ አዋረድሁ። ሰው እጁን ወደ ወፍ ጐጆ እንደሚሰድድ፣ እኔም እንዲሁ እጄን ወደ መንግሥታት ሀብት ሰደድሁ፤ ሰዎች የተተወ ዕንቍላል እንደሚሰበስቡ፣ እኔም እንዲሁ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤ ክንፉን ያራገበ የለም፤ አፉንም ከፍቶ የጮኸ አልነበረም።’ ” መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይኵራራልን? መጋዝስ በሚስበው ላይ ይታበያልን? በትር በሚያነሣው ሰው ላይ ራሱን እንደሚነቀንቅ፣ ዘንግም ራሱን ዕንጨት እንዳልሆነ አድርጎ እንደሚኵራራ ነው። ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በፈረጠሙ ጦረኞቹ ላይ የሚያከሳ በሽታ ይልካል፤ ከክብሩም በታች እንደ ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳት ይለኰሳል። የእስራኤል ብርሃን እሳት፣ ቅዱሱም ነበልባል ይሆናል፤ በአንድ ቀንም እሾኹንና ኵርንችቱን እሳት ይበላዋል፤ ሕመምተኛ እየመነመነ እንደሚሞት፣ የደኑን ክብርና የለማውን ዕርሻ፣ ነፍስና ሥጋንም ፈጽሞ ያጠፋል። በደኑ ውስጥ የሚተርፉት ዛፎች በጣም ጥቂት ናቸው፤ ሕፃን ልጅ እንኳ ቈጥሮ ሊመዘግባቸው ይችላል። የድኾችን መብት ለሚገፍፉ፣ የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፣ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፣ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው!
እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦ ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈስሱ እጆች፣ ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣ በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው።
ለዐቅመ ቢሶችና ለድኻ አደጎች ፍረዱላቸው፤ የችግረኛውንና የምስኪኑን መብት አስከብሩ። ወገን የሌለውንና ድኻውን ታደጉ፤ ከግፈኛውም እጅ አስጥሏቸው።
አምላካችን ሆይ፤ ተንቀናልና ስማን፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ አውርድባቸው፤ በምርኮ ምድር እንዲበዘበዙ አሳልፈህ ስጣቸው። የፈረሰውን በሚሠሩት ፊት የስድብ ናዳ አውርደዋልና በደላቸውን ይቅር አትበል፤ ኀጢአታቸውንም ከፊትህ አታጥፋው።
ከክፉ ራቅ፤ መልካሙንም አድርግ፣ ለዘላለምም ትኖራለህ። እግዚአብሔር ፍትሕን ይወድዳልና፣ ታማኞቹንም አይጥልም። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤ የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።
እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤ መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋራ ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው።
“ሰማይ ሆይ፤ በርሷ ላይ ሐሤት አድርግ! ቅዱሳን፣ ሐዋርያትና ነቢያትም ሐሤት አድርጉ! በእናንተ ላይ ባደረሰችው ነገር እግዚአብሔር ፈርዶባታልና።”
“እኔ እግዚአብሔር ፍትሕን ስለምወድድ፣ ዝርፊያንና በደልን እጠላለሁ፤ በታማኝነቴም የሚገባቸውን እሰጣቸዋለሁ፤ ከእነርሱም ጋራ የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።
እናንተ ድኻውን ትረግጣላችሁ፤ እህል እንዲሰጣችሁም ታስገድዱታላችሁ፤ ስለዚህ በተጠረበ ድንጋይ ቤት ብትሠሩም፣ በውስጡ ግን አትኖሩም፤ ባማሩ የወይን ተክል ቦታዎች ወይን ብትተክሉም፣ የወይን ጠጁን ግን አትጠጡም፤ ኀጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደ ሆነ፣ በደላችሁም የቱን ያህል እንደ በዛ እኔ ዐውቃለሁና። ጻድቁን ትጨቍናላችሁ፤ ጕቦም ትቀበላላችሁ፤ በፍርድ አደባባይም ከድኻው ፍትሕ ትነጥቃላችሁ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ የተገፉትን ምኞት ትሰማለህ፤ ልባቸውን ታበረታለህ፤ ጆሮህንም ወደ እነርሱ ጣል ታደርጋለህ፤ ከዐፈር የተፈጠረ ሰው ከእንግዲህ እንዳያስጨንቃቸው፣ አንተ ለድኻ አደጉና ለተገፋው ትሟገታለህ።
ዐመፀኞችን በማየት አትሸበር፤ በክፉ አድራጊዎችም አትቅና፤ ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታሥሥ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ። ክፉዎች በጻድቃን ላይ ያሤራሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጩባቸዋል። እግዚአብሔር ግን ይሥቅባቸዋል፣ ቀናቸው እንደ ደረሰ ያውቃልና። ችግረኞችንና ድኾችን ለመጣል፣ አካሄዳቸው ቀና የሆነውንም ለመግደል፣ ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፤ ቀስታቸውንም ገተሩ። ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል፤ ቀስታቸውም ይሰበራል። የጻድቅ ጥቂት ሀብት፣ ከክፉዎች ብዙ ጥሪት ይበልጣል። የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና፣ ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ደግፎ ይይዛቸዋል። እግዚአብሔር የንጹሓንን የሕይወት ዘመን ያውቃል፤ ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል። በክፉ ጊዜ ዐንገት አይደፉም፤ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤ እንደ ለምለም ቅጠልም ይጠወልጋሉ።
በዚህም ነገር ማንም ተላልፎ ወንድሙን አያታልል፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደ ነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ ጌታ እንደ እነዚህ ያለውን ኀጢአት ሁሉ የሚፈጽሙትን ይበቀላል፤
ክፉዎች ርኅራኄ ቢደረግላቸው እንኳ፣ ጽድቅን አይማሩም፤ በቅንነት ምድር እንኳ ክፋትን ያደርጋሉ፤ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያስተውሉም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ክንድህ ከፍ ከፍ ብሏል፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም፤ ለሕዝብህ ያለህን ቅናት ይዩ፤ ይፈሩም፤ ለጠላቶችህም የተዘጋጀው እሳት ይብላቸው።
“በዳኝነት ጊዜ በድኻው ላይ ፍርድ አታጓድልበት። ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ጻድቁን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና።
“መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብጽ መጻተኛ ነበራችሁና። “ባል በሞተባት ወይም አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ።
ከፀሓይ በታችም ሌላ ነገር አየሁ፤ በፍርድ ቦታ ዐመፅ ነበር፤ በፍትሕ ቦታ ግፍ ነበር። እኔም በልቤ፣ “ለማንኛውም ድርጊት፣ ለማንኛውም ተግባር ጊዜ ስላለው፣ አምላክ ጻድቁንና ኀጢአተኛውን ወደ ፍርድ ያመጣቸዋል” ብዬ አሰብሁ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የእስራኤል ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ጻድቁን ስለ ጥሬ ብር፣ ድኻውንም ስለ ጥንድ ጫማ ይሸጡታልና። የችግረኞችን ራስ፣ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ ፍትሕንም ከጭቍኖች ይነጥቃሉ፤ አባትና ልጅ ከአንዲት ሴት ጋራ ይተኛሉ፤ እንዲህም እያደረጉ ቅዱስ ስሜን ያረክሳሉ።
“ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
የሚመካ ግን፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና፣ በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣ እደሰታለሁና፤” ይላል እግዚአብሔር።
ለተበደሉት የሚፈርድ፣ ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው፤ እግዚአብሔር እስረኞችን ከእስራት ያወጣል፤ እግዚአብሔር የዕውራንን ዐይን ያበራል፤ እግዚአብሔር የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድኻ አደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤ የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።
ኀያላን ሆይ፤ በውኑ ጽድቅ ከአፋችሁ ይወጣል? የሰው ልጆች ሆይ፤ በቅን ትፈርዳላችሁን? ጻድቃን በቀልን ባዩ ጊዜ ደስ ይላቸዋል፤ እግራቸውንም በግፈኞች ደም ይታጠባሉ። ሰዎችም፣ “በርግጥ ለጻድቃን ብድራት ተቀምጦላቸዋል፤ በእውነትም በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ” ይላሉ። የለም፤ በልባችሁ ክፋትን ታውጠነጥናላችሁ፤ በእጃችሁም ዐመፅን በምድር ላይ ትጐነጕናላችሁ።
“እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣ የጭቈናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣ ተንከራታቹን ድኻ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣ የተራቈተውን ስታይ እንድታለብሰው፣ የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሣው አይደለምን?
ችግረኛና ድኻ የሆነውን የምንዳ ሠራተኛ እስራኤላዊ ወንድምህም ሆነ፣ ከከተሞችህ በአንዲቱ የሚኖረውን መጻተኛ አትበዝብዘው፤ የሠራበትን ሒሳብ በዕለቱ፣ ፀሓይ ሳትጠልቅ ክፈለው፤ ድኻ በመሆኑ በጕጕት ይጠባበቀዋልና። አለዚያ ወደ እግዚአብሔር ይጮኽና ኀጢአት ይሆንብሃል።
ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት አመንዝራ እንደ ሆነች ተመልከቱ፤ ቀድሞ ፍትሕ የሞላባት፣ ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤ አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ማደሪያ ሆነች፤
ድኾች በመሆናቸው ብቻ ድኾችን አትበዝብዛቸው፤ ችግረኛውንም በአደባባይ አታንገላታው፤ እግዚአብሔር ይፋረድላቸዋልና፤ የሚቀሟቸውንም ይቀማቸዋል።
“እናንተ ፈሪሳውያን ግን ወዮላችሁ፤ ከአዝሙድና ከጤና አዳም እንዲሁም ከአትክልት ሁሉ ዐሥራት ታወጣላችሁ፤ ሆኖም ፍትሕንና እግዚአብሔርን መውደድ ቸል ትላላችሁ፤ ነገር ግን ያን ሳትተዉ ይህኛውን ማድረግ በተገባችሁ ነበር።
እናንተ ችግረኞችን የምትረግጡ፣ የምድሪቱንም ድኾች የምታጠፉ ይህን ስሙ፤ እንዲህም ትላላችሁ፤ “መስፈሪያውን በማሳነስ፣ ዋጋውን ከፍ በማድረግ፣ በሐሰተኛ ሚዛን በማጭበርበር፣ እህል እንድንሸጥ፣ የወር መባቻ መቼ ያበቃል? ስንዴም ለገበያ እንድናቀርብ፣ ሰንበት መቼ ያልፋል?” ድኻውን በብር፣ ችግረኛውንም በጥንድ ጫማ እንገዛለን፤ ግርዱን እንኳ በስንዴ ዋጋ እንሸጣለን።
“የሐሰት ወሬ አትንዛ፤ ተንኰል ያለበትን ምስክርነት በመስጠት ክፉውን ሰው አታግዝ። “ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤ ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ። “ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ። “ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ። “በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታከብራላችሁ። “የቂጣ በዓልን አክብር፤ እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን እርሾ የሌለውን ቂጣ ብላ፤ ይህንም በአቢብ ወር በተወሰነ ቀን አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብጽ ወጥተሃልና። “ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ። “በማሳህ ላይ በዘራኸው እህል በኵራት የመከርን በዓል አክብር። “በዓመቱ መጨረሻ በማሳህ ላይ ያለውን እህልህን ስትሰበስብ የመክተቻውን በዓል አክብር። “በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይቅረብ። “የመሥዋዕትን ደም እርሾ ካለበት ነገር ጋራ አድርገህ ለእኔ አታቅርብ። “የበዓል መሥዋዕቴ ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቈይ። “የምድርህን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቤት አምጣ። “ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል። “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል፤ በሕግ ፊት ምስክርነት ስትሰጥ፣ ከብዙዎቹ ጋራ ተባብረህ ፍትሕ አታጣምም። “እነሆ፤ በጕዞ ላይ ሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራ የሚያስገባህን መልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ። በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ ስማው፤ አታምፅበት። ስሜ በርሱ ላይ ነውና ዐመፅህን ይቅር አይልም። የሚናገረውን በጥንቃቄ ብታደምጥና ያልኩህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህን እቃወማለሁ። መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ አንተንም ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ያስገባሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ። ለአማልክታቸው አትስገድ፤ ወይም አታምልካቸው፤ ወይም ልምዳቸውን አትከተል፤ እነርሱን ማፈራረስ አለብህ፤ የአምልኮ ድንጋዮቻቸውንም ሰባብር። አምላክህን እግዚአብሔርን አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ። በምድርህም የሚያስወርዳት ወይም መካን ሴት አትኖርም፤ ረዥም ዕድሜም እሰጥሃለሁ። “በሚያጋጥሙህ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፤ ግራም አጋባቸዋለሁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ። ኤዊያውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን ከመንገድህ ለማስወጣት ተርብን በፊትህ እሰድዳለሁ። ነገር ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አላወጣቸውም፤ ምክንያቱም ምድሪቱ ባድማ ሆና የዱር አራዊት ይበዙባችኋል። በዳኝነት ጊዜ ለድኻው አታድላ።
እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት ብፁዓን ናቸው!
ሀብትን በግፍ የሚያከማች ሰው፣ ያልፈለፈለችውን ጫጩት እንደምትታቀፍ ቆቅ ነው፤ በዕድሜው አጋማሽ ትቶት ይሄዳል፤ በመጨረሻም ሞኝነቱ ይረጋገጣል።
እንደ ገና ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ አስተዋልሁም፤ የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም።
“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤
ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቋል፤ ጽድቅም በሩቁ ቆሟል፤ እውነት በመንገድ ላይ ተሰናክሏል፤ ቅንነትም መግባት አልቻለም። እውነት የትም ቦታ አይገኝም፤ ከክፋት የሚርቅ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። እግዚአብሔር ተመለከተ፤ ፍትሕ በመታጣቱም ዐዘነ።
እግዚአብሔር፣ ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋራ እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤ “የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤ ሕዝቤን በችግር ስታደቅቁት፣ የድኾችንም ፊት በሐዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?” ይላል ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
እግዚአብሔር ግን ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ነው፤ መንበሩንም ለፍርድ አጽንቷል። ዓለምን በጽድቅ ይዳኛል፤ ሕዝቦችንም በፍትሕ ይገዛል። እግዚአብሔር ለተጨቈኑት ዐምባ ነው፤ በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናቸዋል።
“በሕዝቤ መካከል ክፉ ሰዎች አሉና፤ ወፍ እንደሚያጠምዱ ሰዎች፣ ወጥመድ ዘርግተው ሰው እንደሚይዙ ሰዎችም ያደባሉ። ወፎች እንደ ሞሉት ጐጆ፣ ቤታቸው በማጭበርበር የተሞላ ነው፤ ባለጠጎችና ኀያላን ሆነዋል፤ ወፍረዋል፤ ሠብተዋልም። ክፋታቸው ገደብ የለውም፤ ወላጅ የሌላቸው ፍትሕ እንዲያገኙ አልቆሙላቸውም፤ ለድኾችም መብት አልተከራከሩም። ስለ እነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?” ይላል እግዚአብሔር። “እንዲህ ዐይነቶቹን ሕዝብ፣ እኔ ራሴ ልበቀላቸው አይገባኝምን?
በደለኛውን፣ “አንተ ንጹሕ ነህ” የሚለውን፣ ሕዝቦች ይረግሙታል፤ መንግሥታትም ያወግዙታል። በደለኛውን፣ “አንተ ጥፋተኛ ነህ” የሚሉት ግን መልካም ነገር ይገጥማቸዋል፤ የተትረፈረፈ በረከትም ይወርድላቸዋል።
ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቷል። ስለዚህ ሕግ ደክሟል፤ ፍትሕ ድል አይነሣም፤ ፍትሕ ይጣመም ዘንድ፣ ክፉዎች ጻድቃንን ይከብባሉ።
እግዚአብሔርስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ከመጠን በላይስ ችላ ይላቸዋልን? እላችኋለሁ፤ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆንን?”
በአገር ውስጥ ድኻ ተጨቍኖ፣ ፍትሕ ተጓድሎ፣ መብትም ተረግጦ ብታይ፣ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች አትደነቅ፤ ምክንያቱም አንዱን አለቃ የበላዩ ይመለከተዋል፤ በእነዚህ በሁለቱም ላይ ሌሎች ከፍ ያሉ አሉ።
ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ አስታምማችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’
በምትጐበኙበት ቀን ምን ይውጣችኋል? ጥፋት ከሩቅ ሲመጣስ ምን ትሆናላችሁ? ርዳታን ለማግኘትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ሀብታችሁንስ የት ታገኙታላችሁ?
እንግዲህ እናንተ ሀብታሞች ስሙ፤ ስለሚደርስባችሁ መከራ አልቅሱ፤ ዋይ ዋይም በሉ። ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው። ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ፤ በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል። ከእናንተ መካከል በመከራ ውስጥ ያለ አለ? እርሱ ይጸልይ፤ የተደሰተ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር። ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትም ሠርቶ ከሆነ፣ ይቅር ይባላል። ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል። ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም። እንደ ገናም ጸለየ፤ ዝናብም ከሰማይ ዘነበ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ አንዱ ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፣ ሀብታችሁ ሻግቷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል። ይህን አስተውሉ፤ ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው ነፍሱን ከሞት ያድነዋል፤ ብዙ ኀጢአትንም ይሸፍናል። ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለመጨረሻው ዘመን ሀብትን አከማችታችኋል። ልብ በሉ፤ ዕርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የዐጫጆቹም ጩኸት ሁሉን ቻይ ወደ ሆነው ጌታ ጆሮ ደርሷል።
የሠራ አካላቴ እንዲህ ይልሃል፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ማን አለ? ችግረኛውን ከርሱ ከሚበረቱ፣ ችግረኛውንና ድኻውን ከቀማኞች ታድናለህ።”
“እኔ ብሆን ኖሮ፣ ወደ እግዚአብሔር በቀረብሁ፣ ጕዳዬንም በፊቱ በገለጽሁለት ነበር። እርሱ፣ የማይመረመሩ ድንቅ ነገሮች፣ የማይቈጠሩም ታምራት ያደርጋል።
በጽድቅ የሚራመድ፣ ቅን ነገር የሚናገር፣ በሽንገላ የሚገኝን ትርፍ የሚንቅ፣ መማለጃን ላለመቀበል እጁን የሚሰበስብ፣ የግድያን ሤራ ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣ ክፋትን ላለማየት ዐይኑን የሚጨፍን፣
ሰዎች ድንበር ይገፋሉ፤ የሰረቁትን መንጋ ያሰማራሉ። የተሸከመቻቸው ማሕፀን ትረሳቸዋለች፤ ትል ይቦጠቡጣቸዋል፤ ክፉዎች እንደ ዛፍ ይሰበራሉ፤ የሚያስታውሳቸውም የለም። የማትወልደውን መካኒቱን ይቦጠቡጣሉ፤ ለመበለቲቱም አይራሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ኀያላንን በኀይሉ ጐትቶ ይጥላል፤ ቢደላደሉም የሕይወት ዋስትና የላቸውም። ያለ ሥጋት እንዲኖሩ ትቷቸው ይሆናል፤ ዐይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው። ለጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ሆኖም ይጠፋሉ፤ ዝቅ ዝቅ ብለው፤ እንደ ሌሎቹ ይከማቻሉ። እንደ እህል ራስም ይታጨዳሉ። “ይህ እንዲህ ካልሆነማ፣ የሚያስተባብለኝ ማን ነው? ቃሌን ከንቱ የሚያደርገውስ ማን ነው?” የድኻ አደጉን አህያ ቀምተው ይሄዳሉ፤ የመበለቲቱንም በሬ በመያዣነት ይወስዳሉ። ድኾችን ከመንገድ ያስወግዳሉ፤ የምድሪቱም ችግረኞችን ይሸሸጋሉ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ታውቃለህ፤ እንግዲህ ዐስበኝ፤ ጐብኘኝም፤ አሳዳጆቼን ተበቀልልኝ። ታጋሽ እንደ መሆንህ አታጥፋኝ፤ ባንተ ምክንያት የሚደርስብኝን ነቀፋ ዐስብ።
ሕዝቡም፣ “ታዲያ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም፣ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ” ብሎ መለሰላቸው።
በእስር ላይ ያሉትን ከእነርሱ ጋራ እንደ ታሰራችሁ ሆናችሁ አስቧቸው፤ እንዲሁም በሰው እጅ የሚንገላቱትን ራሳችሁ መከራ እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ አስቧቸው።
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል። በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤ ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤ ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣ ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣ የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል። ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣ የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣ ጌታ እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣ ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል። የተወደደችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት፣ የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣ የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤