Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ታላቁ ድርቅ

1 ወደ ኤርምያስ ስለ ድርቅ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው።

2 “ይሁዳ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ፤ ስለ ምድሪቱም አለቀሱ፤ የኢየሩሳሌም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሏል።

3 ታላላቆቻቸውም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ላኩ፤ ወደ ጉድጓድ መጡ ውኃም አላገኙም፥ ዕቃቸውንም ባዶውን ይዘው ተመለሱ፤ አፈሩም ተዋረዱም ራሳቸውንም ተከናነቡ።

4 በምድር ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ስለሆነ አራሾች አፈሩ ራሳቸውንም ተከናነቡ።

5 ዋላ ደግሞ በምድረ በዳ ወለደች፥ ሣርም የለምና ግልገልዋን ተወች።

6 የሜዳ አህዮችም በተራቈቱ ኮረብቶች ላይ ቆመዋል፥ እንደ ቀበሮም ወደ ነፋስ አለከለኩ፤ ልምላሜም የለምና ዐይኖቻቸው ጠወለጉ።

7 “ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአትን ሠርተናል፤ ምንም እንኳ ኃጢአታችን ቢመሰክርብንም ስለ ስምህ ብለህ አቤቱ! አድርግ።

8 አንተ የእስራኤል ተስፋ ሆይ! በመከራም ጊዜ የምታድነው፥ በምድሪቱ እንደ እንግዳ፥ ሌሊቱን ለማሳለፍ ወደ ማደርያ ዘወር እንደሚል መንገደኛ ለምን ትሆናለህ?

9 ግራ እንደ ተጋባ ሰው፥ ለማዳንም እንደማይችል ኃያል ለምን ትሆናለህ? አንተ ግን፥ አቤቱ! በመካከላችን ነህ፥ እኛም በስምህ ተጠርተናል፤ አትተወን።”

10 ጌታ ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “በእውነት መቅበዝበዝን ወድደዋል፥ እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ ጌታ በእነርሱ ደስ አይሰኝም፥ በደላቸውንም አሁን ያስታውሳል ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።”

11 ጌታም፦ “ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው።

12 በጾሙ ጊዜ ልመናቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም፤ ይልቁንም በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ” አለኝ።


ሐሰተኛ ነብያትን ማውገዝ

13 እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! እነሆ፥ ነቢያት፦ ‘ዘላቂ ሰላም በዚህ ስፍራ እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፥ ራብም አያገኛችሁም’ ይሉአቸዋል” አልሁ።

14 ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “ነቢያቱ በስሜ የውሸትን ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸትን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል።

15 ስለዚህ ጌታ በስሜ ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት፦ ‘በዚህች አገር ሰይፍና ራብ አይሆንም’ ስለሚሉ ስላላክኋቸው ነቢያት እንዲህ ይላል፦ እነዚህ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ።

16 ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይጣላሉ፤እነርሱንና ሚስቶቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም፤ ክፋታቸውንም በእነርሱ ላይ አወርድባቸዋለሁ።

17 ይህን ቃል እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘የወገኔ ልጅ ድንግሊቱ በታላቅ ስብራትና ፈጽሞ በማይሽር ቁስል ቆስላለችና ዐይኖቼ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባ ያፍስሱ።

18 ወደ ሜዳ ብወጣ፥ እነሆ፥ በሰይፍ የሞቱ አሉ፤ ወደ ከተማም ብገባ፥ እነሆ፥ በራብ ደዌ የከሱ አሉ፤ ነቢዩና ካህኑም ወደማያውቁት አገር ሄደዋልና።’”


ከጌታ ሕዝቡ ምሕረትን መለመኑ

19 በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለምን መታኸን? ፈውስስ ስለምን የለንም? ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ ፈውስን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ።

20 አቤቱ! በአንተ ላይ ኃጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን።

21 ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፥ የክብርህንም ዙፋን አታዋርድ፤ ከእኛ ጋርም ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስታውስ እንጂ አታፍርስ።

22 በውኑ በአሕዛብ ከንቱ ጣዖታት መካከል ዝናብን ሊያዘንብ የሚችል ይገኛልን? ወይስ ሰማይ ካፊያን መስጠት ይችላልን? አቤቱ አምላካችን ሆይ! አንተ አይደለህምን? አንተ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አድርገሃልና ስለዚህ አንተን በተስፋ እንጠባበቃለን።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos