ኤርምያስ 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ድርቅ 1 ስለ ድርቅ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 ይሁዳ አለቀሰች፤ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ፤ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የኢየሩሳሌምም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአል። 3 ታላላቆችዋም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ሰደዱ፤ ወደ ጕድጓድ መጡ፤ ውኃም አላገኙም፤ ዕቃቸውንም ባዶውን መለሱ፤ ዐፈሩም፤ ተዋረዱም፤ ራሳቸውንም ተከናነቡ። 4 በምድር ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ስለ ሆነ አራሾች ዐፈሩ፤ ራሳቸውንም ተከናነቡ። 5 ዋሊያዎች ደግሞ በምድረ በዳ ወለዱ፤ ሣርም የለምና ግልገሎቻቸውን ተዉ። 6 የሜዳ አህዮችም በወና ኮረብታ ላይ ቆመዋል፤ እንደ ሰገኖም ወደ ነፋስ አለከለኩ፤ ሣርም የለምና ዐይኖቻቸው ጠወለጉ። 7 አቤቱ! ኀጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኀጢአት ሠርተናልና ኀጢአታችን ተቃውሞናል፤ ነገር ግን ስለ ስምህ ብለህ አድርግ። 8 ጌታ ሆይ! አንተ የእስራኤል ተስፋ ነህ፤ በመከራም ጊዜ ታድነዋለህ፤ በምድር እንደ እንግዳ፥ ወደ ማደሪያም ዘወር እንደሚል መንገደኛ ስለ ምን ትሆናለህ? 9 እንዳንቀላፋ ሰው፥ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኀያል ስለ ምን ትሆናለህ? አንተ ግን አቤቱ! በመካከላችን ነህ፤ ስምህም በእኛ ላይ ተጠርትዋል፤ አትርሳንም። 10 እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፥ “መቅበዝበዝን ወድደዋል፤ እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፤ በደላቸውንም አሁን ያስባል፤ ኀጢአታቸውንም ይጐበኛል።” 11 እግዚአብሔርም አለኝ፥ “ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው። 12 ቢጾሙ ጸሎታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ቢያቀርቡም ደስ አልሰኝባቸውም፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ።” 13 እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! እነሆ ነቢያት፦ እውነትንና ሰላምን በዚህ ስፍራ እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፤ ራብም አያገኛችሁም ይሉአቸዋል” አልሁ። 14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውም፤ የሐሰቱን ራእይ፥ ምዋርትንም፥ ከንቱንም ነገር፥ በልባቸውም የፈጠሩትን ይተነብዩላችኋል።” 15 ስለዚህ እግዚአብሔር በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት ስላላክኋቸው፦ በዚህች ሀገር ሰይፍና ረሃብ አይሆንም ስለሚሉ ነቢያት እንዲህ ይላል፥ “እነዚያ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ። 16 ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም መንገዶች ይበተናሉ፤ ክፋታቸውንም አፈስስባቸዋለሁና እነርሱንና ሚስቶቻቸውን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም። 17 “እንደዚህም ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ የወገኔ ልጅ ድንግሊቱ በታላቅ ስብራትና እጅግ ክፉ በሆነ ቍስል ተሰብራለችና ዐይኖቻችሁ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባን ያፍስሱ። 18 ወደ ሜዳ ብወጣ፥ እነሆ በሰይፍ የሞቱ አሉ፤ ወደ ከተማም ብገባ፥ እነሆ በራብ የከሱ አሉ፤ ነቢዩና ካህኑ ወደማያውቋት ሀገር ሄደዋልና።” የሕዝቡ ምልጃ 19 በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለ ምን መታኸን? ፈውስስ ስለ ምን የለንም? ስለ ምን ተስፋ አደረግን? ነገር ግን መልካም ነገር አልተገኘም፤ የፈውስን ጊዜ ተስፋ አደረግን፤ ነገር ግን ድንጋጤ ሆነ። 20 አቤቱ በአንተ ላይ ኀጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን። 21 ስለ ስምህ ብለህ ተመለስልን፤ የክብርህንም ዙፋን አታጥፋ፤ ከእኛ ጋርም ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስብ እንጂ አታፍርስ። 22 በውኑ በአሕዛብ ጣዖታት መካከል ያዘንብ ዘንድ የሚችል ይገኛልን? ወይስ ሰማይ ዝናብ ሊሰጥና ሊያጠግብ ይችላልን? አቤቱ አምላካችን ሆይ አንተ አይደለህምን? አንተ ይህን ነገር ሁሉ አድርገሃልና ስለዚህ አንተን በተስፋ እንጠባበቃለን። |