ኢሳይያስ 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ፍርድ በምድር ላይ 1 እነሆ፥ እግዚአብሔር ዓለምን ያጠፋታል፤ ባድማም ያደርጋታል፤ ይገለብጣትማል፤ በእርስዋም የተቀመጡትን ይበትናል። 2 ሕዝቡ እንደ ካህኑ፥ ባሪያውም እንደ ጌታው ባሪያይቱም እንደ እመቤቷ፥ የሚሸጠውም እንደሚገዛው፥ ተበዳሪውም እንደ አበዳሪው፥ ዕዳ ከፋዩም እንደ ዕዳ አስከፋዩ ይሆናል። 3 እነሆ፥ ምድር መፈታትን ትፈታለች፤ ፈጽማም ትበረበራለች፤ የእግዚአብሔር አፍ እንዲህ ተናግሮአልና። 4 ምድርም አለቀሰች፤ ጠፋችም፤ ዓለም ተገለበጠች፤ የምድርም ታላላቆች አለቀሱ። 5 ምድርም በሚቀመጡባት ሰዎች ምክንያት በደለች፤ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዐቱንም ለውጠዋልና፥ የዘለዓለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና። 6 ስለዚህ ምድር ትውጣቸዋለች፤ በእርስዋ የተቀመጡ በድለዋልና፤ በምድር የሚኖሩ ሰዎችም ይቸገራሉ፤ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ። 7 የወይን ጠጅ አለቀሰች፤ የወይን ግንድ ደከመች፤ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ። 8 የከበሮአቸው ደስታ አልቆአል፤ መታጀራቸውም አልቃለች፤ የኃጥኣን ሀብት አልቆአል፤ የመሰንቆ ድምፅም ቀርቶአል። 9 ወይንን የሚጠጡት አፈሩ፤ የሚያሰክር መጠጥም ለሚጠጡት መራራ ሆነ። 10 ከተሞች ሁሉ ምድረ በዳ ሆኑ፤ ቤቶችም ሁሉ ማንም እንዳይገባባቸው ተዘጉ። 11 ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ አልቅሱ፤ የምድር ደስታ ሁሉ ጨልሞአልና፥ የምድርም ሐሤት ፈልሶአልና። 12 ከተሞችም ባድማ ይሆናሉ፤ ቤቶችም ባዶ ሆነው ይቀራሉ፤ ይጠፋሉም። 13 ይህ ሁሉ በሀገር ውስጥ በአሕዛብ መካከል ይሆናል። የወይራ ፍሬ ለቀማ ባለቀ ጊዜ በቃርሚያው ውስጥ የወይራ ፍሬ እንደሚለቀም እንዲሁ የእስራኤልን ልጆች ይቃርሟቸዋል። 14 እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፤ በምድር የቀሩትም ስለ እግዚአብሔር ክብር በአንድነት ደስ ይላቸዋል፤ የባሕርም ውኃ ይናወጣል። 15 ስለዚህም የእግዚአብሔር ክብር በባሕር ደሴቶች ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም ስም ይከብራል። 16 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ የጻድቁን ድንቅ ተስፋ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እነርሱ ግን፥ “የእግዚአብሔርን ሕግ ለሚያፈርሱ ወንጀለኞች ወዮላቸው!” አሉ። 17 በምድር ላይ በሚኖሩ፥ ፍርሀትና ገደል ወጥመድም አሉ። 18 የሰማይ መስኮቶችም ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና ከፍርሀት ድምፅ የሸሸ በገደል ይወድቃል፤ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። 19 ምድር ደነገጠች፤ ታወከችም፤ ምድር ጐሰቈለች፤ ተነዋወጠችም። 20 ምድር በወይን እንደ ሰከረ ሰው ትንገዳገዳለች፤ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ ሕግን መተላለፍዋም ይከብድባታል፤ ትወድቅማለች፤ ደግማም አትነሣም። 21 በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በሰማይ ሠራዊትና በምድር ነገሥታት ላይ እጁን ይጥላል። 22 እነርሱም ይሰበሰባሉ፤ ተዘግቶባቸውም በግዞት ቤት ይኖራሉ፤ ከብዙ ትውልድም በኋላ ይጐበኛሉ። 23 ጣራቸው ይፈርሳል፤ ግድግዳቸውም ይወድቃል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣልና፥ በሽማግሌዎቹም ፊት ይከብራልና። |