ሆሴዕ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ወቀሰ 1 እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ምሕረት፥ እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚኖሩትን ይወቅሳልና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 2 ነገር ግን ሐሰት፥ ግዳይና ስርቆት፥ ምንዝርናም ምድርን ሞልተዋል፤ ደምንም ከደም ጋር ይቀላቅላሉ። 3 ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ በእርስዋም ከሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፤ ከምድርም ተንቀሳቃሾች ጋር ትጠፋለች፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። 4 ነገር ግን ሕዝቤ እንደሚከራከር ካህን ነውና እንግዲህ የሚከራከር፥ ማንም አይኑር፥ የሚዘልፍም ማንም አይኑር። 5 በቀንም ትደክማለህ፤ ነቢዩም ከአንተ ጋር ይደክማል፤ እናታችሁም ሌሊትን ትመስላለች። 6 ሕዝቤ አእምሮ እንደሌላቸው ይመስላሉ፤ አንተም አእምሮህ ተለይቶሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እተውሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። 7 እንደ ብዛታቸው መጠን ኀጢአት ሠሩብኝ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ውርደት እለውጣለሁ። 8 ሕዝቤንም ኀጢአታቸው ትበላቸዋለች፤ ሰውነታቸውንም በበደላቸው ይወስዷታል። 9 እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፤ እንደ ሥራቸውም እከፍላቸዋለሁ። 10 እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም፤ ሲያመነዝሩም አይበዙም። 11 የሕዝቤ ልቡናቸው ዝሙትን፥ መጠጥንና ስካርን ወደደ። 12 ሕዝቤ በዝሙት መንፈስ ስተዋልና ከአምላካቸውም ርቀው አመንዝረዋልና በትርን ይጠይቃሉ፤ በትሩም ይመልስላቸዋል። 13 በተራሮችም ራስና በኮረብታዎች ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከኮምበልና ከልብን፥ ከአሆማም ዛፍ በታች ያርዳሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ይሰስናሉ፤ ሙሽሮቻችሁም ያመነዝራሉ። 14 ወንዶችም ደግሞ ከአመንዝሮች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰሰኑ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁም በአመነዘሩ ጊዜ አልቀጣኋቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ከአመንዝራ ጋር ይቀላቀላል። 15 እስራኤል ሆይ! አንተ አላዋቂ አትሁን፤ አንተም ይሁዳ! ወደ ጌልጌላ አትሂድ፤ ወደ ቤትአዊንም አትውጡ፤ በሕያው እግዚአብሔርም አትማሉ። 16 እስራኤል እንደምትደነብር ጊደር ደንብሮአል፤ እግዚአብሔርም በሰፊው ቦታ እንደ ጠቦት ያሰማራዋል። 17 እንዲሁም ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጋጠመ፤ ለራሱም ዕንቅፋትን አኖረ። 18 ከነዓናውያንንም መረጣቸው፤ ፈጽመውም አመነዘሩ፤ በክፋታቸውም ውርደትን መረጡ። 19 አንተ በክንፎችዋ ውስጥ የነፋስ መናወጥ ነህ፤ ከመሥዋዕታቸውም የተነሣ ያፍራሉ። |