ኤርምያስ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤልና ይሁዳ ቃል ኪዳንን እንዳፈረሱ 1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ፤ ለይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ተናገሩ፤ 3 እንደዚህም በሏቸው፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የዚህን ቃል ኪዳን ቃል የማይሰማ ሰው ርጉም ይሁን፤ 4 ከግብፅ ሀገር ከብረት ምድጃ ባወጣኋቸው ቀን ለአባቶቻችሁ ያዘዝሁትን፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ” ያልሁትን ቃሌን ስሙ። 5 ይህም ዛሬ እንደ ሆነ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻችሁ የማልሁትን መሐላ አጸና ዘንድ ነው። እኔም፥ “አቤቱ! ጌታ ሆይ! ይሁን” ብዬ መለስሁለት። 6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ይህችን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ተናገር፤ እንዲህም በል፦ የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ፤ አድርጉትም። 7 አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር ከአወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በማለዳ ተነሥቼ እያስጠነቀቅሁ፦ ቃሌን ስሙ በማለት አስጠንቅቄአቸው ነበር። 8 እነርሱ ሁሉ ግን በክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄዱ እንጂ አልሰሙም፤ ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ ስለዚህ ያዘዝኋቸውን እነርሱም ያላደረጉትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ሁሉ አመጣሁባቸው።” 9 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ዘንድ አድማ ተገኝቶአል። 10 ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ ወደ አሉ ወደ አባቶቻቸው ኀጢአት ተመለሱ፥ ያመልኩአቸውም ዘንድ እንግዶችን አማልክት ተከተሉ፤ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ከአባቶቻቸው ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፈረሱ። 11 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር በዚህ ሕዝብ ላይ አመጣለሁ፤ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔ ግን አልሰማቸውም። 12 በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሄደው ወደሚያጥኑላቸው፥ በመከራቸው ጊዜ ከቶ ወደማያድኗቸው አማልክት ይጮኻሉ። 13 ይሁዳ ሆይ! አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸው፤ እንደ ኢየሩሳሌምም መንገዶች ቍጥር ለነውረኛ ነገር ለበዓል ታጥኑባቸው ዘንድ መሠዊያዎችን አድርጋችኋል። 14 አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ በመከራቸው ቀን ወደ እኔ በጮኹ ጊዜ አልሰማቸውምና ስለ እነርሱ አትጸልይ፤ በምልጃና በጸሎት አትማልድ። 15 ወዳጄ በቤቴ ውስጥ ለምን ርኵሰትን አደረገች? ስእለት ወይም የተቀደሰ ሥጋ ክፋትሽን ከአንቺ ያስወግዳልን? ወይስ በእነዚህ ታመልጫለሽን? 16 እግዚአብሔር ስምሽን፦ በመልካም ፍሬ የተዋበችና የለመለመች የወይራ ዛፍ ብሎ ጠራው፤ ከመቈረጥዋም ድምፅ የተነሣ በላይዋ እሳት ነደደባት፤ ቅርንጫፎችዋም ተሰብረዋል። 17 ለበዓልም በማጠናቸው ያስቈጡኝ ዘንድ ለራሳቸው ስለ ሠሩአት ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ ቤት ክፋት የተከለሽ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክፉን ነገር ተናግሮብሻል። ኤርምያስን ለመግደል የተደረገ ሤራ 18 ጌታ ሆይ! አስታውቀኝ፤ እኔም አውቃለሁ፤ ያንጊዜም ሥራቸውን ገለጥህልኝ። 19 እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ ጠቦት በግ ሆንሁ፤ እነርሱም በእንጀራው ዕንጨት እንጨምር ስሙም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰብ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው ብለው ክፉ ምክርን እንዳሰቡብኝ አላወቅሁም ነበር። 20 ኵላሊትንና ልብን የምትፈትን፥ በቅንም የምትፈርድ እግዚአብሔር ሆይ! ክርክሬን ገልጬልሃለሁና ከእነርሱ ፍረድልኝ። 21 ስለዚህም፥ “በእጃችን እንዳትሞት በእግዚአብሔር ስም ትንቢት አትናገር” ብለው ነፍሴን ስለሚሹ ስለ አናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 22 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በመዓት እጐበኛቸዋለሁ፤ ጐበዛዝቶቻቸው በሰይፍ ይሞታሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ፤ 23 በምጐበኛቸውም ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁና ማንም ከእነርሱ የሚተርፍ የለም። |