ኢሳይያስ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ወይን ቦታ የተነገረ መዝሙር 1 አሁን የወይኔን ቦታ በተመለከተ የወዳጄን መዝሙር ለወዳጄ እዘምራለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማው ቦታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው። 2 አጥር አጠርሁ፤ በዙሪያውም ቈፈርሁ፤ ድንጋዮችንም ለቅሜ አወጣሁ፤ ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከልሁ፤ በመካከሉም ግንብ ሠራሁ፤ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማስሁለት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ጠበቅሁት፤ ዳሩ ግን እሾህን አፈራ። 3 አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፥ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ። 4 ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድን ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ጠበቅሁት፤ ነገር ግን እሾህን አፈራ። 5 አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ፤ አጥሩን እነቅላለሁ፤ ለብዝበዛም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፤ ለመራገጫም ይሆናል። 6 ባድማ አደርገዋለሁ፤ አይገረዝም፤ አይኰተኰትም፤ እንደ ጠፍ ቦታ ኵርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፤ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ደመናዎችን አዝዛለሁ። 7 የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፤ ተወዳጁ አዲስ ተክልም የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ያደርጋል ብየ እጠብቅ ነበር፤ እነሆም፥ ዐመፅን አደረገ፤ ጽድቅንም አይደለም፥ ጩኸትን እንጂ። 8 ከጎረቤቶቻቸው እርሻ ይወስዱ ዘንድ፥ ምድርንም ለብቻቸው ይይዟት ዘንድ፥ ቤትን ከቤት ጋር ለሚያያይዙ፥ እርሻንም ከእርሻ ጋር ለሚያቀራርቡ ወዮላቸው! 9 ይህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰምቶአልና፦ ቤቶች ቢሠሩ ባድማ ይሆናሉ፤ ታላላቅና የሚያምሩ ቤቶችም የሚቀመጥባቸው አይኖርም። 10 ዐሥር ጥማድ በሬ ካረሰው የወይን ቦታ አንድ ፊቀን ወይን ጠጅ ይወጣል፤ ስድስት መስፈሪያ የዘራ ሦስት መሥፈሪያ ብቻ ያገባል። 11 በጥዋት ወደ መሸታ ቤት ለሚገሠግሡና በመጠጥ ቤት ለሚውሉ ወዮላቸው! ወይኑ ያቃጥላቸዋልና። 12 በመሰንቆና በበገና፥ በከበሮና በእምቢልታም እየዘፈኑ የወይን ጠጅን ይጠጣሉ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም፤ የእጁንም ሥራ አላስተዋሉም። 13 ስለዚህም ሕዝቤ ወደ ምርኮ ሄዱ፤ እግዚአብሔርን አላወቁትምና፤ ብዙዎቹ በረኃብና በውኃ ጥም ሞቱ፤ 14 ሲኦልም ሆድዋን አስፍታለች፤ አፍዋንም ያለ ልክ ከፍታለች፤ የተከበሩና ታላላቅ ሰዎች ባለጠጎቻቸውና ድሆቻቸውም ወደ እርስዋ ይወርዳሉ። 15 ታናሹ ሰውም ይጐሰቍላል፤ ታላቁ ሰውም ይዋረዳል፤ የትዕቢተኞችም ዐይኖች ይዋረዳሉ፤ 16 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍርድ ከፍ ከፍ ይላል፤ ቅዱሱም አምላክ በጽድቅ ይከብራል። 17 የተማረኩ እንደ በሬዎች ይሰማራሉ፤ የተረሱትም ምግባቸውን ሲፈልጉ እንደ በግ ጠቦቶች በማሰማርያቸው ይሰማራሉ። 18 በደልን እንደ ረዥም ገመድ ለሚስቡ፥ ኀጢአትንም እንደ በሬ ቀንበር ለሚያስሩ ወዮላቸው! 19 “እናይ ዘንድ፥ ሥራውን ያፋጥን፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ምክር፥ ትምጣ” ለሚሉ ወዮላቸው! 20 ክፉውን መልካም መልካሙንም ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው! 21 ለክፋት ጥበበኞች ለሆኑ፥ እኛ ጠቢባን ነን ለሚሉም ወዮላቸው! 22 የወይን ጠጅ ለሚጠጡ ኀያላን፥ የሚያሰክረውንም መጠጥ ለሚደባልቁ ጽኑዓን ወዮላቸው! 23 በደለኛውን ስለ ጉቦ ጻድቅ ለሚያደርጉ፥ የጻድቁንም ጽድቅ ለሚያስወግዱበት ወዮላቸው! 24 ስለዚህ ገለባ በእሳት ፍም እንደሚቃጠል፥ በነበልባልም እንደሚበላ፥ እንዲሁ የእነርሱ ሥር የበሰበሰ ይሆናል፤ አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፤ የእስራኤልም ቅዱስ የተናገረውን ቃል አቃልለዋልና። 25 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ታላቅ ቍጣን ተቈጣ፤ እጁንም በላያቸው ዘርግቶ መትቶአቸዋል፤ ተራሮችም ተንቀጠቀጡ፤ ሬሳቸውም በመንገድ መካከል እንደ ጕድፍ ሆኖአል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 26 በሩቅ ላሉ አሕዛብም ምልክትን ያቆማል፤ ከምድርም ዳርቻ በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እነሆም፥ እየተጣደፉ ፈጥነው ይመጣሉ። 27 አይራቡም፤ አይጠሙምም፤ አይደክሙም፤ አይተኙም፤ የወገባቸውን መታጠቂያ አይፈቱም፤ የጫማቸውም ማዘቢያ አይበጠስም። 28 ፍላጾቻቸው ተስለዋል፤ ቀስቶቻቸውም ሁሉ ተለጥጠዋል፤ የፈረሶቻቸውም ኮቴ እንደ ቡላድ፥ የሰረገሎቻቸውም መንኰራኵር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይቈጠራል። 29 ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤ እንደ አንበሳ ደቦሎችም ይቆማሉ፤ ከጕድጓዱ እንደሚወጣ አውሬም ይነጥቃሉ፤ ይጮሃሉ፤ የሚድንም የለም። 30 በዚያም ቀን እንደ ባሕር መትመም ይተምሙባቸዋል፤ ወደ ምድርም ይመለከታሉ፤ ድቅድቅ ጨለማን ያያሉ፤ ይጨነቃሉም። |