ኤርምያስ 14:2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ይሁዳ አለቀሰች፤ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ፤ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የኢየሩሳሌምም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ይሁዳ ታለቅሳለች፤ ከተሞቿም ይማቅቃሉ፤ በምድር ላይ ተቀምጠው ይቈዝማሉ፤ ጩኸትም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ይሰማል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “ይሁዳ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ፤ ስለ ምድሪቱም አለቀሱ፤ የኢየሩሳሌም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሏል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ይሁዳ በሐዘን ላይ ነች፤ ከተሞችዋም በሞት ጣዕር ላይ ናቸው፤ ሕዝብዋም በሐዘን ምክንያት በመሬት ላይ ተቀምጠው ያለቅሳሉ፤ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ትጮኻለች። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይሁዳ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ በምድርም ላይ ጨለሙ፥ የኢየሩሳሌም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአል። |
እግዚአብሔር በቃሉ ሁሉ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፤ እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣቸዋል።
እግዚአብሔርም ጩኸታቸውን ሰማ፤ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ዐሰበ።
ሞዓብ ራሷን ይዛ ትጮኻለች፤ ለልቧም ይረዳታል፤ እስከ ሴጎርም ድረስ ብቻዋን ታለቅሳለች። ሞዓብ እንደ ሦስት ዓመት ጥጃ ናትና በሉሒት ዐቀበት ትጮኻለች። በአሮሜዎን መንገድም ይመለሳሉ፤ ይጮኻሉም፥ ጥፋትና መናወጥም ይሆናል።
የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፤ ተወዳጁ አዲስ ተክልም የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ያደርጋል ብየ እጠብቅ ነበር፤ እነሆም፥ ዐመፅን አደረገ፤ ጽድቅንም አይደለም፥ ጩኸትን እንጂ።
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር በዚህ ሕዝብ ላይ አመጣለሁ፤ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔ ግን አልሰማቸውም።
በሚኖሩባት ሰዎች ክፋት ምድሪቱ የምታለቅሰውና የዱሩ ሣርስ ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቼ ነው? እግዚአብሔር ፍጻሜያችንን አያይም ብለዋልና እንስሶችና ወፎችም ጠፍተዋል።
ሊይዙኝ ጕድጓድ ቈፍረዋልና፥ ለእግሮችም ወጥመድ ሸሽገዋልና፥ በቤታቸው ጩኸት ይሰማ፤ ድንገትም በላያቸው ወንበዴን አምጣባቸው።
ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፤ በላይም ሰማይ ይጠቍራል፤ ተናግሬአለሁና፤ አልጸጸትም ወደፊት እሮጣለሁ፤ ከእርስዋም አልመለስም።
ጦረኞች በጦረኞች ላይ ተሰናክለው ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ ቃልሽን ሰምተዋል፤ ልቅሶሽም ምድርን ሞልቶአታል።”
በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ወድቄ ተሰብሬአለሁ፤ ጠቍሬማለሁ፤ ራስ ማዞርም ይዞኛል፤ ምጥ እንደያዛትም ሴት በመከራው እጨነቃለሁ።
ሔት። እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ያፈርስ ዘንድ ዐሰበ፤ የመለኪያውንም ገመድ ዘረጋ፤ እርስዋን ከማጥፋት እጁን አልመለሰም፤ ምሽጉና ቅጥሩ አለቀሱ፤ በአንድነትም ደከሙ።
ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፤ መወርወሪያዎችዋም ተሰበሩ፤ ንጉሥዋና አለቃዋ በአሕዛብ መካከል አሉ፤ ሕግም የለም። ነቢያቷም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላዩም።
ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ በእርስዋም ከሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፤ ከምድርም ተንቀሳቃሾች ጋር ትጠፋለች፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ።
መከሩ ከእርሻቸው ጠፍቶአልና ገበሬዎች ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ ዐፈሩ፤ የወይን አትክልተኞችም ስለ ወይኑ አለቀሱ።
ጾምን ቀድሱ፤ ምህላንም ዐውጁ፤ ሽማግሌዎቹንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም በአንድነት ጩኹ።
እኔም በምድርና በተራሮች፥ በእህልና በወይንም፥ በዘይትና ምድርም በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶችም ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ።
የእግዚአብሔር ታቦት ወደዚያ በገባች ጊዜ በከተማው ሁሉ ታላቅ ሁከት ሆኖአልና። በሕይወትም ያሉ፥ ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፤ የከተማዪቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ።
እንዲህም አለው፥ “ነገ በዚህች ሰዓት ከብንያም ሀገር አንድ ሰው እልክልሃለሁ፤ ልቅሶአቸው ወደ እኔ ስለ ደረሰ የሕዝቤን ሥቃያቸውን ተመልክችአለሁና ለሕዝቤ ለእስራኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ሕዝቤን ያድናል።”