Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ አሠቃቂው ድርቅ

1 እግዚአብሔር ወደ ፊት ስለሚመጣው ድርቅ እንዲህ አለኝ፥

2 “ይሁዳ በሐዘን ላይ ነች፤ ከተሞችዋም በሞት ጣዕር ላይ ናቸው፤ ሕዝብዋም በሐዘን ምክንያት በመሬት ላይ ተቀምጠው ያለቅሳሉ፤ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ትጮኻለች።

3 ሀብታሞች ውሃ ለማግኘት ሠራተኞቻቸውን ይልካሉ፤ እነርሱም ወደ ውሃ ጒድጓዶች ይሄዳሉ፤ ነገር ግን ምንም ውሃ ስለማያገኙ፥ ባዶ እንስራ ተሸክመው ይመለሳሉ፤ ተስፋ ቈርጠው ግራ ስለሚጋቡ፥ በሐዘን ራሳቸውን ይሸፍናሉ።

4 ዝናብ ከመጥፋቱ የተነሣ፥ ምድር ትደርቃለች፤ ገበሬዎችም ተስፋ በመቊረጥ፥ በሐዘን ራሳቸውን ይሸፍናሉ።

5 ሣር ካለመገኘቱ የተነሣ፥ አጋዘን እንደ ወለደች ግልገልዋን በሜዳ ላይ ጥላ ትሄዳለች።

6 የሜዳ አህዮች ከውሃ ጥም የተነሣ፥ በየኰረብታው ጫፍ ላይ ቆመው እንደ ቀበሮ ያለከልካሉ፤ ምግብ ስለማያገኙም የማየት ኀይላቸው ይቀንሳል።

7 ሕዝቤም ወደ እኔ እንዲህ በማለት ይጮኻሉ፤ ‘ምንም እንኳ የበደላችን ብዛት በእኛ ላይ ቢመሰክርም፥ እግዚአብሔር ሆይ! በተስፋ ቃልህ መሠረት እርዳን፤ ከአንተ ርቀናል፤ አንተንም አሳዝነናል።

8 የእስራኤል ተስፋ አንተ ብቻ ነህ፤ ከመቅሠፍት የምታድነንም አንተ ነህ፤ ታዲያ በምድራችን እንደ እንግዳ፥ ለአንድ ቀን እንደሚያድር መንገደኛስ የሆንከው ለምንድን ነው?

9 ለምን ግራ እንደ ተጋባ ሰውና ሌላውን መርዳት እንደማይችል ኀይለኛ ወታደር ትሆናለህ? እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን በመካከላችን ነህ፤ በስምህም እንጠራለን፤ እባክህ አትተወን።’ ”

10 እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “ከእኔ ርቀው መሄድ ይወዳሉ፤ ራሳቸውንም አይቈጣጠሩም፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ደስ አልሰኝም፤ የፈጸሙትን በደል ሁሉ በማስታወስ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።”

11 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ “ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤

12 እየጾሙ ቢጸልዩ እንኳ አላዳምጣቸውም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ የእህል ቊርባን ቢያቀርቡልኝ እንኳ በእነርሱ ደስ አልሰኝም፤ ይልቁንም በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ እንዲያልቁ አደርጋለሁ።”

13 እኔም እንዲህ አልኩ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ነቢያቱ ‘ጦርነት ሆነ ራብ አይኖርም’ እያሉ ለሕዝቡ ይናገራሉ፤ ‘በምድራችን ዘላቂ ሰላም ብቻ እንደሚሰፍን እግዚአብሔር ተናግሮአል’ ይላሉ።”

14 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ነቢያቱ በእኔ ስም ሐሰት ይናገራሉ፤ እኔ አላክኋቸውም፤ ትእዛዝም አልሰጠኋቸውም፤ አንድ ቃል እንኳ አልነገርኳቸውም፤ አየን የሚሉት ራእይ ሁሉ ከእኔ የተገኘ አይደለም፤ ትንቢታቸው ሁሉ የሐሰት ራእይ፥ መተት፥ ጣዖት አምልኮና ከሐሳባቸው ያፈለቁት ከንቱ ነገር ነው።

15 እኔ ሳልካቸው ‘በምድራችን ላይ ራብም ሆነ ጦርነት አይመጣም’ እያሉ በስሜ ትንቢት የሚናገሩትን እነዚህን ነቢያት እኔ እግዚአብሔር በጦርነትና በረሀብ እንዲሞቱ አደርጋለሁ።

16 ይህንንም የተነበዩላቸው ሕዝብ ሁሉ በራብና በጦርነት ይሞታሉ፤ ሬሳቸውም ሁሉ በኢየሩሳሌም ውስጥ በየመንገዱ ይወድቃል፤ የሚቀብራቸውም አይኖርም፤ ይህም በሚስቶቻቸው፥ በወንዶች ልጆቻቸውና በሴቶች ልጆቻቸው ሳይቀር በሁሉም ላይ ይፈጸማል፤ በበደላቸውም መጠን ተገቢ ቅጣታቸውን እሰጣቸዋለሁ።”

17 ስለዚህ ጉዳይ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ብዬ እንድናገር አዘዘኝ። “ሕዝቤ እጅግ ቈስሎአል፤ በብርቱም ተጐድቶአል፤ ስለዚህ ዐይኖቼ ቀንና ሌሊት እንባ ያፈሳሉ፤ ባለማቋረጥም አለቅሳለሁ።

18 ወደየመስኩ ብወጣ በጦርነት የተገደሉ ሰዎችን ሬሳ አያለሁ፤ ወደ ከተማም ብገባ በራብ ለመሞት የሚያጣጥሩ ሰዎችን አያለሁ፤ ነቢያትና ካህናት የራሳቸውን ጉዳይ ይከታተላሉ፤ ነገር ግን የሚያደርጉትን አያውቁም።”


ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ያቀረቡት ምልጃ

19 እግዚአብሔር ሆይ! ይሁዳን ፈጽመህ ልትጥላት ነውን? የጽዮንንስ ሕዝብ እንደ ጠላህ መቅረትህ ነውን? ለመፈወስ እስከማንችል ድረስ፥ ይህን ያኽል እንድንጐዳ ማድረግህስ ስለምንድን ነው? ሰላም እናገኛለን ብለን ተስፋ አደረግን፥ ነገር ግን ምንም መልካም ነገር አልገጠመንም፤ ፈውስ እናገኛለን ብለን ተስፋ አደረግን፤ ነገር ግን ሽብር እየበዛ ሄደ።

20 እግዚአብሔር ሆይ! እኛ አንተን በድለናል፤ ስለዚህም የራሳችንንና የቀድሞ አባቶቻችንን ኃጢአት በፊትህ እንናዘዛለን።

21 የተስፋ ቃልህን ሁሉ በማሰብ እኛን አትናቀን፤ ግርማህ የሚገለጥበት የክብር ዙፋንህ መኖሪያ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን አታዋርዳት፤ ከእኛም ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን አስብ።

22 ከአሕዛብ አማልክት መካከል አንዱ እንኳ ዝናብ ማዝነብ አይችልም፤ ሰማይም በራሱ ፈቃድ ካፊያ አያወርድም፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! ይህን ሁሉ የምታደርግ አንተ ስለ ሆንክ እኛ ተስፋ የምናደርገው በአንተ ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos